ዶ/ር አረጋዊ በርሔ ተሾሙ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 5 2013
ዶ/ር አረጋዊ በርሔ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። ዶ/ር አረጋዊ በጠቅላይ ሚንስትሩ የተሾሙት ትናንት ረቡዕ ጥቅምት 04 ቀን 2013 ዓ/ም ነው። በዚህም መሠረት ዶ/ር አረጋዊ በርሔ ቀደም ሲል ጽህፈት ቤቱን በዋና ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ የነበሩና በጡረታ የተሰናበቱትን ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴን ይተካሉ። ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ ከአራት ዓመታት በላይ ጽህፈት ቤቱን በዋና ዳይሬክተርነት የመሩ መሆናቸውን የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብረሃም ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። ሕዝባዊ ወያኔ ኣርነት ትግራይ (ሕወሓት) በቅርቡ በፌዴራል መንግሥት ውስጥ በኃላፊነት በማገልገል ላይ ለነበሩ የፓርቲው አባላት ጥሪ አድርጓል። ይህ ጥሪ ከተደረገላቸው ኃላፊዎች መካከል ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ አንዷ ነበሩ። ነገር ግን አቶ ኃይሉ እንደሚሉት ወ/ሮ ሮማን ኃላፊነቱን የለቀቁት በ2012 ዓ/ም በጡረታ ለመልቀቅ ባመለከቱት መሠረት ነው። እናም ጡረታቸው ተጠብቆ ጽሕፈት ቤቱ አሸኛኘት እንዳደረገላቸውም የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ኃይሉ አክለው ገልጸዋል። ዶይቸ ቬለ የወ/ሮ ሮማንን ሃሳብ ለማካተት በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ላይ ቢደውልም ስልካቸው ባለመሥራቱ አልተሳካም። አዲሱ ተሿሚ ዶ//ር አረጋዊ በርሔ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር /ትዴት/ ሊቀመንበር ናቸው ።
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሠ