1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመናዊትዋ፤ ለኢትዮጵያ በመስራት ማመስገን እፈልጋለሁ

ሐሙስ፣ ጥር 11 2015

ስራ በጀመርኩበት እድሜ ክልል ያሉ አዲሶቹን ትዉልዶች በመርዳትና በማገዝ የተደረገልኝን ነገር ሁሉ መልሼ መስጠት እፈልጋለሁ። መልሼ በመክፈል ማመስገን እፈልጋለሁ። ለብዙ ዓመታት ኢትዮጵያዉያን ሃገር ዉስጥ ያሉም ሆነ በዉጭ የሚኖሩ እዚህም ጀርመን ዉስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ያገኘሁትን ትልቅ ጉልበት ያለዉ አወንታዊ ድጋፍ መልሼ መስጠት እፈልጋለሁ።

Beate Wedekind
ምስል Privat

በጀርመን በተለይ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የተለያዩ የማኅበረሰብ ጉዳዩችን በማቅረብዋ ታዋቂ እና የተከበረች የፕሮግራም አዘጋጅ የዛሬዉ የባህል መድረክ እንግዳ ነች። ቤአተ ቬደኪንድ ለኢትዮጵያ ያላት ፍቅርን በተለያዩ የጀርመን ሚዲያዎች ላይ ቀርባ ቃለ ምልልስ በመስጠትዋ፤ ለኢትዮጵያ ያላት ፍቅር በጀርመናዉያን ዘንድ ይታወቃል። ቤአተ በጀርመን «ቡንት» የተባለ ታዋቂ እና ተነባቢ የሆነ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆና ለብዙ ዓመታት ሰርታለች። «ባንቢ» እና የ«ጎልደን ካሜራ» የተባሉ እና በጀርመን የታዋቂ ሰዎች ዓመታዊ የሽልማት መድረክን በዋና አዘጋጅነት በመምራትዋ ከፍተኛ እዉቅናን ያገኘች ጋዜጠኛም ነች። የ 71 ዓመትዋ ጀርመናዊት ቤአተ ቬደኪንድ በኢትዮጵያ ሰዎች ለሰዎች ከተባለዉ የግብረሰናይ ድርጅት ጋር ከ 45 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ዉስጥ ኖራ ሰርታለችም። ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍቅር እንዳላት የምትናገረዉ ጀርመናዊት አብዛኛዉን መኖርያዋን ኢትዮጵያ ዉስጥ ብታደርግም ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በኮሮና ተህዋሲ ስርጭት እና የዝዉዉር እገዳ ምክንያት እንደልቧ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና የያዘችዉን የስራ እቅድም መፈፀም አለመቻልዋን ነግራናለች። አሁን የኮሮና እገዳ በመነሳቱ ከዝያም በላይ የኢትዮጵያዉ የእርስ በርስ ጦርነት ቆሞ የሰላም ስምምነት ላይ በመደረሱ እፎይታን ፈጥሮላታል። ቤአተ ቬደኪንድ ለቃለ-ምልልስ በመቅረቧ መማመስገን ቃለምልልሳችን በጥያቄ ጀመርን።

ቤአተ ቬደኪንድ ፤ ከሰዎች ለሰዎች የግብረሰናይ ድርጅት መስራች ከካርልሃይንስ ቦም ጋር በኢትዮጵያምስል Privat

ቤአተ፤ በአዲሱ 2023 ዓመት በኢትዮጵያ ዉስጥ የጀመርሽዉን ፕሮጀክት እንደምትቀጥይ ነግረሽናል። አዲሱ ፕሮጀክትሽ በምን ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነዉ?  

«አዎ በዓለማችን የኮቪድ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት በነበሩት ዓመታት የጀመርኩት ፕሮግራም ነዉ። በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ዉጭ የሚገኙ ወጣት ኢትዮጵያዉያን የሥራ ፈጣሪዎችን እና ስራዎቻቸዉን ብሎም ንግዳቸዉን በመደገፍ እና ሥራ ፈጣሪዎቹን ወጣቶች የልምድ ልዉዉጥ እንዲያደርጉ እና ግባቸዉ ላይ እንዲደርሱ መደገፍ እፈልጋለሁ። ስለዚህም አዲሱ 2023 ዓመት ለዚህ ሥራ ትልቅ ጊዜ ነዉ ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ያበቃበት በመሆኑ ነዉ።  በሌላ በኩል በመንግሥት እና በትግራይ አማጽያን መካከል የሰላም ስምምነት በመደረሱ እና የሰላም ስምምነቱም ተግባራዊ እየተደረገ በመሆኑ ነዉ። በአዲሱ 2023 ዓመት ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለምንም ፖለቲካዊ ችግር ለሥራ የምንነሳበት ለወደፊት ስራችን ተስፋ የሰነቅንበት ጊዜ ነዉ።»

በኢትዮጵያ አዲስ የጀመርሽዉ ወይም የምትጀምሪዉ ፕሮግራም በማን ነዉ የሚደገፈዉ ቤአተ?

«ይህ ትልቅ ፕሮጀክት በመጀመርያ ደረጃ በራሴ ትልቅ ፍላጎት እና ተነሳሽነት የምሰራዉ ስራ ነዉ። በሌላ በኩል ይህን ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ የጀርመን ኢንዱስትሪዎች ከሁሉም በላይ ሴቶችን የሚደግፉ ሴቶችን ወደ ከፍታ ቦታ እንዲመጡ በስራቸዉ እንዲበረቱ ከሚፈልጉ የጀርመን ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ አገኛለሁ። እኔም ብሆን እንደ አንድ ጋዜጠኛ የራሴ ድርጅት አለኝ፤ በዚህም ድጋፍ የማደርግ አቅሙ አለኝ። ሴቶችን መደገፍ እወዳለሁ። እኔም እራሴ አብዛኛዉን ወንዶች ካሉበት የሥራ መድረክ በጥረት በድጋፍ እዚህ እንዴት እንደደረስኩ ስለማዉቅ፤ ለሥራ የሚጥሩ ሴቶች መደገፍ እንዳለባቸዉ አምናለሁ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚኖሩ ድርጅት የመሰረቱ ሴቶች የወደፊት ኑሮዋቸዉን ቀለል ለማድረግ ለመርዳት ትልቅ ፍላጎት አድሮብኛል።»   

ምስል Beate Wedekind

ቤአተ ለኢትዮጵያ ትልቅ ፍቅር እንዳለሽ ሃገሪቱንም ለረጅም ዓመታት እንደምታዉቂ ነግረሽናል።  ኢትዮጵያ ዉስጥም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ በጣም ብዙ ጓደኞች የስራ ባልደረቦች እንዳሉሽ እንዲሁ። ግን አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ ለመጀመር ያሰብሽዉን ስራ ከማን ጋር ነዉ ለመስራ ያቀድሽዉ?   

«ይህን ስራ ለመስራት ያቀድኩት ከወጣቶች ጋር ሳይሆን፤ አዳዲስ ድርጅትን ከሚፈጥሩ በስራ ታዳጊ ከሆኑ ኢትዮጵያዉያን ጋር ነዉ። አዲስ የስራ እቅድ እና የስራ ሃሳብ ያላቸዉ ኢትዮጵያዉያን የያዙትን እቅድ ይዘዉ ጠንክረዉ እንዲወጡ እገዛ ነዉ የምሰጠዉ።  ይህን ስራዬን የጀመርኩት ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ የሥነ-የህንፃና ከተማ ፕላን ተቋም የመገናኛ ዘዴዎች ባለሙያ ሆኜ በተጋበዝኩበት ወቅት ነበር። የተጋበዝኩበት ጉዳይ ደግሞ ኩባንያን ወይም ድርጅትን ለመመስረት የሚያስችል የመጀመሪያ ሃሳቦችን በማሰባሰብ ላይ ያተኮረ ነበር። በዚያ ወቅት የዩንቨርስቲ አስተማሪ እና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩት እና አሁን በጀርመን በርሊን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞንን አግንቻቸዉ ነበር። በዝያን ግዜ ከተዋወክዋቸዉ ሰዎች መካከል በአሁኑ ወቅት «ጋርደን ኦፍ ኮፊ» በተባለዉ ቡናዋ እና  «ሶል ሬብልስ» በሚለው የጫማ ምርቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኝነትን ያተረፈችው ቤተልሄም ጥላሁን አለሙ ትገኝበታለች። ከቤተልሄም ሌላ በዚያን ጊዜ ተማሪ የነበሩ እና በአሁኑ ወቅት የንግድ ድርጅቶችን ያቋቋሙም ይገኙበታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቀስ በቀስ አውታረ መረብ ገንብቼ ስለስራዎቼ  በ TEDxAddis በተባለዉ አገናኝ አዉታረ መረብ ስለ አዲሲቲዋ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ብዙ ስራን ሰርቻለሁ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ከጀርመኑ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር GIZ ጋር ሆኜም የጥናት ስልጠናን አከናዉኛለሁ። በኢትዮጵያ እና በጀርመን መካከል ተመሳሳይ አይነት ስራ ያላቸዉ እንዲገናኙ አውታረ መረብ እንዲዘረጉ አድርጌያለሁ። ዋናዉ ነገር በኢትዮጵያ ውስጥ አዳዲስ ብቃት ያላቸው ሥራዎችን መፍጠር እና በሁሉም የስራ ሂደቶች ላይ ዘላቂነት እንዲኖራቸዉ ብሎም ማህበራዊ ኃላፊነት እና እኩልነትን ግንባር ቀደም ያደረጉ መሆናቸው ሁሌም አስፈላጊ መሆኑን አሳያለሁ። እንደ ጋዜጠኛ፣ ጥያቄዎችን መጠየቅ እና መልሶችን መፈለግ ዋናዉ ተግባሪ ነዉ። ከሰዎች ጋር መነጋገር፤ ወደ እነርሱ መቅረብ፤ አስተማማኝ ግንኙነት ማድረግ ብቸኛው አስፈላጊዉ መንገድ መሆኑ ዋናዉ መርሆዬ ነዉ። ከቀድሞዉ የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር ከዶክተር ጌርድ ሙለር ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ተጨመሪ እድልም አግንቼ ነበር። ይህ ከኢትዮጵያ መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረትም አስችሎኛል። እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር ከ 2018 ዓ.ም ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ መንግስትን ተዋዉቄያለሁ።  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድንም ቢሆን በግል ለመተዋወቅ እንድሉን አግንቻለሁ። ባለፉት ሦስት ዓመታት በኮሮና ወረርሽኝ፤  ከዚህም በተጨማሪ በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት፤ ሌሎች ነገሮች በሙሉ ወደኋላ እንዲገፉ መደረጉ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነበር ። በኢትዮጵያ ስለ ወጣቱ ትውልድ ስኬት ማንም አያወራም ነበር። የሚያወራው ሁሉ ስለ ጦርነት ብቻ ነበር። ኢትዮጵያ ዉስጥ ስለተፈፀሙ አዎንታዊ ነገሮች ሁሉ ችላ ተብሎ ነበር።»

ቤአተ ቬደኪንድ ከቀድሞዉ የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር ከዶክተር ጌርድ ሙለር እና ከጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ጋርምስል Privat

ቤአተ፣ አዲስ ድርጅት ያቋቋሙ ያልሻቸዉ ኢትዮጵያዉያን በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ብቻ ናቸዉ ?

«ከአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ከተሞች እና በገጠር አካባቢ የሚኖሩም ይገኙበታል። ለበርካታ ዓመታት ካርል ሃይንስ በም፤ በመሰረቱት ሰዎች ለሰዎች በተባለዉ ግብረሰናይ ድርጅት ዉስጥ ስሰራ ሃገሪቱን በደንብ አዉቂያታለሁ በጣም ብዙ ሰዎች እና ባልንጀሮችም አፍርቻለሁ። ከነዚህ ሰዎች መካከል፤ በድሪደዋ በሃረር ብሎም በባህርዳርም ትንንሽ ድርጅቶችን አቋቁመዉ የሚኖሩ ሰዎች አዉቃለሁ። በገጠር አካባቢዎችም በጤናው ዘርፍ በኮምፒዩተር ባለሞያነት ወይም በግብርና ስራ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ዙጎችም አሉ። በከተሞች የሚኖሩ  ወጣቶች በአብዛኛዉ በሥነ-ጥበብ ሞያ፤ በዘመናዊ ልብስ ቅድ ሞያ፤ አልያም በኮምፒዉተር ባለሞያነት እየሰሩ ያሉ ናቸዉ። እና እንደ ቦታዉ እና እንደሁኔታዉ ይለያያል።»  

እነዚህ አብረሽ ልትሰርያቸዉ ያቀድሻቸዉ ኢትዮጵያዉያን አሁን ለመምጣት እቅድ እንደያዝሽ ያዉቃሉ?

«አዎ ያዉቃሉ እየጠበቁኝም ነዉ። እኔ ትንሽ ቀስ ያሉኩት በእርግጥ በኮሮና ወረርሽ የዝዉዉር እገዳ  ምክንያት ነዉ።  ወረርሽኙ በጎርጎረሳዉያኑ በ 2020 ጀመረ  በ2021 እና በ 2022 ም፤ ለአጭር ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዤ ነበር። በዋናነት የአማካሪነት ስራ እና አዉደ ጥናቶችን፤ አዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ አካሂጄ ነዉ የተመለስኩት። እና ይህን ሁሉ በ 2022 ዓመት ማድረግ የፈለግኩትን ነገር ነዉ፤ አሁን አዲስ በያዝነዉ 2023 ዓመት ለመስራት ያቀድኩት። በአዲሱ ስራ ተግዳሮት ብሎም ለዉጥ የምናየዉ የንግድ ኢንዱስትሪዎችን ከአዳዲስ የትብብር አጋሮች፣ የማዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ማለትም - ኢንቬስተሮች እና ከአዳዲስ ሸማቾች ጋር የሚያገናኝ፤ የልምድ ልውውጥ፤ የኢንዱስትሪ መገናኛ መድረክ ይሆናል ማለት ነዉ።»

በአሁኑ ጊዜ ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህን ሁሉ ነገር ለመስራት የሃገሪቱ የፀጥታ ጉዳይ ትንሽ ስጋት አይዝሽም ?

ቤአተ ቬደኪንድ በኢትዮጵያምስል Privat

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በጀርመናዊትዋ እይታ«በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ኢትዮጵያን የማዉቃት ዛሬ አይደለም። እድሜዬን በሙሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰርቻለሁ ኖርያለሁም። ከ 45 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዤ በጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት ዉስጥ አገልግያለሁ። ከዝያም በመለጠቅ ሰዎች ለሰዎች በተሰኘዉ ካርልሃይንዝ ቦህም በመሰረተዉ የሰብዓዊ ርዳታ ድርጅት ዉስጥ አገልግያለሁ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ ከማርክሲስቱ ስርዓት ጀምሮ አውቀዋለሁ። ከመለስ ዜናዊ  እስከ ኃይለማርያም ከዝያም እስከ ዴሞክራቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ድረስ አዉቀዋለሁ፤ አይቸዋለሁም።  እና ልነግርሽ የምፈልገዉ የሚፈራ ሰዉ ወደ ኢትዮጵያ መሄድ አይችልም። እኔ ኢትዮጵያ አታስፈራኝም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደባለፉት ሁለት ዓመታት ከባድ ቀዉስ አይሁን እንጂ ሁልግዜም ቢሆን አንዳንድ ችግር ጠፍቶ አያዉቅም። ኢትዮጵያውያን ግን የመለወጥ ፍላጎት እና ፈቃድ ብሎም እምቅ ጉልበት አላቸው። ግን ይህን እምቅ ጉልበት የያዙ ዜጎች ምንም ነገር ሳይኖራቸዉ ለወደፊት ጥሩ ህይወት የሆነ ነገር ይሰራሉ ብዬ መናገር አልችልም። በሌላ በኩል ማንም በቀዉስ ዉስጥ መኖር አይፈልግም። ሙስናንም ሆነ ጦርነትን የሚፈልግ ሰው የለም። ሁሉም ሰው ሰላምና ብልጽግና ይፈልጋል። አሁን ኢትዮጵያ የምትፈልገዉ ሰላም እና ብልፅግናን ብቻ ነዉ። በሀገሪቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ቢኖርም በኢትዮጵያም ሆነ በዲያስፖራው የሚኖሩ የማዉቃቸዉ በርካታ እጅግ ጥሩ ኢትዮጵያዉያን በሃገሪቱ ነጻነት፣ አንድነትና ብልፅግና እንደሚሰፍን ያምናሉ»

ኢትዮጵያን እንዴት ትገልጫታለሽ? ኢትዮጵያ ላንቺ ምንድን ናት?

«ኢትዮጵያ ለኔ ከእ.ኤ.አ በ1976 ጀምሮ አዳዲስ እድሎችን ማፈላለግ የጀመርኩባት እና የስራ ህይወቴ መጀመርያ ናት። አሁን ደግሞ 71 ዓመት እድሜዬ፤ አድማሴን በማስፋት እድል የሰጠችኝ ሀገር ላይ መስራት ብቻ ነው የምፈልገው። ያኔ ስራ በጀመርኩበት እድሜ ክልል ላይ ያሉትን አዲስ ትዉልዶች በመርዳት እና በማገዝ የተደረገልኝን ነገር ሁሉ መልሼ መስጠት እፈልጋለሁ።  መልሼ በመክፈል ማመስገን እፈልጋለሁ። ለብዙ ዓመታት ኢትዮጵያዉያን ሃገር ዉስጥ ያሉም ሆነ በዉጭ የሚኖሩ እዚህም ጀርመን ዉስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ያገኘሁትን ትልቅ ጉልበት ያለዉ አወንታዊ ድጋፍ መልሼ መስጠት እፈልጋለሁ። ለእኔ ኢትዮጵያ – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን አናሌና ባርቦክ በአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ወቅት እንዳረጋገጡት – ኢትዮጵያ ለኛ አጋር ሀገር ናት። ምክንያቱም በሃገሪቱ የሚገኘዉ ወጣቱ ትዉልድ ለአገሩ፣ ለማህበረሰቡ፣ ለቤተሰቡ እና ለራሱ ለልጁ እና ለልጅ ልጁ መልካም፣ ህያው የሆነ የወደፊት ጠንካራ ነገርን ለመቅረጽ አቅም እንዳለሁ አውቃለሁ»

በኢትዮጵያ ያለዉን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ትገመግሚዋለሽ?

ቤአተ ቬደኪንድ በኢትዮጵያምስል Privat

«ስለዚህ ነገር ሲነሳ  አንዳንዴ ሰዎች እኔን እንደ የዋህ እንደ ሞኝ አድርገዉ ይገምቱኛል። ይሁን እንጂ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ኢትዮጵያን የማዉቃት ቢያንስ ለ 45 ዓመታት ነዉ። የሃገሪቱን የፖለቲካ ስርዓቶችን ጠንቅቄ አዉቃለሁ። ህዝቡን አዉቀዋለሁ። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ብዙ ከእውነት የራቁ መረጃዎች ይወጣሉ።  ስለኢትዮጵያ እጅግ ብሩህ የሆነ አዎንታዊ አመለካከት ነዉ ያለኝ። የእኔ የህይወት ፍልስፍና ደግሞ ስለነገሩ ማዉራት ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን በተጨባጭ መፈጸም ነው ። ለዚህም ይህን አላማየን ለማሳካት አሁን ወደ ኢትዮጵያ እሄዳለሁ።»

ቤአተ ኢትዮጵያን እንዴት ትገልጫታላሽ፤ኢትዮጵያ ለአንቺ ምንድን ናት?

«ኢትዮጵያ ለኔ ከጎርጎረሳዉያኑ 1976 ጀምሮ አዳዲስ እድሎችን ማፈላለግ የጀመርኩባት እና የስራ ህይወቴ መጀመርያ ናት። አሁን ደግሞ 71 ዓመት እድሜዬ፤ አድማሴን በማስፋት እድል የሰጠችኝ ሀገር ላይ መስራት ብቻ ነው የምፈልገው። ያኔ ስራ በጀመርኩበት እድሜ ክልል፤ አሁን ያሉትን አዲስ ትዉልዶች በመርዳት እና በማገዝ የተደረገልኝን ነገር ሁሉ መልሼ መስጠት እፈልጋለሁ። መልሼ በመክፈል ማመስገን እፈልጋለሁ። ለብዙ ዓመታት ኢትዮጵያዉያን ሃገር ዉስጥ ያሉም ሆነ በዉጭ የሚኖሩ እዚህም ጀርመን ዉስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ያገኘሁትን ትልቅ ጉልበት ያለዉ አወንታዊ ድጋፍ መልሼ መስጠት እፈልጋለሁ። ለእኔ ኢትዮጵያ – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን አናሌና ባርቦክ በአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ወቅት እንዳረጋገጡት – ኢትዮጵያ አጋር ሀገር ናት። ምክንያቱም በሃገሪቱ የሚገኘዉ ወጣቱ ትዉልድ ለአገሩ፣ ለማህበረሰቡ፣ ለቤተሰቡ እና ለራሱ ለልጁ እና ለልጅ ልጁ መልካም፣ ህያው የሆነ የወደፊት ጠንካራ ነገርን ለመቅረጽ አቅም እንዳለሁ አውቃለሁ»

ቤአተ ቬደኪንድምስል Beate Wedekind

ቤአተ ምናልባት ያልጠየኩሽ ግን መናገር የምትፈልጊዉ ነገር ካለ በመጨረሻ እድሉን ልስጥሽ። 

«ኢትዮጵያ ማለት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ እና ከኢትዮጵያ ዉጭ የሚኖሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን የድርጅት ባለቤቶችን ማገናኘት እፈልጋለሁ። ለምሳሌ በጀርመን ዉስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ባለድርጅቶችን ሃገር ዉስጥ ከሚገኙ ወጣት ባለድርጅቶችን በሥራ ማገናኘት ማለት ነዉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ የድርጅት ባለቤቶች ስኬታቸዉ እና ትኩረታቸዉ ሃገር ዉስጥ ብቻ ሳይሆን ሥራቸዉ ድንበር ተሻጋሪ እንዲሆን እና ስኬታማ እንዲሆኑ ማስቻል ነዉ። ይህ እንዲሳካ ግን እንደሚታወቀዉ ወጣት ባለድርጅቶቹ ፣ ኢንቨስትመንት «መዋዕለ ንዋይ የሚያፈስ» ያስፈልጋቸዋል፣ የስራ ተጓዳኞች ያስፈልጋቸዋል፣ የሚያገናኛቸዉ አገናኝ ያስፈልጋቸዋል። እና ይህን የምሰራላቸዉ እኔ እሆናለሁ ማለት ነዉ።»

ቤአተ ቤደኪንድ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዛ ሥራዋን ትጀምራለች። እንዲሳካላት  በመመኘት ቃለ ምልልሱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW