1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስአፍሪቃ

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈር ቀዳጁ ጂኦፍሪ ሂንተን፤ የሰሩትን ቴክኖሎጅ ለምን ፈሩት?

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ግንቦት 27 2017

የሰው ሠራሽ አስተውሎት በአሁኑ ወቅት በበርካታ ዘርፎች ላይ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝ ቴክኖሎጂ ነው። ያም ሆኖ የቴክኖሎጂው ፈር ቀዳጅ ጂኦፍሪ ሂንተን፤ ቴክኖሎጂው በርካታ ፈተናዎችን ይፈጥራል የሚል ስጋት አላቸው።ለመሆኑ ሂንተን ያለሙትን ቴክኖሎጅ ለምን ፈሩት? ቴክኖሎጂው የጋረጠው አደጋስ ምንድነው?

ዶክተር ጎፈሪ ሂንተን፤ የሰውሰራሽ አስተውሎት አባት
ዶክተር ጎፈሪ ሂንተን፤ የሰውሰራሽ አስተውሎት አባት በመባል የሚጠሩ የኮምፒዩተር ሳይንቲስትምስል፦ Bildgehege/IMAGO

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈር ቀዳጁ ጂኦፍሪ ሂንተን፤ የሰሩትን ቴክኖሎጅ ለምን ፈሩት?

This browser does not support the audio element.

ሰው ሠራሽ አስተውሎት / AI/ የሥራ ቅልጥፍናን እና ምርታማነትን በመጨመር ፣ በሰዎች የሚሰሩ ስህተቶችን በመቀነስ፣ ወጪ በመቆጠብ  እና የተሻሻለ ውሳኔ በመስጠት ለሰው ልጆች በርካታ ጠቀሜታዎችን እየሰጠ ይገኛል።ያለ ሰው እርዳታ ራሱን ችሎ ተግባራትን በማከናወን፣ ሰፊ የውሂብ ስብስቦችን መተንተን እና የወደፊት ውጤቶችንም በመተንበይ ወደ ተሻለ  ትክክለኛነት ሊወስድ ይችላል። AI ፈጠራን እና ግላዊነትን በማላበስ፣ የደንበኞችን ተሞክሮ በማጎልበት የንግድ ሥራ እድገትን ያፋጥናል።

ቴክኖሎጅው ከጥቅሙ ባሻገር አደጋም ደቅኗል

ይሁን እንጅ ይህ ቴክኖሎጂ ከእነዚህ መሰል ጥቅሞቹ ባሻገር በርካታ ችግሮችንም ደቅኗል። የ AI መስራች አባት የሚባሉት ጂኦፍሪ ሂንተን ቴክኖሎጂው ከሚጠበቀው በላይ በፍጥነት እየገሰገሰ ነው ይላሉ። ከዚህ አንፃርየሰው ሠራሽ አስተውሎት የማሰብ ችሎታ ከሰዎች ከበለጠ ፣ሰዎች ይህንን ቴክኖሎጂ  ለመቆጣጠር  ምንም ዓይነት መንገድ ላይኖራቸው ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።ከዚህ ባሻገር ጆፈሪ ሂንተን እንደሚሉት ቴክኖሎጂው የጋረጠው በርካታ  አደጋውችም አሉት።  «ጥቂት የአጭር ጊዜ አደጋዎችን እና የረጅም ጊዜ አደጋዎችን እለያለሁ። በእውነቱ ትልቁን አደጋ መምረጥ ከባድ ነው። የሚገጥመን ትልቁ አደጋ እንደ ሳይበር ጥቃቶች እና፣ ምርጫዎችን ማበላሸት የመሳሰሉ ናቸው።ምርጫን ማበላሸት ምናልባት ፋሺዝም እንዲፈጠር የሚያደርግ ትልቁ  አደጋ ነው ብዬ አስባለሁ። እኔ እንደማስበው በረጅም ጊዜ ውስጥ ትልቁ አጠቃላይ ስጋት እኛ የሠራናቸው እንግዳ ፍጡራን ከእኛ ከሰዎች የበለጠ ብልህ በመሆን ሥራችንን እና ገንዘባችንን ይነጥቁናል።» ብለዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ የሥራ ቅልጥፍናን እና ምርታማነትን ይጨምራል።በአንፃሩ በርካታ አደጋዎችን ደቅኗል።ምስል፦ Christian Ohde/CHROMORANGE/picture alliance

«ገዳይ የነብር ግልገልን ማሳደግ»

በ19 50ዎቹ  በአለን ቱሪንግ እና ጆን ማካርቲ በተባሉ ተመራማሪዎች መሠረቱ የተጣለው ይህ ቴክኖሎጂ በፍጥነት በማደግ  አዳዲስ ስልተቀመሮችን እና መተግበሪያዎች እንዲወጡ በማድረግ ላይ ይገኛል።በ1986 ጂኦፍሪ ሂንተን  እና ባልደረቦቻቸው ለማሽን መማሪያ ዋና የሆነውን የሰው ሠራሽ የነርቭ መረቦችን/ Artificial neural networks/  በማዘጋጀት፤ ቴክኖሎጅውን ወደ ላቀ ደረጃ አሳድገውታል።ጂኦፍሪ ሂንተን በዚያን ወቅት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ከሰው ልጅ የማሰብ ችሎታ አይበልጥም የሚል እምነት ነበራቸው። ቢያንስ በሕይወት ዘመናችን ይህ አይሆንም የሚል ግምት የነበራቸው።የጎግል የቀድሞ ሠራተኛው  ሂንተን፤ ያለሙት ቴክኖሎጂ ተስፋ ሰጪ ነገር ግን አንድ ሕፃን ልጅ ካለው ችሎታ በላይ የተሻለ ማድረግ የማይችል አድርገው ነበር የሚያዩት። በአሁኑ ጊዜ ግን በዚህ ጉዳይ እርግጠኛ አይደሉም። እንዲያውም ቴክኖሎጂው የላቀ የማሰብ ችሎታን ከሰዎች ሊነጥቅ ይችላል ብለው ይሰጋሉ።ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ከተራ የትርጉም ሥራ እሰከ ያለ ሰው የሚሽከረከሩ መኪናዎች እና ለጦርነት የሚውሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች  ድረስሰው ሠራሽ አስተውሎት ሰዎችን ተክቶ ውሳኔ በመስጠት እና በመሥራት ላይ ይገኛል።ከዚህ አንፃር፤ሂንተን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ልማትን ወደ ገዳይነት ሊለወጥ የሚችል የነብር ግልገልን ከማሳደግ ጋር ያነፃጽሩታል።

ቴክኖሎጅው ሰዎችን ከስራ ያፈናቅላል 

የብሪታንያ እና የካናዳ ጥምር ዜግነት ያላቸው የኮምፒዩተር ሳይንቲስቱ ጆፈሪ ሂንተን ቴክኖሎጅው ሥራ በመንጠቅ ሰዎችን ሥራ አጥ ያደርጋል የሚል ስጋትም አላቸው።
«ስለዚህ ፍላጎቱ የሚለጠጥ መሆኑን መመልከት ያለብን ይመስለኛል። ስለዚህ፣ በጤና እንክብካቤ፣ ዶክተሮችን እና ነርሶችን 10 እጥፍ ቀልጣፋ ማድረግ ከተቻለ፣ ሁላችንም 10 እጥፍ ተጨማሪ የጤና እንክብካቤ እናገኛለን። ያ በጣም ጥሩ ነበር። የትኛውንም ሥራና ሠራተኛ አይነካም። ነገር ግን ሰዎችን የሚተኩ ሌሎች መስኮች አሉ። ስለዚህ በእነዚያ አካባቢዎች ሥራ አጥነት ይኖራል ብዬ አስባለሁ።»የ2025 የዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ መድረክ ያወጣው መረጃም የሳይንቲስቱን ስጋት ያጠናክራል።በመረጃው መሠረት በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት ያለው የሥራ ገበያ 48 በመቶ በሰዎች የሚሠራ ሲሆን በ2030 ግን ይህ አኀዝ ወደ 32 በመቶ ዝቅ ይላል።ከሥራ መፈናቀል ባሻገር  ስልተቀመር ላይ የሚታይ መድልኦ ሌላውቴክኖሎጂው የሚያመጣው ጉዳት ሲሆን፤ በዚህም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ንድፎች በሰለጠኑበት መረጃ ውስጥ ያሉትን አድሎአዊ መረጃዎች ሊያንፀባርቁ እና ሊያሳድጉ ይችላሉ።ይህም በተለያዩ ዘርፎች ማለትም እንደ ብድር አሰጣጥ፣ የፍትህ እና የዳኝነት ስርዓት እና ቅጥርን በመሳሰሉ ጉዳዮች አድሎአዊ ውጤቶችን ያስከትላል። 

የተሳሳቱ ውሳኔዎችን ሊወስን ይችላል

ምንም እንኳ ማሽን የሰውን ልጅ ተክቶ እንዲሰራ ቢሰለጥንም፤ ልክ እንደ ሰዎች ርኅራኄ፣ ሀዘኔታ፣ ደስታ የመሳሰሉ ስሜቶች ስለሌሉት፤ ወይም ይህንን የሚገልፁ የፊት ገፅታ እና የሰውነት እንቅስቃሴዎች ስለማይለይ በውሳኔ ወቅት ከባድ ስህተት ሊፈፅም ይችላል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሰውን ተክተው እንዲሰሩ ከሚደረጉት ማሽኖች መካከል ሮቦቶች ይገኙበታል።ምስል፦ Alexander Limbach/Zoonar/picture alliance

ከአካባቢ ጥበቃ አንፃርም ሞዴሎችን ለማሰልጠን እና  ለማሰማራት ከፍተኛ የኃይል ፍጆታ እና የሃብት ፍላጎቶች  የአካባቢ ብክለት መዘዝን ሊያስከትሉ ይችላሉ።የተሳሳተ እና የተዛባ መረጃን በተመለከተም፤ ቴክኖሎጂው የውሸት ዜናዎችን፣ ፕሮፓጋንዳዎችን እና ሌሎች የተሳሳቱ መረጃዎች ስርጭትንም ሊያባብስ ይችላል።  ሰው ሠራሽ አስተውሎት ይበልጥ የተራቀቁ የሳይበር ጥቃቶችን ለመፍጠር ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።ከዚህ አንፃር ከፍተኛ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያው አቶ ብሩክ ወርቁ  እንደሚሉት ቴክኖሎጅው የሳይበር ደኅንነት ስጋቶችን ሊፈጥር ይችላል።

ቴክኖሎጅው ለውሂብ ግላዊነት ጥሰት ይዳርጋል

በሌላ በኩል  ሰውሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ መረጃን በከፍተኛ መጠን ለመተንተን ችሎታ  ያለው ቢሆንም፤ የውሂብ ግላዊነትን በመጣስ፤ ምስጢራዊ  መረጃን ላልተፈለገ ዓላማ ጥቅም ላይ እንዲውል ወይም ለሌላ ወገን ያለ አግባብ ተላልፎ ሊሰጥ ይችላል።በዚህ የተነሳ አቶ ብሩክ እንደሚሉት የመረጃ ግላዊነት ላይ ስጋት ይፈጥራል። ከዚህ በተጨማሪ ለማጭበርበር እና ለመረጃ ምንተፋም ሊያጋልጥ ይችላል።ያም ሆኖ ከጉዳቱ ባሻገር ሰውሠራሽ አስተውሎት ለሳይበር ደኅንነት ጥበቃም አስተዋፅኦ ያደርጋል።ከዚህ አንፃር አቶ ብሩክ ቴክኖሎጂው፤«በሁለት በኩል የተሳለ ቢላዋ ነው»ይሉታል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአፍሪቃ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቋማት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ አተኩረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ለአኅጉሪቱ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ቢሆንም፤ በዚያው ልክ ስጋቶች እንዳሉትም ያስጠነቅቃሉ።ምክንያቱም የሰውሠራሽ አስተውሎት ንድፎች መረጃ የሚሰበስቡት ባደጉ ሃገራት የመረጃ ቋት ላይ ተመስርቶ በመሆኑ እና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ ሃገራት የቴክኖሎጂ ተቀባይ ብቻ በመሆናቸው ከጥቅሙ ባሻገር የሚመጣውን ጉዳት ለመከላከል የቴክኖሎጂ አቅም የላቸውም።

አቶ ብሩክ ወርቁ፤  ከፍተኛ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያ ምስል፦ Privat

ችግሩን ለመቆጣጠር ዓለም አቀፍ ህጎች እና መመሪያች 

ይህን መሰሉን የቴክኖሎጅውን ጉዳት ትልልቅ ኩባንያዎች ያውቁታል የሚሉት ጆፍሪ ሂንተን  ከሚያገኙት ትርፍ ባሻገር ለችግሩ ትኩረት እንደሌላቸው ገልፀዋል። በመሆኑም ችግሩን ለመቆጣጠር  ዓለም አቀፍ ሕግ እና የመንግሥታት ቁጥጥር ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።«እኔ እንደማስበው ብዙዎቹ ትልልቅ እና አንጋፋ ኩባንያዎች ጉዳዩን ያውቃሉ ።ነገር ግን ከዚያ በኋላ የአጭር ጊዜ ትርፍ ነው የሚያዩት።እኔ እንደማስበው የነዳጅ ኩባንያዎች አካባቢን የሚበክሉባቸው ቦታዎች ነበሩ። ነገር ግን የእኔን ቤት ለመጠበቅ ለነዳጅ ኩባንያዎች አስፈላጊ አይደለም። ስለዚህ ተጨማሪ የመንግሥት ቁጥጥርን ማየት እንፈልጋለን። ኤአይ በአጠቃላይ ጠንካራ ተጨማሪ የመንግሥት የቁጥጥር ደንብ ያስፈልገዋልለማለት እወዳለሁ።» በማለት ገልፀዋል።

አቶ ብሩክ በበኩላቸው  የክሎን ቴክኖሎጂን ለመሳሰሉ ዘርፎች የሚነሱ የሞራል እና የሕግ ማዕቀፎች ሁሉ፤ ለሰውሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅዎችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕግ ሊወጣለት እንደሚገባ  አብራርተዋል።ያ ካልሆነ ግን በተለይ አቅም የሌላቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ፤የቴክኖሎጂ ተቀባይ ሃገራት የበለጠ ተጎጅ ይሆናሉ ብለዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።



ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW