ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተመሠረቱ ክሶች ተነሱ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 17 2017በዩናይትድ ስቴትስ ልዩ አቃቤ ሕግ ጃክ ስሚዝ በኩል በፕሬዝዳንት ተመርጩ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተመሰረቱ ክሶች ውድቅ ተደረጉ ። ሕጋዊ ምርጫን ለመገልበጥ በማሴርና የአሜሪካን ምሥጢራዊ ሰነዶች አላግባብ በመጠቀም የቀረቡባቸው ክሶችም ሆኑ ማስረጃወቹ ጠንካራ ቢሆኑም ዶናልድ ትራምፕ ዳግም በመመረጣቸውና ያለመከሰስ መብት ስለሚኖራቸው ክሱ እንዲቆም መጠየቃቸውን ከሳሹ ልዩ አቃቢ ሕግ ጃክ ስሚዝ በማመልከቻቸው ላይ ገልጸዋል ። ይሄው ውሳኔ በዶናልድ ትራምፕና ደጋፊዎቻቸው ሲሞገስ በተቃዋሚወቻቸው በኩል ደግሞ ፍትህ ላይ የተሰራ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ ተቆጥሯል ።
በልዩ አቃቤ ሕግ ጃክ ስሚዝ በኩል በፕሬዝዳንት ተመርጩ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተመሰረቱ ክሶች ውድቅ ተደረጉ። ሕጋዊ ምርጫን ለመገልበጥ በማሴርና የአሜሪካን ሚስጥራዊ ሰነዶች አላግባብ በመጠቀም የቀረቡባቸው ክሶችም ሆኑ ማስረጃወቹ ጠንካራ ቢሆኑም ዶናልድ ትራምፕ ዳግም በመመረጣቸውና ያለመከሰስ መብት ስለሚኖራቸው ክሱ እንዲቆም መጠየቃቸውን ከሳሹ ልዩ አቃቢ ሕግ ጃክ ስሚዝ በማመልከቻቸው ላይ ገልጸውል። ይሄው ውሳኔ በዶናልድ ትራምፕና ደጋፊወቻቸው ሲሞገስ በተቃዋሚወቻቸው በኩል ደግሞ ፍትህ ላይ የተሰራ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ ተቆጥሯል።
ልዩ አቃቤ ሕጉ ጃክ ስሚዝ ክሶቹን ውድቅ አድርገዋል
ዶናልድ ትራምፕ ላይ ክስ እንዲመሰርቱ የተሾሙት ልዩ አቃቤ ሕግ ጃክ ስሚዝ፣ ዶናልድ ትራምፕ ሕጋዊ የምርጫ ውጤትን ለመገልበጥ በመሞከርና የአሜሪካንን ምሥጢራዊ ሰነዶች አላግባብ በመጠቀም የተመሰረተባቸው ክስ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱም ክሶች ጥፋተኛ ተብለው ክሳቸውን የሚከታተሉ ቢሆኑም ዳግም መመረጣቸው ለክሱ መቋረጥ ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል።
ልዩ አቃቤ ሕጉ ጃክ ስሚዝ በዚሁ የክስ ውድቅ ማድረግያ ማመልከቻቸው ላይ እንዳሉት የክሱ ጭብጥ ላይ የተለወጠ ነገር የለም። ማስረጃወቹም አሁንም ጠንካሮች ናቸው። የተለወጠው አንድ ነገር ዶናልድ ትራምፕ ዳግም መመረጣቸው ብቻ ነው። እናም ክሱ ዶናልድ ትራምፕ ቃለ መሐላ ሳይፈጽሙ ውድቅ ይደረግልኝ ብለዋል። የኒውዮርክ ግዛት ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞው ዳኛ ዲያን ኬሰል ይሄው የሆነው በፍትህ ሚኒስቴር በኩል በስልጣን ላይ ባለ ፕሬዝዳንት ላይ መሰል ክስ ማካሄድ የማያስችል መርህ ስላለ ነው ብለዋል።
ይሄው የክስ ማቆምያ ጥያቄ የቀረበላቸው ዳኛም ጥያቄውን ተቀብለው ክሱን ሰርዘዋል። ይሄንኑ ውሳኔ ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ በተጋረጡብኝ ፈተናወች ፊት ሁሉ ጸንቼ አለፍኩ፣ እናም አሸነፍኩ ብለዋል። የትራምፕ ቃል አቀባይ ስቴቨን ቸንግ በበኩላቸው ይሄው ክስተት ለሕግ የበላይነት ታላቅ ድል እንደሆነ ገልጸው ዶናልድ ትራምፕ እና የአሜሪካ ሕዝብ የሃገሪቷ የፍትህ ሚኒስቴር የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑ የሚያበቃበትን ቀን ለማየት ይጓጓሉ ብለዋል።
በዲሞክራቶችና በዶናልድ ትራምፕ ተቃዋሚወች ዘንድ ግን ይሄው ዕውነት በአሜሪካ የፍትህ ስርዓት ውስጥ የተፈጠረ ታሪካዊ ጠባሳ እንደሆነ እየተነገረ ነው። የኒውዮርክ ግዛት የዲሞክራት እንደራሴ ዳን ጎልድማን፣ ዶናልድ ትራምፕ ከህግ በላይ የሆኑበት አሳፋሪ ክስተት እንደሆነ ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኋይት ሐውስ ሊገቡ ነው
ሌሎች ደግሞ የአሜሪካ ሕዝብ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተደረጉ መጠነ ሰፊ ምርመራወችን፣ የተከፈቱ በርካታ ክሶችና የተሰጡ የጥፋተኝነት ውሳኔወችን አይቶም፣ ሰምቶም፤ ይሁን ብሎ መርጧቸዋል ይላሉ። እናም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የፍርድ ቤትን ውሳኔ የገለበጠ፣ የሕዝብ ድምጽ፣ ብያኔውን ሰጥቷል ብለዋል። ከአምሳ ዓመታት በፊት ሪቻርድ ኒክሰን «ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም፤ ፕሬዝዳንትም ቢሆን» በሚለው መርኅ ሥስልጣናቸውን ለቅቀው ነበር። ዛሬ ያ መርኅ በዶናልድ ትራምፕ እና በደጋፊወቻቸው ተቀልብሶ ከ90 በላይ ክሶሽ ያለባቸውና ከ34 በላይ በሚሆኑ የክስ ጭብጦች ጥፋተኛ የተባሉት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ተመርጠው ወደ ኋይት ሐውስ ሊገቡ ነው።
ልዩ አቃቤ ሕጉ ጃክ ስሚዝም ሆነ ክሱን ውድቅ የማድረግ ጥያቄውን ያጸደቁት ዳኛ በክሶቹ ላይ ወድግራም ሆነ ወደቀኝ የውሳኔ ሐሳብ አልሰጡም። ይህም ማለት ከአራት ዓመታት በኋላ፣ የዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንትነት ሲያበቃ፣ ያለመከሰስ መብታቸውም ሲነሳ ከሳቸው ጋ እሰጣገባ የማድረግ አቅምና ፍላጎት ያለው አቃቤ ሕግ ከመጣ መልሶ ሊያነሳው ይችላል ማለት ነው። ይህ የመሆኑ እድል ግን እጅግ በጣም የመነመነ ነው።
የፌደራል ክሶቹ ይቁሙ እንጂ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በኩል የተጀመሩ የክስ ሂደቶች በዚህ ውሳኔ ውስጥ አልተካተቱም። ጃክ ስሚዝ፤ ዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን አድርገው ወደ ኋይት ሐውስ ከመግባታቸው በፊት የምርመራ ውጤታቸውን የያዘ ዘገባ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
አበበ ፈለቀ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሐይ ጫኔ