1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሴ በኢትዮጵያ ስለታገቱት ተማሪዎች መግለጫ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2016

«በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በቅርቡ እና ተከታታይ እገታዎች» መከሰታቸው እንዳሳሰበው አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ትናንት ዐሳውቋል ። ፖለቲከኞች፦ ለትጥቅ ግጭት ምክንያት የሆኑ ፖለቲካዊ ሁናቴዎች ቶሎ እልባት አለማግኘታቸው ለተገባበት የደህንነት ምስቅልቅል መነሻ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

US Ambassador Ervin Massinga and USAID   Assistance Sonali Korde
ምስል Seyoum Getu/DW

«ድርጊቱን ማንም ይፈጽም ማን እገታ ሰይጣናዊ ተግባር ነው»

This browser does not support the audio element.

«በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በቅርቡ እና ተከታታይ እገታዎች» መከሰታቸው እንዳሳሰበው አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ትናንት ዐሳውቋል ። በአምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ስም መግለጫ ያወጣው ኤምባሲውን ጨምሮ የሰብአዊ ተቋማት እና ፖለቲከኞች ጭምር ጉዳዩ ስጋት እንዳሳደረባቸው አስተያየት በመስጠት ድርጊቱን እየኮነኑ ነው ። የአሜሪካ ኤምባሲ በትናንቱ መግለጫ፦ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ እገታዎች የግጭቶች መራዘም ውጤት ቢሆኑም ሊቆሙ ግን ይገባለል ሲል አሳስቧል ። ኤምባሲው ባለፈው ሳምንት  ከ100 በላይ ተማሪዎች እና መንገደኞች ታግተው ገንዘብ እየተጠየቀባቸው መሆኑንም በአሳሳቢነቱ ጠቅሷል ። 

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጠዋት ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ ቁጥራቸው ከ 100 በላይ ይሆናል የተባሉ ተማሪዎች ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አካባቢ በታጣቂዎች ከታገቱ በኋላ የተማሪዎቹ ቤሰተቦች በጭንቀት ላይ ወድቀዋል፡፡ 

የእገታ መባባስ አሳሳብነት እና መፍትኄው

ሰሞነኛው የተማሪዎች እገታ ክፉኛ እንዳስደነገጣቸው ገልጸው፤ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ፖለቲከኛ ራሔል ባፌ ለትጥቅ ግጭት ምክንያት የሆኑ ፖለቲካዊ ሁናቴዎች ቶሎ እልባት አለማግኘታቸው ለተገባበት የደህንነት ምስቅልቅል መነሻ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

«መሰረታዊ ችግሩ በአገሪቱ ስነሱ የነበሩ የፖለቲካ ጥያቄዎች ፖለቲካ ምላሽ አለማግኘታቸው ነው፡፡ ጥያቄዎቹ ወደ ጎን መገፋታቸው ፈተናውን አባብሷል» ብለዋል ። ፖለቲከኛ ራሔል እገታውም በተለያዩ አካላት እና መንገዶች ሊወሰዱ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ «እያገተ የሚዘርፍ አካል፣ ያለ እገታ በጦር መሣሪያ አስፈራርቶ መንገድ ላይ የሚዘርፍ እንዲሁም ታጣቂዎቹ እራሳቸው ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም አሊያም ለመሳሪያ ግዢ ማኅበረሰቡን እያገቱ ሊዘርፉ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ ከዚህ ውጪ ታጣቂን መስሎ የሚዘርፍም ይኖራል» ነው ያሉት፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ እና የዩኤስኤይድ ረዳት ሶናሊ ኮርዴ። ፎቶ፦ ከማኅደር ምስል Seyoum Getu/DW

«ድርጊቱን ማንም ይፈጽም ማን እገታ ሰይጣናዊ ተግባር ነው»

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ ባለሥልጣን ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ በፊናቸው ድርጊቱን ማንም ይፈጽም ማን እገታ ሰይጣናዊ ተግባር ነው ብለውታል ። «ፈጣሪ እና መንግስት ላይ ራሳቸውን ጥለው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚሄዱ ንጹሃን ሰዎችን እንዲህ ማድረግ ሰይጣናዊ ተግባር ነው፡፡ ይህ ለመንግስትም ለአገርም አስነዋሪ ከመሆኑም ባሻገር የፖለቲካ ስርዓቱ መዳከምን የሚያሳይ ነው» ብለዋል፡፡

ፖለቲከኞቹ ከነዚህ አስነዋሪ ካሉት ተግባራቱ መውጣት የሚቻልበትን መንገድ ስጠቁሙም፤ «አንደኛው ሕዝብ፣ መንግስት እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ለህዝብ ደህንነት ሲባል በሕግ የበላይነት ላይ መሥራት ነው» ብለዋል ። «መንግስት መሰል ከፍተኛ ድንጋጤን የሚፈጥሩ ጉዳዮች ስከሰቱ ለሕዝብ መረጃን ከመስጠት ጀምሮ የተለየ ትኩረት በመውሰድ የፌደራል መንገዶችን የመጠበቅ ተግባራትን መከወን አለበት» ሲሉም እንደ መፍትሄ የተመለከቱትን ሐሳባቸውን አጋርተዋል ። 

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW