1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመንን በመገንባት አሻራቸውን ያኖሩ ሴቶች

ማክሰኞ፣ ሰኔ 14 2014

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በጀርመን ሴቶች በኢኮኖሚና በፖለቲካ የነበራቸው አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልነበር ድርሳናት ያመላክታሉ። ሴቶች 3K ማለትም Kinder ሕጻናትን ማሳደግ፣ Küche ኩሽና Kirche ማለትም ቤተክርስትያን በነዚህ ይጠመዱ ነበር።

Trümmerfrauen Denkmal Berlin Deutschland Zweiter Weltkrieg
ምስል picture-alliance/dpa/Matthias Hiekel

ጀርመንን በመገንባት አሻራቸውን ያኖሩ ሴቶች

This browser does not support the audio element.

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጀርመን ከተሞች ከፍተኛ  ውድመት ደርሶባቸዋል። ወንዶች በጦርነቱ አልቀዋል፣ የተረፉትም በየካምፑ ታጉረዋል። በዚህ ጊዜ የከተሞቹ ፍርስራሽ የማጽዳትና መልሶ የመገንባት ሥራ በጀርመን ሴቶች ጫንቃ ላይ ወደቀ። በዛሬ አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን  የአሁኗን ጀርመን በመገንባት አሻራቸውን ያኖሩት የጀርመን ሴቶች ወይም Trümmerfrau መጠነኛ ቅኝት እናደርጋለን።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በጀርመን ሴቶች በኢኮኖሚና በፖለቲካ የነበራቸው አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልነበር ድርሳናት ያመላክታሉ። ሴቶች 3K ማለትም  Kinder ሕጻናትን ማሳደግ፣  Küche  ኩሽና Kirche ማለትም ቤተክርስትያን። በነዚህ ሦስቱ ጉዳዮች ላይ እንዲጠመዱ የሚያድርግ ማሕበራራዊ መሰረትና ሥርአት ነበር።
በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የተባበሩት ሐይሎች በወሰዱት የማጥቃት እርምጃ በጀርመን በ62 ከተሞች ውስጥ ከሚገኙት አሥራ ስድስት ሚልዮን ቤቶች  3.6 ሚልዮኑ   የወደሙ ሲሆን  ሁሉም የትምህርት ቤት ሕንፃዎች ፣ አርባ በመቶ የሚሆኑት የመሠረተ ልማት አውታሮች እንዲሁም በርካታ ፋብሪካዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል አሊያም ወድመዋል ። ግምታዊ አኃዝ እንደሚያሳየው 500 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚያክል ፍርስራሽ በተለያዩ ከተሞች ተከምሮባቸው ነበረ። በዚህም ውድመት 7.5 ሚሊዮን ሰዎች ቤት አልባ ሆነዋል።
 ከተሞቹን አጽድቶ መልሶ ለመገንባት በወቅቱ የነበሩ ወንዶች በአባዛኛው በጦርነቱ በመገደላቸዉ፣ በመቁሰላቸዉ ወይም በየካምፖቹ በመታሰራቸዉ የሰራተኛ ኃይል አልነበረም። በመሆኑም ይህ ተግባር በሴቶች ጫንቃ ላይ ሊወድቅ ግድ ሆነ።
ዶክተር ልኡል አስፋወሰን አስራተ የታሪክ ሙሁርና ተመራማሪ እንዲሁም በርካታ ታሪካዊ መጻህፍት በመጻፍ ይታወቃሉ። በነዚህ የጀርመን ሴቶች ጉዳይ ካነጋገርናቸዉ አንዱ ናቸው።
ከ1945 እስከ 1946 ባለው ጊዜ የሕብረቱ ሐይሎች ከ15 እስከ 50 ዓመት የሆናቸውን የጀርመን ሴቶች የሕንጻ ፍርስራሽ በማጽዳት እንዲሳተፉ አዘዙ። በመሆኑም በቀን ከ20 እስከ 30 ደቂቃ እረፍት በማድረግ ለ9 ሰአታት የምግብ ራሽን እየተከፈላቸው አስቸጋሪውን የጉልበት ሥራ ይሰሩ እንደነበር ድርሳናት ያመላክታሉ።
ዶክተር ቮልበርት ስሚት የታሪክ ሙሁርና ተመራማሪ ሲሆኑ በኢትዮጵያ የተለያዩ ታሪኮች ላይ ምርምር በማድረግና በዩነጸርስቲዎች በማስተማር ይታወቃሉ። ያኔ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልጹታል።
<<እንደምታቀው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ቦኋላ   በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ ሞቷል። በተለይም ወንዶች ከወንዶችም ወጣት ወንዶች በየግንባሩ ሞቷል።  ይህ ብቻ አደለም በሺዎችና በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ወንዶች በየማጎሪያ ጣብያዎች ታጉረው አልቋል።  ይህ ማለት በአገሪቱ የኢኮነሚ ግንባታ፣ ፖለቲካዊ አመራር ቁልፍ ሚና ይጫወቱ የነበሩ ወንዶች ናቸው ያለቁት።  በመሆኑም የፈረሰችው ጀርመን የመገንባቱ ሥራ በሴቶች ጫንቃ ላይ አርፏል።
በርሊንና ሃምቡርግን የመሳሰሉ ትልልቅ ከተሞች ሳይቀሩ በነበረው የቦንብ ውርጅብኝ ወድመዋል። በመሆኑም በወትቱ የነበሩ ሴቶች መደበኛውንና የተለያዩ የሥራ ዘርፎችን  ሃላፊነት እንዲሸከሙ ሆኗል።>>
ልጅ በማሳደግ፣ ቤተክርስትያንና ኩሽና ተወስነው የነበሩት ሴቶች በሁሉም የግንባታ ዘርፎች በተለይም የፈረሱ ሕንጻዎችን በማጽዳትና በመገንባት ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው የታሪክ ድርሳናት ከትበውታል። በዚህም ለወንዶች ተወስነው የነበሩ ሥራዎችን በሙሉ ሴቶች የመስራት ብቃታቸው ያሳዩበት አጋጣሚ እንደሆነላቸው የታሪክ ሙሁርና ተመራማሪ ዶክተር ልዑል አስፋወሰን አስራተ ይናገራሉ።
አካፋ፣ዶማ፣ በእጅ የሚገፉ ጋሪዎች በወቅቱ የጀርመን ሴቶች ወይም ትሩመርፍራው ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቀላል መሳሪያዎች ናቸው። በተለይም ከ10 እስከ 20 እንደየአስፈላጊነቱ ከዛም በላይ ቁጥር ተደራጅተው ሰንሰለታዊ ረድፍ በመፍጠር ፍርስራሾችንና ለግንባታ የሚያስፈልጉ ጡቦችን እየተቀባበሉ መስራት እለታዊ ትእይንት ነበረ።ዶክተር ቮልበርት ስሚት 
<<የፈራረሱ ቤቶችን በማጽዳትና በመገንባት በጉልህ የሚታዩት እነዚሁ ሴቶች ነበሩ። የፈራረሱ ቤቶች   ለማጽዳትና ለሚገነቡ ሕንጻዎች የሚያስፈልጉ ግብአቶች ለማቅረብ መስመር ሰርተው እየተቀባበሉ  ከፍተኛ አስተወጽኦ አድርገዋል። በነገራችን ላይ የተጎዱ የሕንጻ መሳሪያዎች መልሰው ለግንባታና ጥገና ስራ እንዲውሉ አድርገዋል። 
ይህ ለሁለት ሦስት አመታት ከዛም በላይ የዘለቀ ስራ ነበር። የውጭ ወታደሮችና በወቅቱ በውጭ ሃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩ አካባቢያዊ መስተዳድሮች  በሚሰጧቸው ትንሽ ጉርሻና የምግብ ድጋፍ በተላያዩ የግንባታ ስራዎች ተሳትፏል።   የዚህ ሥራቸው ውጤትም  ከተሞቻቸውን መገንባት ችለዋል፣ ሕብረተሰባቸውን መገንባት ችለዋል። 
በጀርመን እነዚህን ሴቶችን ለመዘከር በተለያዩ ከተሞች መዶሻ ወይም አካፋ የጨበጡ ሴቶች አልያም በጥንካሬያቸው የሚታወቁ እንስሳት ምስል ተቀርጾ ሐውልት ቁሞላቸዋል። የተለያዩ ተቋማት ስያሜዎች፣ የሽልማት መድረኮች በስማቸው ይጠራሉ፣ ሕዝባዊ መድረኮች ላይም እየተወደሱ ስማቸው ይወሳል ሲሉ ዶክተር ልዑል አስፋወሰን አስራተ አክሏል።
ጀርመንን በመገንባት አሻራቸውን ስላኖሩ የጀርመን ሴቶች መጠነኛ ዳሰሳ ያደረግንበትን የዛሬውን አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችንን በዚሁ ፈጸምን። ማብራሪያ በመስጠት ለተባበሩን የታሪክ ሙራንና ተመራማሪዎች ዶክተር ልኡል አስፋወሰን አስራተንና ዶክተር ዎልበርት ስሚትን እናመሰግናለን።

ምስል Landesdenkmalamt Berlin
ምስል Fred Ramage/Keystone Features/Hulton Archive/Getty Images
ምስል picture-alliance/dpa
ምስል Getty Images/Fred Ramage/Keystone

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር 

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW