1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጀርመን ውስጥ ለየት ያለ አሠራር የዘረጋ የጋዜጠኞች ማሕበር

ሰለሞን ሙጬ
ዓርብ፣ መጋቢት 4 2018

ፖለቲከኞች ማሕበሩ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጡ ሲጋብዛቸው የመምጣት ሕጋዊ ግዴታ ባይኖርባቸውም፣ ጉዳዩ የሀገሪቱ የፖለቲካ ባሕል ያንን እንዲያደርጉ ጠንካራ ልማድ ሆኗል። አንድ ፖለቲከኛ በተለይም ቻንስለር ከማሕበሩ ለቀረበለት ጥሪ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ጋዜጠኞች ይህንን በይፋ ሊተቹት እና ለሕዝብ ሊያሳውቁ ይችላሉ።

ምንም እንኳን ፖለቲከኞች ማሕበሩ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጡ ሲጋብዛቸው የመምጣት ሕጋዊ ግዴታ ባይኖርባቸውም፣ ጉዳዩ የሀገሪቱ የፖለቲካ ባሕል ያንን እንዲያደርጉ ጠንካራ ልማድ ሆኗል።
ምንም እንኳን ፖለቲከኞች ማሕበሩ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጡ ሲጋብዛቸው የመምጣት ሕጋዊ ግዴታ ባይኖርባቸውም፣ ጉዳዩ የሀገሪቱ የፖለቲካ ባሕል ያንን እንዲያደርጉ ጠንካራ ልማድ ሆኗል።ምስል፦ Solomon Muche/DW

ጀርመን ውስጥ ለየት ያለ አሠራር የዘረጋ የጋዜጠኞች ማሕበር

This browser does not support the audio element.

"ቡንደስ ፕረሰ ኮንፈረንስ" የሚባለው ይህ አንድ ሺህ ጋዜጠኞችን ያቀፈው ማሕበር፣ ቻንስለሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ቃል አቀባዮችን በመደበኛነት ለጋዜጣዊ መግለጫ የሚጋብዝ እና አባል ጋዜጠኞች ገደብ ሳይኖር ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ የሚያደርግ ነው።

የመንግሥት ኃላፊዎች በሕግ የተደነገገ ግዴታ ባይኖርባቸውም ማሕበሩ በሳምንት ሦስት ጊዜ በጽ/ቤቱ በሚያዘጋጀው መግለጫ ላይ እየታደሙ ከጋዜጠኞች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ። ይህም ሀገሪቱ ከዘረጋቻቸው ጠንካራ የዲሞክራሲ ባሕሌች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል።

ይህ ማሕበር በሚያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አንጌላ ሜርክልን እና ኦላፍ ሾልዝን ጨምሮ የሀገሪቱ ዋና መቀመጫ ቦን ከተማ በነበረችበት ጊዜ የነበሩ ቀደምት ቻንስለሮችም ተገኝተው ምላሽ ሰጥተው ያውቃሉ።

ማሕበሩን ልዩ ያደረገው ሥራው ምንድን ነው?

ቡንደስ ፕረሰ ኮንፈረንስ "በዓለም ላይ ልዩ ተቋም ነው" ይሉታል የማሕበሩ የቦርድ አመራሮች። ይህ ከጀርመን ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ጋር አብሮ ከ 70 ዓመታት በላይ የዘለቀው የጋዜጠኞች ማሕበር፣ የሀገሪቱን የፖለቲካ መሪዎችን እና የመንግሥት ተቋማት ቃል አቀባዮችን ለጋዜጠኞች ጋዜጠዊ መግለጫ እንዲሰጡ ወደ ጽ/ቤቱ የሚጋብዝ ነው።

በዋናነት የፖለቲካ ጉዳዮችን የሚዘግቡ ጋዜጠኞችበአባልነት ያቀፈው ይህ ማሕበር በሳምንት ሦስት ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ያዘጋጃል። 1000 አባላት ያሉት ማሕበሩ በሳምንቱ ዉስጥ የትኛው የተቋም መሪ፣ ቃል አቀባይ ስለሚሰራበት ተቋም መረጃ እንዲሰጥ ግብዣውንም፣ ኹኔታውንም ያመቻቻል። የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ወደ ጋዜጠኞቹ ማሕበር እና ጽ/ቤት እንጂ ጋዜጠኞቹ ወደ ተቋሙ የሚሄዱበት አይደለም።

የማሕበሩ አባል መሆን የሚችሉት የትኞቹ ጋዜጠኞች ናቸው


የማሕበሩ አባል ጋዜጠኛ የግድ እንደ ቡንደስታግ (የፌዴራሉ ምክር ቤት)፣ ቡንደስራት (ክልሎቹን የሚወክለው ምክር ቤት) እና የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ባሉ ተቋማት ላይ አዘውትሮ የሚዘግብ መሆን ይኖርበታል። ይህም ብቻ አይደለም ጀርመን ውስጥ የሚኖሩ ሆነው ለሌላ ሀገራት መገናኛ ብዙኋንየሚሠሩ ጋዜጠኞችም የማሕበሩ አባል መሆን ይችላሉ።

ከቡንደስ ፕረሰ ኮንፈረንስ ማሕበር ቁልፍ መርኾዎች አንዱ እያንዳንዱ ጋዜጠኛ ለሚቀርበው የሥራ ኃላፊ ጥያቄዎችን ያለ ገደብ የመጠየቅ መብት ያለው መሆኑ ነው። ፖለቲከኞች ጋዜጣዊ መግለጫውን የማይቆጣጠሩት መሆናቸው ማሕበሩን ሌላው ልዩ የሚያደርገው ነጥብ ነው። ይህ በተለይ አቅማቸው ትንሽ ለሆኑ መገናኛ ዐውታሮች መረጃ በቀላሉ እንዲያገኙ ሰፊ ዕድል የሚሰጣቸው ነው።

ቡንደስ ፕረሰ ኮንፈረንስ ለሰባት አሥርት ዓመታት ራሱን የቻለ ሲሆን፣ የመገናኛ ብዙኃንን ከመንግሥት ተጽእኖ በመጠበቅ በዓለም ላይ ካሉት የዘርፉ ጥንታዊ ተቋማት አንዱ አድርጎታል።ምስል፦ Solomon Muche/DW


አባል ጋዜጠኞች በየ ዓመቱ 300 ዩሮ የአባልነት መዋጮ ያዋጣሉ


ይህ የጋዜጠኞች ማሕበር ገለልተኛ እና ከተጽዕኖ ነፃ ሆኖ የሚንቀሳቀስ መሆኑን የቦርድ አባሏ ጀርመንን እየጎበኘ ላለው 14 የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ለያዘው ቡድን ባደረገችው ገለፃ አብራርታለች።

ማሕበሩ ሥራውን የሚያከናውነው ከእያንዳንዱ አባል ጋዜጠኞች በየ ዓመቱ 300 ዩሮ የአባልኑት መዋጮ በመሰብሰብ ነው። ከ1949 - 1990 እንደ ግሪጎሪያን የጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክ ዋና ከተማ በነበረችው ቦን ከተማ የተቋቋመው ይህ የጋዜጠኞች ማሕበር፣ በኋላ ፓርላማው ወይም ቡንደስታግ ወደ በርሊን ሲዛወር አብሮ የተዛወረ ነው። የሀገሩ የዴሞክራሲያዊ ባሕል ዕድገት አካልም ሆኗል።

አብዛኞቹ የጀርመን መራኅያነ-መንግሥት የማሕበሩን ጥሪ አክብረው ለመግለጫ ሲጠሩ ይሄዳሉ


ምንም እንኳን ፖለቲከኞች ማሕበሩ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጡ ሲጋብዛቸው የመምጣት ሕጋዊ ግዴታ ባይኖርባቸውም፣ ጉዳዩ የሀገሪቱ የፖለቲካ ባሕል ያንን እንዲያደርጉ ጠንካራ ልማድ ሆኗል። አንድ ፖለቲከኛ - በተለይም ቻንስለር - ከማሕበሩ ለቀረበለት ጥሪ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ጋዜጠኞች ይህንን በይፋ ሊተቹት እና ለሕዝብ ሊያሳውቁ ይችላሉ። ይህም መሪው ለነፃ ፕሬስ አክብሮት የጎደለው ተደርጎ እንዲስሮቆጠር ያደርገዋል። በዚህ ምክንያት ጫናው በዋናነት ከሕጋዊነት ይልቅ የዴሞክራሲ ባሕሉን እና የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማስቀደም ጋር የተያያዘ ይሆናል።

ይህም በመሆኑ የቅርብ ጊዜ የጀርመን ቻንስለሮችን ማለትም አንጌላ ሜርክልን እና ኦላፍ ሾልዝን ጨምሮ የሀገሪቱ ዋና መቀመጫ ቦን ከተማ በነበረችበት ጊዜ የነበሩ ቀደምት ቻንስለሮች የማሕበሩን ግብዣ ተቀብለው ጋዜጣዊ መግለጫ ቦታው ላይ ተገኝተው ምላሽ ከሰጡት መካከል ናቸው። የዚህ ጉብኝት ተካፋይ ከሆኑት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው የአፍሪካ ሬነሰንስ ቴሌቪዥን - ARTs የዜና ክፍል ኃላፊ ጋዜጠኛ ያብስራ ገዛኸኝ ምን እንደተሰማው ጠይቀነዋል።

"አንድ የመንግሥት ኃላፊ፣ ቻንስለሩ፣ ሚኒስትሮች መጥተው በዚያ ደረጃ ገለልተኛ፣ ጋዜጠኞች ብቻ በሚመሩት መድረክ ላይ የሕዝብን ጥያቄ እንዲመልሱ የሚደረበት ልምምድ በጣም አስገርሞኛል። ለሙያው የሚሰጡትን ክብር ያሳያል።"

ቡንደስ ፕረሰ ኮንፈረንስ ለሰባት አሥርት ዓመታት ራሱን የቻለ ሲሆን፣ የመገናኛ ብዙኃንን ከመንግሥት ተጽእኖ በመጠበቅ በዓለም ላይ ካሉት የዘርፉ ጥንታዊ ተቋማት አንዱ አድርጎታል።

ማሕበሩ የእስከዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ሰንዶ ይዟል

ማሕበሩ ያለፉትን እና እስከዛሬ የተሰጡ የጋዜጣዊ መግለጫ ሰነዶችንና መዝገቦችን እንዲሁም የድምፅ እና የምስል ቅጅዎችን የሀገሪቱ ሕዝብ እና መንግሥት ታሪካዊ ሐብት አድርጎ እንደያዛቸውም ማዕከላዊ በርሊን ከተማ ውስጥ የቡንደስታግ ወይም የሀገሪቱ የፌዴራል ምክር ቤት ፊት ለፊት የሚገኘውን ዋናውን የማሕበሩን ጽሕፈት ቤት ስንጎበኝ ለመገንዘብ ችያለሁ።

ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር       
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW