1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ከአፍሪቃ የተዘረፉ ቅርሶችን ልትመልስ ነው

ቅዳሜ፣ ሰኔ 25 2014

የጀርመን ቤተ መዘክሮች እና የፖለቲካ አመራሮች፣ የቤኒን ነሐሶች ለባለቤቶቻቸው እንዲተላለፉ የሚያስችሉ ተጨባጭ ስምምነቶችን ወደ ጎን ሲገፉ ቆይተዋል። ሆኖም ይህ የጀርመን አቋም ከጎርጎሮሳዊው 2021 ወዲህ ተቀይሯል። ቅርሶቹ ከሚገኝኙባቸው 20 የጀርመን ቤተ መዘክሮች ውስጥ አብዛኛዎቹ ያሉባቸው አምስቱ ቅርሶቹን ለማስረከብ አቅደዋል።

DW Video-Still | Benin-Bronzen | Rautenstrauch-Joest-Museum
ምስል Benjamin Bischof/DW

ጀርመን ከአፍሪቃ የተዘረፉ ቅርሶችን ልትመልስ ነው

This browser does not support the audio element.

ጀርመን በተለያዩ ቤተ መዘክሮቿ የሚገኙ፣በቅኝ ግዛት ዘመን ከአፍሪቃ ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶችን ለመመለስ ተስማምታለች። ከመካከላቸው ንብረትነታቸው የናይጀሪያ የሆነ ከ1ሺህ በላይ ከነሐስ የተሰሩ የቤኒን ቅርሶች ይገኙበታል። የጀርመን መንግሥት ወደ 1100 የሚጠጉ የቤኒን ነሐሶችን ለመመለስ በዚህ ሳምንት በቀጥታ ከናይጀሪያ መንግሥት ጋር ተስማምቷል። እነዚህ የያኔው የቤኒን ንጉሣዊ ስርዓት ቤተ መንግሥት፣ ቅርጻ ቅርጾች የተዘረፉት በቅኝ ግዛት ዘመን ነበር ። አካባቢው የአሁኑ ደቡብ ምዕራብ ናይጀሪያ ነው።ጀርመን ውስጥ ባሉ ሀያ ቤተ መዘክሮች ውስጥ ከሚገኙት የቤኒን ነሐሶች  አብዛኛዎቹ የብሪታንያ ኃይሎች የዛሬ 125 ዓመት የቤኒን ከተማን ይዘው ባቃጠሉና በዘረፉበት ወቅት ነው የተወሰዱት ።ቤተ መንግሥቱንም በእሳት አጋይተውታል። ናይጀሪያ ውስጥ የነበረችው የቤኒን ከተማም ሙሉ በሙሉ ወድማለች ማለት ይቻላል። ከተዘረፉት ቅርሶች አብዛኛዎቹ በሀያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ለንደን ውስጥ ለጨረታ በቀረቡበት ወቅት  ጀርመን ብዙ ቅርሶችን ከወሰዱት ውስጥ ሁለተኛውን ደረጃ ትይዛለች። የቀድሞው የቤኒን ንጉሳዊ መንግሥት ከ100 ዓመት በፊት ቅርሶቹ እንዲመለሱለት ቢጠይቅም አልተሳካለትም።በ1970 ዎቹ ደግሞ አፍሪቃውያን ምሁራን ጥያቄውን እንደገና ቢያቀርቡም አውሮጳውያን ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው አልፈውታል።ይሁንና ዋጋቸው ሊተመን የማይችለውን እነዚህን ቅርሶች ለባለቤታቸው ለናይጀሪያ ለመመለስ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ የጀርመን የባህልና የመገናኛ ብዘሀን ኮሚሽን ኮሚሽነር ክላውድያ ሮት የናይጀሪያ የባህል ሚኒስትር ላይ መሐመድና የናይጀሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ዙባይሮ ዳዳ  ትናንት በርሊን ውስጥ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ከፊርማው በኋላም ሁለት ከነሐስ የተሰሩ በርሊን ቤተ መዘክር የነበሩ ቅርጻ ቅርጾች ለናይጀሪያ በቀጥታ ተሰጥተዋል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ከፊርማው በኋላ ባሰሙት ንግግር እነዚህ ትናንት ለናይጀሪያ የተሰጡት  ከአንድ ሺህ በላይ ከሚሆኑት ጀርመን ከሚገኙት የቤኒን ንጉሳዊ ስርዓት ቅርሶች የመጀመሪያዎቹ መሆናቸውን ገልጸው እነዚህ የሆኑት ከነሐስ የተሰሩ ቅርሶች የናይጀሪያ ንብረቶች መወሰዳቸውንም ሆነ ከ120 ዓመት በላይ ጀርመን መቆየታቸውንም ስህተት ብለውታል። የትናንቱን ስምምነት ደግሞ ታሪካዊ በማለት አወድሰውታል።
«ዛሬ ታሪካዊ ስምምነት ላይ ስለደረስን እለቱን የምናከብርበት ምክንያት አለን።እነዚህ ቅርሶች እጹብ ድንቅ ብቻ አይደሉም፤ከአፍሪቃ የተከበሩ ታላላቅ ሀብቶች ጥቂቶቹ ናቸው።የቅኝ ግዛት ጥቃት ታሪክንም የሚነግሩን ናቸው።»
የሰነዱ መፈረም በጀርመን ቤተ መዘክሮች ውስጥ የሚገኙትን የቤኒን ነሐሶች ስብስብ ወዲያውኑ የናይጀሪያ ንብረት ያደርጋቸዋል። ለዚሁ ጉዳይ ጀርመን የመጡት የናይጀሪያ ቤተ መዘክሮችና ጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች ብሔራዊ ኮሚሽን ሃላፊ አባ ኢሳ ቲጃኒ ናይጀሪያና ጀርመን በፊርማ ያጸደቁት ይህ ስምምነት 1130 የሚሆኑ የቤኒን ቅርሳ ቅርሶች ለባለቤታቸው ለናይጀሪያ የመመለሳቸው ይፋ ማረጋገጫ መሆኑን ተናግረዋል። እርሳቸውም ወቅቱንም ታሪካዊ ብለውታል። 
«ይህ ለኛ ታሪካዊ ወቅት ነው፤ለኛ ብቻ ሳይሆን ለሁለቱም ሀገራት።»
የቤኒን ነሐሶች የሚባሉት ቅርጻ ቅርጾች በሙሉ ከነሐስ የተሰሩ አይደሉም።ከመካከላቸው ከመዳብና ዚንክ ቅይጥ ወይም ናስ ፣ከዝሆን ጥርስ አለያም ከእንጨት የተሰሩም ይገኙባቸዋል። የጀርመን ቤተ መዘክሮች እና የፖለቲካ አመራሮች፣ እነዚህ ቅርሶች ለባለቤቶቻቸው እንዲተላለፉ ወይም ካሳ ለመስጠት ተጨባጭ ስምምነቶችን ወደ ጎን ሲገፉ ቆይተዋል። ሆኖም ይህ የጀርመን አቋም  ከጎርጎሮሳዊው 2021 ወዲህ ተቀይሯል። የጀርመንና የናይጀሪያ መንግሥትና ቤተ መዘክሮች ተወካዮች ባለፈው ዓመት ነበር ቅርሶቹን ለባለቤቶቹ የመስጠት ውሳኔ ላይ መደረሱን ያሳወቁት።ቅርሶቹም ጀርመን በሚገኙ 20 ቤተ መዘክሮች ውስጥ ነው ያሉት።እስካሁን ባለው መረጃ ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ የሚገኙባቸው 5 ቤተ መዘክሮች ቅርሶቹን ለማስረከብ አቅደዋል። በጀርመኖቹ የሽቱትጋርቱ የሊንደን ቤተ መዘክር ፣የበርሊኑ ሁምቦልት ፎረም ፣የኮለኙ ራውተን ሽትራው ዮሴት ቤተ መዘክር  የሀምቡርጉ የዓለም ባህሎች ቤተ መዘክር እንዲሁም በሳክሰኒ ግዛት በሚገኝ የባህል ቤተመዘክር በአጠቃላይ  ከ1130 በላይ ከአፍሪቃ የተዘረፉ ቅርሳቅርሶች ይገኛሉ። በዋጋ መተመን የማይቻሉት የቤኒን ንጉሣዊ መንግስት ንብረቶች ከሚገኙባቸው የጀርመን ቤተ መዘክሮች አንዱ  የሆነው የሽቱትጋርቱ የሊንደን ቤተ መዘክር የሚገኝበት የባደን ቩርተምበርግ ፉደራዊ ክፍለ ሀገር የስነ-ጥበብ ሳይንስና ትምሕርት ሃላፊ ቴሬሳ ባወር ርክክቡ በአፋጣኝ እንደሚከናወን እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።ፊርማው ስለተከተናወነ አሁን ቅርሶቹን ከጀርመን ወደ ናይጀሪያ ቤተ መዘክሮች መዛወሩን መጀመር እንደሚችል ቲጃኒ ተናግረዋል።ሆኖም ቅርሶቹ ለናይጀሪያ ሲተላለፉ መታሰብ የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ ብለዋል።
«እነደዚህ ዓይነት ቅርሶችን በቀጥታ ማዛወር ዝግጅት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ብዙ ተያያዥ ጉዳዮች አሉ።ቅርሶቹን ለማጓጓዝ ፈቃደኛ የሆኑ ባለሞያዎች ያስፈልጋሉ።ከዚህ ሌላ ስለ መድን ዋስትና ኢንሹራንስም እንነጋገራለን። ስለ ጥበቃና ሌሎችም ጉዳዮች ትነጋገራለህ አስተሻሸግም እንዲሁ። ይህ በአንድ ለሊት የሚያልቅ ሳይሆን ጊዜ የሚወስድ ሂደት ነው። ስለዚህ እነዚህ ቅርሶች በጥንቃቄ ባለሞያዎች በሚሰጡት አስተያየት መሠረት ወደ ናይጀሪያ  እንዲመለሱ ይደረጋል። ናይጀሪያም ቅርሶቹን ለመቀበል ዝግጁ ናት።  የቅርሶቹ ማከማቻ እና ማሳያ ስፍራዎች ቅርሶቹ ከመሄዳቸው በፊት ተዘጋጅተዋል። »በአሁኑ ጊዜ በቅርቡ ለናይጀሪያ ስለሚተላለፉት ብቻ ሳይሆን በውሰት ጀርመን ሊቆዩ ስለሚችሉት  ቅርሶችም ንግግሮች እየተካሄዱ ነው። 

ምስል Annabelle Steffes-Halmer/DW
ምስል Britta Pedersen/dpa/picture alliance

 

የፈረንሳይ ጦር ከማሊ መውጣት ያሳደረው ስጋት 

ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

የተመድ የማሊን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ካራዘመ በኋላ ጀርመን ለተልዕኮው ባዘመተቻቸው ወታደሮች ብዛት የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛለች።ይሁንና ፈረንሳይ በመጪው የመጸው ወራት ጦርዋን ከማሊ ስታስወጣ አንድ ትልቅ ደኅንነት ክፍተት ይፈጠራል የሚል ስጋት አለ ። ፈረንሳይ  ፅንፈኛ ተዋጊዎችን ከማሊ ለማባረር ጣልቃ ከገባች በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2013 ዓም ነበር የተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ማሊ የዘመተው።በምህጻሩ ሚኑስማ የተባለው ማሊን የማረጋጋት ተልዕኮ የተሰጠው ይኽው ሰላም አስከባሪ ኃይል ከ9 ዓመት በኋላ ዘንድሮ የማሊ ቆይታው ለተጨማሪ አንድ ዓመት ተራዝሟል። ይሁንና ሚኑስማ ከዚያ በኋላ የሰላም ማስከበር ተልእኮውን የሚያካሂደው ፈረንሳይ በሌለችበት ነው።የፈረንሳይ ከማሊ መውጣት ሰላም አስከባሪውን ኃይል ለተጨማሪ አደጋ ያጋልጣል የሚል ስጋት ፈጥሯል።የሚኑስማ ተልዕኮ መራዘም ለረዥም ጊዜ አጠራጣሪ ሆኖ ነበር የቆየው።ይሁንና የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሊን ከጎበኙ በኋላ የበርሊን መንግሥት የጀርመን መከላከያ ሠራዊት የማሊ ቆይታን አራዝሟል።በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በማሊ የጀርመን ወታደሮች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ይጠበቃል።ይሁንና የጀርመን ወታደሮች ቁጥር ሲጨምር የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን የሚጠብቁ የአጥቂ ሄሊኮፕተሮች ቁጥር ይቀንሳል። ጀርመን በማሊ የወታደሮችዋን ቆይታ ያራዘመችው በቅድመ ሁኔታ ነው፤በአየር ከለላ እጦት ዘመቻው ለወታደሮቼ እጅግ አደገኛ ከሆነ ተልዕኮውን አቋርጣለሁ ብላለች።ይህ ደግሞ ከመጪው መጸው በኋላ የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በብቃት ማከናወን መቻሉን አጠራጣሪ አድርጎታል። የፈረንሳይ ጦር  ማሊን ለቆ ከወጣ ሰላም ለማስጠበቅ ለሚቀረው ሚኑስማ ከአየር ከለላ የሚሰጥ ላይገኝ ይችላል የሚል ስጋት አለ። ጽንፈኞች በተደጋጋሚ በሰላማዊ ሰዎች ፣በማሊ በተሰማራው ዓለም አቀፍ ኃይል እና ከሰላም አስከባሪው ጋር በሚተባበሩ ሰዎች ላይ ጥቃት በሚጥሏባት በማሊ የሚኑስማ ዘመቻ አደገኛ ነው። በዚህ የተነሳም ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎች ከቀድሞው ይጨምራሉ ተብሎም ይፈራልል። ኡልፍ ሌሲንግ ለጀርመኑ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ቅርበት ባለው ኮናርድ አደናናወር በተባለ ተቋም የማሊ ቅርንጫፍ የሳህል መርኃ ግብር ሃላፊ ናቸው ሚኑስማ ሃላፊነቱን እንዳይወጣ ያደርጉታል የሚባሉትን ምክንያቶች  ለዶቼቬለ አስረድተዋል። 
«ሚኑስማ ሥልጣኑ በግልጽ መከላከል ብቻ ስለሆነ ተዳክሟል። የፈረንሳዮች ሃላፊነት በአጥቂ ሄሊኮፕተራቸው መዋጋት ነበር። እንደ የተመድ ኃይል ፣የማረጋጋት ሚና ሳይሆን በግልጽ  አክራሪዎችን የመዋጋት ሃላፊነት ነበራቸው።ሄሊኮፕተሮቻቸውን ይዘው ስለወጡ እነርሱን በሌሎች ለመተካት እየተሞከረ ነው። ይሁንና ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ያላቸው ማሊ ሊዘምቱ የሚችሉ ሀገሮች አሁን የምሥራቅ አውሮጳ የኔቶን አባል አገራት ደኅንነት በማስጠበቅ ሥራ ተጠምደዋል።»
በዚህ የተነሳም ሚኑስማ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች ውጭ ብዙም መንቀሳቀስ ሊያዳግተው ይችላል በርሳቸው አስተያየት።ከዚህ በተጨማሪ ዋግነር የሚባለው ድርጅት ቅጥረኛ የሩስያ ወታደሮች ሰሜን ማሊ ውስጥ በንቃት ይንቀሳቀሳሉ ፤ በአሲሚ ጎይታ የሚመራው የማሊ ወታደራዊ መንግሥትም የድርጅቱን ተዋጊዎችን እየቀጠረ ነውም ይባላል።ሚኑስማ በአሳሳቢ የፀጥታ ችግሮችና ስር የሰደደ  ድህነት ውስጥ የምትገኘውን ማሊን ላለፉት 9 ዓመታት እየረዳ ነው ። ማሊ አሁንም ባትረጋጋም የጀርመን መንግሥት በዚያ የሚገኙ  ወታደሮቹን ቁጥር ወደ ወደ 1400 ከፍ አድርጓል ። እነዚህ ወታደሮች በከፊል የፈረንሳይ የፀጥታ ኃይሎች የህክምና አገልግሎትን የሚተኩና ፤ የጋኦን አውሮፕላን ማረፊያንም የሚጠብቁ ናቸው ተብሏል ። ይሁንና የጋኦን አውሮፕላን ማረፊያ የወደፊት አስተዳደር ያሳስባል ብለዋል ሌሲንግ። አውሮፕላን ማረፊያው የተገነባው በፈረንሳዮች ነው እስካሁንም የተመ ወታደሮች በፈለጉ ጊዜ እንዲጠቀሙበት አስተማማኝ ከለላ የሚሰጡትም ፈረንሳዮች ነበሩ። እርሳቸው እንደሚሉት ቅጥረኛ የተባሉት የሩስያ ወታደሮች በየአካባቢው ከተዛመቱ የተመድ የሰላም ተልዕኮ እንቅስቃሴ ሊገደብ ይችላል። ያም ሆኖ የሚኑስማ መኖር ለህዝቡ መረጋጋትና የሰላም ተስፋ ወሳኝ ነው እንደ ሌሲንግ።
«ሆኖም ሚኑስማ ባለው የሰላም አስከባሪ ኃይል ብዛትና ቃኚዎቹ ብቻውን ሰሜናዊ ማሊን ለማረጋጋት አስተዋጽኦ ያደርጋል።አንድ የተመድ ቃኚ ወደ አንድ አካባቢ ሲገባ ፍርድ ቤቶች ይከፈታሉ፤ዳኞች ሥራ ይጀምራሉ ፍርድም ይሰጣሉ። ገበያዎች ይከፈታሉ የልማት ሠራተኞችም ሥራዎቻቸውን ለማከናወን ይችላሉ።ይህ ብዙውን ጊዜ ትኩረት የማይሰጠው ጉዳይ ነው። ጉዳዩ አሸባሪዎችን መዋጋት ብቻ ነው። አዎ ፈረንሳዮች ያጎድላሉ። ይሁንና ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ተስፋ ቆርጦ በአክራሪዎች እጅ እንዳይወድቅ ጎን ለጎን የልማት ትብብሮችን ማራመድ ያስፈልጋል።»
በአሁኑ የማሊ ሁኔታ በሀገሪቱ የዘመቱትን ወታደሮችዋን ቁጥር ከፍ ያደረገችው ጀርመን በማሊ ትልቅ ሚና ይኖራታል ተብሎ ተገምቷል። ዴን ሀግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው የክሊንገንዴል ተቋም ባልደረባ አና ሽማውደር እንደተናገሩት የሚኑስማ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ  ከተራዘመ በኋላ ከፍተኛ ሠራዊት ያዘመተች ሀገር ጀርመን ናት። ሆኖም ጀርመን ወታደሮቿን ከማሊ ለማውጣት ብትወስን ሌሎች ሀገራትም የርስዋን ፈለግ መከታላቸው እንደማይቀር ይገመታል። ሽማውደር እንደሚሉት የእስካሁኑ የተመ የማሊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አርኪ አይደለም።ማሊ አሁንም ጦርነት ውስጥ ናት። ሚሊሽያዎቹን ትጥቅ የማስፈታት ጥረት እስካሁን ምንም ዓይነት ለውጥ አላመጣም ማለት ይቻላል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨማሪ የሀገሪቱ ክፍሎች በፅንፈኞች ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው። ጊዜያዊው የማሊ መንግሥት ከሩስያ አጋሮቹ ጋር በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሰው ጥቃት እየተጠናከረ ሄዷል እንደ ዶቼቬለዋ ማርቲና ሽቪኮቭስኪ ዘገባ።ፀረ ምዕራባውያንና ፀረ ፈረንሳይ  አቋም ያለው የማሊ መንግሥት በሀገሪቱ የሚከሰቱትን እጅግ አደገኛ ሁኔታዎች በውጭ አጋሮች ማሳበቡን ቀጥሏል።ያም ሆኖ ጀርመን አሁንም ራሷን  በአካባቢው ሚና ካላቸው ሀገራት አንዷ አድርጋ ነው የምትቆጥረው። ሆኖም በማሊ የአውሮጳ ኅብረት የስልጠና ተልዕኮ ሲቋረጥ ጀርመን የማሊ ጉዳይ ከሚያገባቸው ሀገራት አንዷ መሆኗ አይቀርም። 

ምስል Alexander Koerner/Getty Images
ምስል Speich Frédéric/Maxppp/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW