ዶ/ር አብይ በመጀመሪያ ንግግራቸው ይቅርታ ጠይቀዋል
ሰኞ፣ መጋቢት 24 2010አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተለያየ ጊዜ ህይወታቸው ለተቀጠፈ ወጣቶች፣ መስዋዕትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎች እና ፖለቲከኞች ይቅርታ ጠየቁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ መንግስት ጋር ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዛሬ ረፋዱ ላይ በተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመታቸው የፀደቀላቸው ዶ/ር አብይ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባሰሙት ንግግር በርካታ ጉዳዮችን ዳስሰዋል፡፡ “መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍትህ እና የይቅርታ ጊዜ ነው” ያሉት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ራሳቸውም በተለያዩ ጊዜያት ህይወታቸውን ላጡ እና መስዋዕትነት ለከፈሉ ኢትዮጵያውያን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
“በዜጎቻችን ሕይወት እና በግልም በጋራም ንብረቶቻችን ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሷል። ይኸንን ሁላችንም ማስቀረት እንችል እና ይገባንም ነበር በተለያየ ጊዜ መስዋዕትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎች ፖለቲከኞች በቅጡ ሳይቧርቁ ሕይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ለስነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ"
“አዲሱ የዲሞክራሲ ስርዓት እውን አንዲሆን አዕላፍ ተሰውተዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ታዳጊውን ዲሞክራሲያችንን ለማዳበር ግን ተጨማሪ የህይወትም ሆነ የአካል መስዋዕትነት አያስፈልግንም” ሲሉ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ባሰስተላለፉት መልዕክት ፓርቲዎች “በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ” መንግስት እንደሚሻ ጠቁመዋል፡፡ “የተመቻቸ እና ፍትሃዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር በመንግስት በኩል ጽኑ ፍላጎት አለ” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ ባነሱበት የንግግራቸው ክፍል ሀገሪቱ በተለይም “ከጎረቤት ሀገራት ጋር በችግርም፣ በተድላም” አብራ እንደምትቆም ጠቁመዋል፡፡ በድንበር ይገባኛል ከኢትዮጵያ ጋር ለምትወዛገበው ኤርትራ ያቀረቡት ጥሪም ከምክር ቤት አባላት ጭብጨባ አስለግሷቸዋል፡፡
ዶ/ር አብይ ከተወካዮች ምክር ቤት የበዓለ ሲመት በኋላ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በማምራት ከተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር የርክክብ እና የሽኝት ስነ ስርዓት በማከናወን ስራቸውን አሃዱ ብለዋል፡፡ ስነስርዓቱን በስፍራው ተገኝቶ የተከታተለው የአዲስ አበባው ወኪላችን ዮሐንስ ገብረ እግዚብሔር ዘገባ ልኮልናል።
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
ተስፋለም ወልደየስ
ኂሩት መለሰ