የደቡብ አፍሪቃዉ ድርድር እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየት
ሰኞ፣ ጥቅምት 14 2015
ከጥቂት ቀናት በኃላ ሁለት ዓመት የሚሞላው የሰሜን ኢትዩጵያዉ ጦርነት ላይ እየተዋጉ ያሉት የፌደራል መንግስት እና የህውሓት ኃይሎች ዛሬ ለመጀመሪያ ግዜ በአፍሪቃ ኅብረት አደራዳሪነት የሰላም ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ነዉ። ሁለቱም አካላት ወክለው የላክወቸውን የልዑካን ቡድኖች ደቡብ አፍሪቃ ገብተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመጀመሪያ ግዜ ከሚደረገው ከዚህ ድርድር ምን ይጠብቃሉ? ምንስ ተስፋ ያደርጋሉ። ይህን ጥያቄ መጀመርያ ያቀረብነዉ ለኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ነበር። ፕሮፌሰር መረራ እንደሚሉት ድርድሩ ይሳካል የሚል ብዙም ተስፋ የለኝም ብለዋል።
« ካለው ጫና አንድ እርምጃ ወደፊት ሊመጡ ይችላሉ ጦርነት የማቆም ሁኔታ ማለት ነው። አለበለዚያ ብዙ ችግር አለው እኔ ብዙም ተስፋ የለኝም» ያሉት ፕሮፌሰር መረራ ሌሎች ጉዳዩች ግን ግዜ የሚሹ የተወሳሰቡ ነገሮች አሉ ብለዋል ለዚህም እንደምሳሌ ሲያነሱ «ኤርትራ መግባቱ የራሱ ጥያቄ አለ፣ የወልቃይት ጠገዴ የመሬት ጥያቄ አለ ፣የስልጣን ጥያቄ አለ እንዲሁም ሁለቱ አካላት ያደረጉት የምርጫ ክርክር አለ ስለዚ ይሄን ሁሉ የሚይዝ መሆን አለበት በአገሪቱ ደረጃ ሰላም እና መረጋጋት ለመፍጠር » ብለዋል የአፍሪካ ህብረት ተኩስ አቁም ላይ ሊበረታ ይችላል ይሳካላቸው አይሳካላቸው የምናየው ይሆናል ሲሉ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል ።
ሌላው የብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ በአጭሩ ባይቶና የህግ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዩሴፍ ኃይለስላሴም ድርድሩ ይሳካል የሚል ተስፋ የለኝም ይላሉ። እንደ አቶ ዮሴፍ ምን አልባት በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ላይ የውጪ ኃያላት ተጽእኖ ካደረጉባቸው የሰላም ድርድሩ ሊሳካ ይችላል። ነገር ግን ሁለቱም አካላት ለምን ተዋጋን የሚል ጥያቄ እንዳይመጣባቸው አሁንም ጦርነቱን ይፈልጉታል ባይናቸዉ። « ድርድሩ የማን እንደሆነ እንኩዋን አናውቅም ብዙ አካላት ነው ያሉበት ምዕራባውያን የፌደራል መንግስት እና ህውሀት ናቸው በድርድሩ ተሳታፊ የሆኑት የአማራና የኤርትራ አካላት በቀጥታ መሳተፍ አለባቸው እነሱ ተሳታፊ ካልሆኑ እኔ የሚሳካ አይመስለኝም» ብለዋል አክለውም ብዙ ወንጀል ስለተሰራ ህዝቡ ጥያቄ ያቀርባል ለምን ተዋጋችሁ ለምን አቆማችሁ ይባላሉ ስለዚ በስልጣናቸው ላይ አደጋ ይመጣል በዚ ምክንያት ጦርነቱን ይፈልጉታል ብለዋል።
ዶክተር ደሳለኝ ጫኔየህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል በበኩላቸው የሰላም ድርድሩ ጦርነት እንዲቆም በሰላም እንዲቁዋጭ ነው እኔ ለሰባዊ መብት ተጠያዊ የሆኑ አካላት ተጠያቂ ይሆናሉ ብለን ነው ምናስበው ሲሉ አክለውም «በአማራ በአፋር እና በትግራይ ከፍተኛ ውድመት ያደረሰ ነው ይህ ጦርነት በህውሀት ወታደሮች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ መግባባት ላይ ይደረሳል የሚል ግምት አለኝ » ሲሉ አክለውም «መተኳኮሱ መተላለቁ ይቆማል የሚል ግምት አለኝ» ብለዋል የአማራ ህዝብ በዚ ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል በዚ የድርድር ሂደት ውስጥ አማራ እንደ አማራ ከፌደራል መንግስቱ በተለየ መወከል መሳተፍ አለበት ብለን እናምናለን ብለዋል ።
ከዚቀደም የተለያዩ የዓለም መንግስታት ሁለቱ አካላት ጦርነት አቁመው ወደ ድርድር እንዲመጡ በተለያዩ ግዜያት ሙከራ ቢደረግም ሊሳካ አለመቻሉ ይታወሳል። ዛሬ በደቡብ አፍሪቃ ለመጀመሪያ ግዜ የሚካሄደው ድርድር በኢትዮጵያ የሚታየዉን ጦርነት አስቆሙ ህዝቡ ሰላምን ያገኛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
ማኅሌት ፋሲል
አዜብ ታደሰ