1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«ዶይቸ ቬለ ላይ የደረሰው ጥቃት ገለልተኛው ፕሬስ ላይ የተደቀነ መጠነ ሰፊ ሥጋት ነው» ተባለ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2018

ሒውማን ራይትስ ዎች፦ የዶይቸ ቬለ ሁለት ወኪሎች በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለ ሥልጣን ለዘለቄታው መታገዳቸውን አወገዘ ። ለ«ኢትዮጵያ መንግሥት» ጥሪ ያስተላለፈው ሒውማን ራይትስ ዎች፦ «በዶይቸ ቬለ ጋዜጠኞች ላይ የጣለውን እገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሳ፤ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚያደርሰውን ተጨማሪ ጥቃት እንዲያቆም» ሲልም ጥሪ አስተላልፏል ።

የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሒውማን ራይትስ ዎች መለያ
የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሒውማን ራይትስ ዎች መለያምስል፦ John MacDougall/AFP/Getty Images

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሒውማን ራይትስ ዎች፦ የዶይቸ ቬለ ሁለት ወኪሎች በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለ ሥልጣን ለዘለቄታው መታገዳቸውን አወገዘ ። ድርጅቱ፦ «ኢትዮጵያ ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ነጻነት ላይ ሌላ አሉታዊ ተግዳሮት» በሚል ዐቢይ ርእስ ባወጣው መግለጫው በንዑስ ርእሱ፦ «ዶይቸ ቬለ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ገለልተኛው ፕሬስ ላይ የተደቀነ መጠነ ሰፊ ሥጋት መሆኑን ያረጋግጣል» ብሏል።

«እነዚህን ጋዜጠኞች ማገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ለማንም የማይወግኑ ገለልተኛ እና ሂሳዊ ዘገባዎች ላይ ያለውን ባላንጣነት የሚያረጋግጥ ነው» ሲልም ተችቷል ። በሒውማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃው ክፍል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማውሲ ሴጉን ትናንት (ታኅሣሥ 6 ቀን፣ 2018 ዓ.ም) የወጣው መግለጫ፦ ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ  ውስጥ ለዓመታት በባለሥልጣናት ያላሰለሰ ክትትል፤ ፍርሐት ባጠላበት ድባብ ውስጥ እንደሚሠሩ አመልክቷል። «የመብቶች ጥሰቶችን ያጋለጡ አለያም መንግሥትን የሚያሒሱ ዘገባዎችን የሚያቀርቡ» ጋዜጠኞች ላይ «ተከታታይ ክትትል፣ እስር፣ እና ዘብጥያ መውረድ» እንደሚከተልም ሒውማን ራይትስ ዎች ዘርዝሯል። በዐሥራዎቹ የሚቆጠሩ ጋዜጠኞችም አገር ጥለው መሰደዳቸውን ድርጅቱ በመግለጫው አክሏል። ለ«ኢትዮጵያ መንግሥት» ጥሪ ያስተላለፈው ሒውማን ራይትስ ዎች፦ «በዶይቸ ቬለ ጋዜጠኞች ላይ የጣለውን እገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሳ፤ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚያደርሰውን ተጨማሪ ጥቃት እንዲያቆም» ሲልም ጥሪ አስተላልፏል ።

ሙሉ  የእንግሊዝኛ መግለጫውን ይህን ማገናኛ ጠቆም በማድረግ ማንበብ ይቻላል ።

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW