ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ ፕሬዝደንት ሆነዉ ተሾሙ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 30 2017
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነትጀነራል ታደሰ ወረደ ተረከቡ። ጀነራል ታደሰ ወረደ ከሕገመንግስት እና የፕሪቶርያ ውል ያፈነገጡ የተባሉ እንቅስቃሴዎች ለማስቆም መስማማታቸው ዛሬ የተሰራጨው 'የትግራይ ክልል አካታች ግዚያዊ አስተዳደር የተልእኮ አፈፃፀም የቃል ኪዳን ሰነድ' የተሰኘ ባለስምንት ነጥብ ፅሑፍ ያመለክታል።
ትላንት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በመምራት ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነው ካሰናበቱ በኃላ ዛሬ በተሰራጨ መረጃ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንትነት ጀነራል ታደሰ ወረደ መረከባቸው ተገልጿል። የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የፅሑፍ መልእክት ለሁለት ዓመት የክልሉ ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ባለፉት ግዚያት የነበሩ ጥንካሬዎችና ድክመቶች እንደሚገነዘቡ፣ በትግራይ ያለው ክፍተት እንደሚሞሉ ተስፋ እንደሚጣል ያወሳል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት ዛሬ የተረከቡት ጀነራል ታደሰ ወረደ የፈረሙት 'የቃል ኪዳን ሰነድ' ተብሎ የተሰራጨ ፅሑፍ እንደሚያመለክተው ደግሞ ከሕገመንግስት፣ የፕሪቶርያ ውል እና የሀገር ሉአላዊነት ያፈነገጡ የተባሉ እንቅስቃሴዎች [በትግራይ] እንዲቆሙ ለማድረግ መስማማታቸው ያመለክታል። ከዚህ በተጨማሪ ይህ የትግራይ ክልል አካታች ግዚያዊ አስተዳደር የተልእኮ አፈፃፀም የቃል ኪዳን ሰነድ የተሰኘ ባለስምንት ነጥብ ስምምነት ጀነራል ታደሰ ወረደ ክልሉ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲያዘጋጁ፣ የክልሉ ህዝብ በሀገራዊ ምክክር መድረክ እንዲሳተፍ እንዲያደርጉ፣ ትጥቅ የመፍታት እና የቀድሞ ተዋጊዎች ወደሰላማዊ ህይወት የመመለስ ስራ በአፋጣኝ እንዲፈፀሙ ማድረግ የሚሉ ነጥቦች ተካተውበታል።
በአዲሱ ፕሬዝደንት ሹመትጉዳይ በትግራይ የተለያየ አስተያየት እየተሰጠ ያለ ሲሆን፥ አስተያየት ያጋሩን ፖለቲከኛ አቶ ደጋፊ ጎደፋይ፥ ለሁለት ዓመት ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ከቆዩት ጀነራል ታደሰ ወረደ የተለየ ነገር እንደማይጠብቁ ያነሳሉ። ፖለቲከኛው ጨምረውም የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር አካታች ሆኖ እንደአዲስ መዋቀር አለበት የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።በተለይም በክልሉ አንዣቦ የቆየ የፀጥታ ስጋት አዲስ የተሾሙት ፕሬዝደንት ሊቀርፉ ይችላሉ የሚሉ ሓሳቦች በሌሎች የሚሰነዘር ሲሆን፥ በትግራይ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የመመለስ ተግባር ደግሞ ቀዳሚ ሐላፊነታቸው ሊያደርጉ እንደሚገባ በበርካቶች እየተገለፀ ነው። ከሽረ አስተያየት የሰጡን አቶ ገብረመድህን ገብረማርያም በተለይም የተፈናቃዮች ጉዳይ በአጭር ግዜ ውስጥ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ