1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ውስጥ በየቀኑ አንድ ሴት ትገደላለች

ሐሙስ፣ ኅዳር 12 2017

ጀርመን ውስጥ በየቀኑ አንድ ሴት ትገደላለች ። የወንጀል ፈጻሚዎቹ ደግሞ በአብዛኛው የኑሮ ተጓዳኞች (የቀድሞ አጋሮች) ናቸው ። ለመሆኑ ለሴቶች አደገኛው ማን ነው? በጭለማ ከአጥሩ ጀርባ አለያም የመኪና ማቆሚያው ውስጥ ያደፈጠው የማይታወቀው ሰው ብቻ ነው፥ ወይንስ ማን?

Deutschland I Gewalt gegen Frauen, Femizid I Symbolbild
ምስል Fabian Sommer/dpa/picture alliance

ሴቶች ከጥቃት የበለጠ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል

This browser does not support the audio element.

በሴቶች ላይ የሚደርስ የተለያየ በደል  ጀርመን ውስጥ  ቁጥሩ ጨምሯል።  የጀርመን ፌዴራል ወንጀል መከላከል መሥሪያ ቤት (BKA) በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሠረት፦ በጎርጎሪዮሱ 2023 ብቻ «ፆታ ላይ ባነጣጠር ጥቃት» 360 ሴቶች ተገድለዋል ። በሴቶች ላይ ግድያዎቹ የተፈጸሙትም አንድም ጥቃት ሸሽተው በተጠለሉበት የሴቶች መጠለያ አለያም በቤታቸው ውስጥ በሚደርስ ጥቃት ወይንም ከፍቺ ጋር በተገናኘ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ ። የጀርመን ፌዴራል የሀገር ውስጥ ሚንሥትር ናንሲ ፌዘር (SPD)፦ «በየቀኑ ሊባል በሚችል መልኩ ጀርመን ውስጥ አንዲት ሴት ከጾታዋ ጋር በተገናኘ ግድያ ይፈጸምባታል» ብለዋል ። እንዲህ ያለውን ወንጀል የጀርመን መንግሥት አንደማይታገስ፤ ወንጀል ፈጻሚዎቹ በሚገባ መቀጣት እንዳለባቸው ሚንሥትሯ አስገንዝበዋል ።

«ሴቶች ሴት በመሆናቸው ብቻ ግድያ ከተፈጸመባቸው፥ ድርጊቱን ሴቶች ላይ በሴትነታቸው የደረሰ ግድያ ብለን በትክክል ማብራራት አለብን እንዲህ ያለው ሴቶችን በሴትነታቸው የመግደል ድርጊት በትዳር ወቅት የተፈጸመ አሳዛኝ አጋጣሚ አለያም በቅናት የተነሳ የተከሰተ ብለን ማሳነስ የለብንም እንደ ማኅበረሰብ ጉዳዩን ልንመለከተው፤ ልንይዘው እና በደል በየትኛውም መንገድ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ እጅግ በጣም ግልጽ ልንሆን ይገባል » 

ለመሆኑ ለሴቶች አደገኛው ማን ነው? 

ጀርመን ውስጥ  በየቀኑ አንድ ወንድ የኑሮ አጋሩን አለያም የቀድሞ ተጓዳኙን ሊገድል ይሞክራል ።  ብዙውን ጊዜም ይሳካለታል ። እንደ የጀርመን ፌዴራል ወንጀል መከላከል መሥሪያ ቤት መረጃ፦ በ2023 ብቻ 155 ሴቶች በቀድሞ የኑሮ አጋሮቻቸው ተገድለዋል ። አብዛኛው በደል ብሎም ግድያ የሚደርስባቸው ሴቶች የሀገሩን ባሕል እና ቋንቋ በቅጡ የማያውቋ ናቸው ።  ኮብሌንዝ ከተማ የሚገኝ አንድ የሴቶች ከለላ መስጪያ ቤት ኃላፊ የሆኑት አሌክሳንደር ኔሲዩስ ይህንኑ አብራርተዋል ።

«የውጭ አገር ሴቶች፣ ፍልሰተኞች ላይ የሚፈጸመው ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ከመሆኑ አንጻር በኅብረተሰቡ ውስጥ ካለው አማካይ ከፍ ያለ ነው ብዙውን ጊዜ እዚህ ሊረዳቸው የሚችል ቤተሰብ የላቸውም፤ ቋንቋውን በቅጡ አይናገሩም፤ ስለመብት የተደነገጉ ደንቦችን ዐያውቁም እናም እነሱ ከጥቃት ማምለጪያ መንገዱን ለማግኘት ተጨማሪ የባለሞያ ርዳታ ይሻሉ »

ናይሲዩስ አንዳንድ ሴቶች በጥበቃ ቤቶች ለቆይታቸው እንዲከፍሉ መደረጉን አጥብቀው ይተቻሉ ። መጠለያው ለሁሉም ሴቶች ከክፍያ ነጻ መሆን አለበት ሲሉም ይሞግታሉ ።

በርካታ ሴቶች የጥቃት ዛቻ ሲደርስባቸው  ወደ ፖሊስ ይደውላሉ ። አንዳንዶች ደግሞ የኑሮ አጋሮቻቸውን በመፍራት ሻንጣቸውን ሸክፈው ከልጆቻቸው ጋር ወደ ሴቶች ከለላ መስጪያ ቤቶች ይሄዳሉ ። በኮብሌንዝ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በቤት ውስጥ ለሚደርሱ ጥቃቶች ተጠሪዋ ፖሊስ ጋብሪኤሌ ዝላባይንግ ጥበቃ ስለሚሹ በርካታ ሴቶች ይናገራሉ ።

የሴቶችን መግደል በመቃወም በሃኖቨር ከተማ ሰልፍ፦ ጀርመን ውስጥ በየሁለት ቀኑ አንድ የኑሮ አጋር ወይም የቀድሞ አጋር ሴትን ይገድልምስል Moritz Frankenberg/dpa/picture alliance

«ጥበቃ ያሻኛል፤ ዳግም ወደ ቤት መመለስ አልችልም፥ ድብደባ ይፈጸምብኛል፤ የግድያ ዛቻም ይደርስብኛል የሚሉ በርካታ ሴቶች በየጊዜው እዚህ ይመጣሉ »

ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች የባለሞያ ድጋፍ

ፖሊስ ጋብሪኤሌ ከባልደረቦቿ ጋር በዓመት ውስጥ ከ150 እስከ 200 በሴቶች ላይ በቤት ውስጥ የሚደርሱ በደሎችን ይመረምራሉ ። የኮብሌንዝ ፖሊሶች እንዲህ አይነት የጥቃት ሥጋት ያለባቸው ሴቶችን ከ200 እስከ 300 ኪሎ ሜትሮች ርቀት አጓጉዘው ይወስዳሉ ። ባለሞያዎችም ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች ድጋፍ ይሰጣሉ ።  በአጥቂዎቻቸው ያሉበትን ቦታ እንዳይሰለሉ እና ክትትል እንዳይደርስባቸውም አንዳንድ መተግበሪያዎችን ከእጅ ስልኮቻቸው ላይ ይደመስሳሉ ። ሥጋት የገባቸው ሴቶች ከዚህም በላይ ድጋፍ እንደሚያሻቸው ይነገራል ።

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማክተም  የተመድ ዓለም አቀፍ መታሰቢያ ቀን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ይውላል ። የሰብአዊ መብቶች ቀን ደግሞ ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ። የሴቶችን ጥቃት እንደዚህ የመሳሰሉ ጊዜያትን ብቻ ጠብቆ በማሰብ ብቻ ማስቆም አይቻልም ።  ሴቶችን ከጥቃት ለመታደግ በየትኛውም የዓለም ክፍልም ሆነ ጊዜ ተከታታይ ብርቱ ጥበቃ እንደሚያሻ በተደጋጋሚ ውትወታው ቀጥሏል ።

አንድሪያ ግሩናው/ ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW