1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያካሄደችው የመጀመሪያው ብሔራዊ ምርጫ 75ተኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14 2016

ሶሻል ዴሞክራቱ ሹማኽር ክርስቲያን ዴሞክራቱን አደናወርን ውሸታም እያሉ ሲሰድቧቸው እና ፓርቲያቸውን (CDU)ንም የባለጸጋዎችን እና ከጦርነት አትራፊ የሆኑትን ጥቅም ለማስጠበቅ የተወከለ በማለት ሲያጣጥሉባቸው፣ የቀድሞው የኮሎኝ ከንቲባ አደናወር በአጸፋው ሹማኽርን ፀረ-ቤተ ክርስቲያን ሲሉ ከኮሚኒስቶች ጋር በመደመር ይተችዋቸው ነበር።

Deutschland Bundestagswahl 1949
ምስል dpa/picture alliance

ጀርመን ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያካሄደችው የመጀመሪያው ብሔራዊ ምርጫ 75ተኛ ዓመት

This browser does not support the audio element.

ጀርመን ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያካሄደችው የመጀመሪያው ብሔራዊ ምርጫ ሲታወስ

ፈላጭ ቆራጩ የናዚ ጀርመን አገዛዝና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከአራት ዓመታት በኋላ ጀርመናውያን ዳግም የዴሞክራሲያዊ ፓርላማ ምርጫ ካካሄዱ ዘንድሮ 75 ዓመት ሆነው። ጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 14 ቀን 1949 ዓ.ም. የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ወይም የምዕራብ ጀርመን ህዝብ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጹን ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የሄደበት እለት ነው ። ይህ እንዲሆን ያስቻለውም ጀርመናውያን የህዝብ እንደራሴዎቻቸውን በነጻና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መምረጥ የሚችሉበት ጊዜ በመምጣቱ ነበር። ነጻው ምርጫ የተካሄደው የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ከተቋቋመ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር። ከዚያ በፊት በጀርመን ነፃ ምርጫ የተካሄደው ከ17 ዓመት በፊት ነበር። ይህም ያኔ ከሀገሪቱ ዴምክራሲን ያጠፋው ሂትለር ሥልጣን ከመያዙ ጥቂት ቀደም ብሎ ነበር የተካሄደው። የጀርመን የምርጫ ዉጤትና፤ የጥምር መንግሥት ምስረታ ሂደት  


በጎርጎሮሳዊው 1945 የሁለተኛው የዓለም ጦርነትና የሂትለርም ብሔራዊ ሶሻሊዝም ቢያከትምም ከአራት ዓመት በኋላም  በ1949 በጀርመን የጦርነቱ  ፍርስራሾች እንዳሉ ነበሩ። የታሪክ ምሁሩ ቤኔዲክት ቪንትጀንስ ያኔ ከጦርነቱ በኋላ የተካሄደው የመጀመሪያው ምርጫ ብቻ እንዳይደለ ይናገራሉ። በርሳቸው አስተያየት ለምዕራብ ጀርመን አዲስ ጅምርም ነበር። «ይህ የመጀመሪያው የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ብቻ አይደለም። ይልቁንም በ1932 በመጸው ወቅት የቫይመር ሪፐብሊክ ቀውስ ውስጥ ከነበረበት የመጨረሻዎቹ ቀናት ወዲህ የተካሄደ የመጀመሪያው ነጻ ምርጫ ነው።

ከቫይመር ሪፐብሊክ በኋላ ከዚህ በፊት ያልተከሰተ የስልጣኔ መቋረጥና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከነመዘዙ ተከተለ። እናም በዚህ ረገድ ለምርጫ ለዴሞክራሲ እና አዲስ ፖለቲካዊ ማዕቀፍ ለማመቻቸት አዲስ  ጅማሮ ነበር። » ይሁንና በዚህ ምርጫ ሁሉም ጀርመናውያን አልተሳተፉም። በጦርነቱ የተሸነፈችው ጀርመን በአራት አሸናፊ ኃይላት በተያዙ ዞኖች ተከፋፍላ ነበር። ሦስቱ ምዕራባውያን ሀገራት ዩናይትድ ስቴትስ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ በተቆጣጠሩት በምዕራብ ጀርመን ምርጫ እንዲካሄድ ሲፈቅዱ፣ ሶቭየት  ኅብረት በያዘችው በምሥራቅ ጀርመን ግን ካለ ነጻ ምርጫ ክምኒስት ስርዓት ተመሰረተ። 

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከባድ ጉዳት የደረሰበት የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እስከ ጎርጎሮሳዊው 1990 ከአገልግሎት ውጭ ነበር።ምስል Usis-Dite/Leemage/picture alliance

በምርጫው የተሳተፉ የተለያዩ ፓርቲዎች 

 በምዕራብ ጀርመን የመምረጥ መብት የነበረው 31 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ ለውድድር ከቀረቡት በርካታ ፓርቲዎች መካከል የመምረጥ እድል ተሰጠው። ያኔ ታዲያ  ለውድድር የቀረቡት ፓርቲዎች ምዕራብ ጀርመንን የያዙትን የአሸናፊዎቹን የሦስቱን ኃያላን መንግሥታት ይሁንታ ማግኘት ነበረባቸው ። ከወግ አጥባቂዎቹ ከክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት በጀርመንኛው ምህፃር (CDU) እና ከክርስቲያን ሶሻል ኅብረት በጀርመንኛው ምህፃር (CSU) ፓርቲዎች እንዲሁም ከሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ SPD በተጨማሪ የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በምህጻሩ (FDP) የኮምኒስቶች ፓርቲ ፣በባቫርያ ብቻ ይንቀሳቀስ የነበረው የባቫርያ ፓርቲና የጀርመን ብሔራዊ ወግ አጥባቂ ፓርቲ እንዲሁም የካቶሊኮች ማዕከላዊ ፓርቲ የተባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችም በምርጫው ተካፍለዋል። ከነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ከከሰሙ ብዙ ጊዜያት ተቆጥረዋል። ዳግም የጀርመንን ምርጫ ያስተናገደችዉ በርሊን ከተማ


የያኔውን የምርጫ ስርዓት ከቀደሙት ልዩ የሚያደርገው ተወዳዳሪ ፓርቲዎች  በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫ ለማግኘት ቢያንስ የመራጩን 5 በመቶ ድምጽ ማግኘት እንዳለበቸው በደነገገው ደንብ ነበር። ይህም በርካታ ጥቃቅን ፓርቲዎች ከሌሎች ጋር በመጣመር የሚፈለገውን አብላጫ ድምጽ እንዳያገኙ ገፍቷቸዋል። በወቅቱ የቦን ከተማ በጊዜያዊነት የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አዲሷ መቀመጫ ሆና ተመረጠች።ሆኖም ጊዜያዊ የነበረው ይህ መፍትሄ ሁለት የተከፈለችው ጀርመን እስከተዋሀደችበት እስከ ጎርጎሮሳዊው 1990 ድረስ ቀጥሏል። ከውህደቱ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የምክር ቤቱ መቀመጫ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ወደነበረበት ወደ በርሊን ተመልሷል።

 

አደናወርና ሹማኽር ለመራጮች ያቀረቡት ጥሪ


ይሁንና ያኔ በምዕራቡ ዞን የሚገኙ ጀርመናውያን መልሰው የተቀዳጁትን የመምረጥ መብት በመጠቀም ወጣቱን የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ሕጋዊ ያደርጉታል አያደርጉትም የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም። የዋነኛዎቹ ሁለት ፓርቲዎች መሪ እጩ ተወዳዳሪዎች ማለትም የሾሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ እጩ ኩርት ሹማኽር እና የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት ፓርቲው እጩ ተወዳዳሪ ኮንራድ አደናወር ህዝቡ በብዛት ወጥቶ ላይመርጥ ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነበራቸውና ሁለቱም በየፊናቸው ህዝቡ ድምጹን እንዲሰጥ ተማጸኑ ።

«ነሐሴ 14 ቀን ማንም ሰው ቤቱ መቀመጥ የለበትም።ሁሉም ወደ ድምጹ መስጫ ጣቢያዎች መሄድ አለበት» ኮንራድ አደናወር ህዝቡ ድምጽ ለመስጠት እንዲወጣ እንዲህ ሲጠይቁ ። ኩርት ሹማኽር ደግሞ «በምዕራብ ጀርመን የሚገኘው የፌደራል ሪፐብሊክ ለጀርመን ውኅደት መሰረት ለመጣል አንድ መሆን አለበት።ጀርመናውያን እንደገና የተደራጀው አውሮጳ እኩል የሆነ ክፍል እንዲሆኑ እድል ሊሰጣቸው ይገባል ።» በማለት ሰዉ በምርጫው እንዲሳተፍ ቀስቅሰው ነበር። »

በጎርጎሮሳዊው 1949ኙ የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ የተሳተፉ የተለያዩ ፓርቲዎች ምስል dpa/picture alliance

በምርጫ ዘመቻ ወቅት የታየው የተጣናከረ የቃላት ጥቃት 

የምርጫ ዘመቻው እጅግ ጠንካራ እንኪያ ሰላንትያ ያስተናገደ ነበር። በናዚዎች የሰዎች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ለዓመታት ቆይተው የነበሩት ሶሻል ዴሞክራቱ ሹማኽር ክርስቲያን ዴሞክራቱን አደናወርን ውሸታም እያሉ ሲሰድቧቸው እና ፓርቲያቸውን (CDU)ንም የባለጸጋዎችን እና ከጦርነት አትራፊ የሆኑትን ጥቅም ለማስጠበቅ የተወከለ በማለት ሲያጣጥሉባቸው፣ የቀድሞው የኮሎኝ ከንቲባ አደናወር በአጸፋው ሹማኽርን ፀረ-ቤተ ክርስቲያን እያሉ ከኮሚኒስቶች ጋር በመደመር ይተችዋቸው ነበር። 


ምርጫው የተካሄደበት ወቅት ጀርመን ከባድ ችግሮች ውስጥ የምትገኝበት ነበር። ጦርነቱ ባደረሰው ውድመት በየአካባቢው የመኖሪያ ቤት እጥረት ነበር። ሀገሪቱ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ከምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች ወደ ምዕራብ ጀርመን በጎረፉ ስደተኞችም ተጠለቅልቃ ነበር። የዋጋ ንረትና ስራ አጥነትም በእጅጉ ተስፋፍቶ ነበር። የኤኮኖሚ ፖሊሲን በሚመለከት CDU  የማኅበራዊ ኤኮኖሚ ገበያን ሲያቀነቅን SPD አወስዳለሁ ካላቸው እርምጃዎች መካከል ቁልፍ ኢንዱስትሪዎች በመንግሥት ይዞታ ስር እንዲሆኑ ያወጣው እቅድ ይገኝበታል። ዳግም ውኅደት በምርጫ ዘመቻ ወቅት ይነሱ ከነበሩት ዋነኛዎቹ ጉዳዮች አንዱ ነበር ።ይህን ጉዳይ ሹማኽር በእጅጉ ወደፊት ሲገፉት አደናወር ደግሞ ይበልጥ ያተኮሩት  በምዕራብ ጀርመን ውኅደት ላይ ነበር ።የጀርመን ፕሬዝዳንት ምርጫ

የምርጫው ውጤትና የመንግሥት ምስረታ 


በምርጫው የመምረጥ መብት ካላቸው ጀርመናውያን 78.5 በመቶው ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ይህ የመራጮች ቁጥርም ከታሰበው በላይ ከፍተኛ ነበር። በዚህ ምርጫ ኪ,ተወዳደሩት መካከል 11 ፓርቲዎች የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ገቡ። ከመካከላቸው የክርስቲያን ዴሞክራትን የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች ቡድን 31 በመቶ ድምጽ ማለትም ከምክር ቤቱ 402 መቀመጫዎች 139ኙን በማሸነፍ በፓርላማው አብላጫውን መቀመጫ ያዘ። SPD ደግሞ 29.2 ድምጽ አግኝቶ 131 መቀመጫዎችን አሸነፈ።  52 መቀመጫዎችን ያገኘው የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ  ደግሞ ሦስተኛው ጠንካራ ፖርቲ ሆኖ አሸንፏል።የባቫርያ ፓርቲ 17 የኮምኒስቶቹ ፓርቲ ደግሞ 15 መቀመጫዎችን አግኝተው ነበር። ይህም የያኔው ምክር ቤቱ በእጅጉ የተከፋፈለ እንደነበር አሳይቷል ።  

ኮንራድ አደናወር በጎርጎሮሳዊው መስከረም 20 ቀን 1949 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በመጀመሪያው መራኄ መንግሥትነት ቃለ መሀላ ሲፈጽሙ ምስል dpa/picture alliance


የምክር ቤቱ የመጀመሪያው ጉባኤም በጎርጎሮሳዊው መስከረም 7 1949 ተካሄደ። ጠንካራ ድርድር ከተደረገ በኋላ CDU እና CSU ከ ነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ FDP ጋር ተጣምረው መንግሥት መሠረቱ ። ኮንራድ አደናወርም በጎርጎሮሳዊው መስከረም 17 ቀን 1949 ዓ.ም. መራኄ መንግሥት ሆነው ተመረጡ ። FDP የጥምሩ መንግሥት አካል በመሆኑ የፓርቲው አባል ቴዎዶር ሆይስ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሰየሙ። ይህም የሆነው  አደናወር በመራኄ መንግሥትነት ከመመረጣቸው ከአምስት ቀናት በፊት መስከረም 17 ቀን 1949 ዓ.ም. ነበር ።

የምርጫው ሂደት አስተምህሮት 

በዚህን ዓይነት መንገድ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተመሰረተው አዲሱ የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ወይም የምዕራብ ጀርመን መንግሥት ብዙ ፈተናዎችን አሳልፏል። ዶቼቬለ በስተመጨረሻ ለታሪክ ምሁሩ ቤኔዲክት ቪንትጀንስ  ከዚህ ምን ትምሕርት መውሰድ ይቻላል የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር ። እርሳቸው ሲመልሱም ያልተረጋጋችው ጀርመርን ዴሞክራሲያዊ እንድትሆን ያደረገው ይህ ሂደት ችግሮችን ለመፍታት እንደ ትምሕርት  ለመውሰድ እንደሚቻል አስረድተዋል።
«የ1949ኙን  ምርጫ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ሁሉም ነገር እንዴት እንደገና መደራጀትና መዋቀር እንደነበረበት ማየት እንችላለን። ለፖለቲካ ሽግሽጉ ና ለፖለቲካ አመራሩ እንዲሁም ለፖለቲካው ሂደትም ምስጋና ይግባቸውና በብሔራዊ ሶሻሊዝም እና በቀዝቃዛው ጦርነት በእጅጉ የተጎዳችው ያልተረጋጋችው ሀገር የተረጋጋች ዴሞክራሲያዊት ሀገር እንድትሆን አስችሏል። ምናልባት ከዚህ የምንወስደው ትምሕርት በፖለቲካ እርምጃና ተሳትፎ ነገሮች ሊስተካከሉ እንደሚችሉ ነው።»

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW