1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጅቡቲ በፍልሰተኞች ላይ ያወጣችው ማስጠንቀቂያ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 17 2017

ጅቡቲ በሕገ-ወጥ መንገድ በሀገሪቱ የሚኖሩ ሰነድ አልባ የውጭ ሀገር ዜጎች እስከዚህ ወር መጨረሻ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ በጥብቅ አሳስባለች።

የጅቡቲ የባሕር በር
የጅቡቲ የባሕር በርምስል፦ Solomon Muchie/DW

ጅቡቲ በፍልሰተኞች ላይ ያወጣችው ማስጠንቀቂያ

This browser does not support the audio element.

አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኝ ይህ የጅቡቲ ውሳኔ ባልተለመደ መልኩ ኢትዮጵያዊያንንም ማካተቱ ሀገሪቱ «ከኢትዮጵያ ልታገኘው የምትችለው የወደብ ኪራይ ወይም አገልግሎት ጥቅም ሊቀንስ አልያም ሊቋረጥ» የሚችልበት ኹኔታ እንዳለ የሚጠቁሙ ጉዳዮች በመኖራቸው የመጣ  ሳይሆን እንዳልቀረ ገልፀዋል። በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጉንና ቀነ ገደቡ «በሦስት ወር እንዲራዘም» ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር አስታውቋል። የጅቡቲ ባለሥልጣናት ግን «የተያዘው ዕቅድ የሚሻሻልበትና በልዩ ሁኔታ የሚታይ ሀገር እንደሌለ» በግልጽ ምላሽ መስጠታቸውን ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

1.1 ሚሊዮን ዜጎች ያሏት ጅቡቲ ሕጋዊ ፍቃድ የሌላቸው እና በሕገ-ወጥነት በሀገሪቱ የሚኖሩ ያለቻቸው የውጭ ሀገር ዜጎች እስከ ሚያዝያ መጨረሻ ለቀው እንዲወጡ በብርቱ አስጠንቃለች። «ጸጥታ እና የጤና ችግሮች» የዚህ ውሳኔ ምክንያት ሆነው የቀረቡ ጉዳዮች ናቸው ተብሏል። የፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ አማካሪ ከፈረንሳይ የዜና ዐውታር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ «ጅቡቲ የዓለምን ድህነት መሸከም እንደማትችል» መናገራቸው ተዘግቧል። አማካሪው «ሁሉንም የዓለምን ድህነት ማስተናገድ አንችልም» በማለት የመንግሥታቸው የውሳኔ መነሻ ምን እንደሆነም ጠቁመዋል።

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ «ርምጃው አንድ መንግሥት ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።» ጅቡቲ ተከተለች የሚባለው ፖሊሲ የአንድ መንግሥት ዋና ተግባር ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው።»

የዓለም አቀፍ ሕግ እና ዲፕሎማሲ ተንታኝ አስተያየት

በጉዳዩ ላይ ጅቡቲ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት፣ ኬንያ የሚገኘውን የድርጅቱ የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ ጽሕፈት ቤት እና የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ምላሽ አላገኘም። የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኙ ግን ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ጅቡቲ ሳትቀር የምታስፈራራበት ደረጃ ላይ የመደረሱ ሀቅ አድርገው ጠቅሰውታል።

«ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲ ቅርቃር ውስጥ የገበንበት ወቅት ነው። ገናና፣ ብርቱ፣ ጠንካራ ከምንለው ተክለ ቁመና ወርዶ [ዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬዋ - የኢትዮጵያ] እነ ጅቡቲም የሚያስፈራሯት ሀገር መሆን ችላለች።»

ጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስለጉዳዩ ያወጣው መግለጫ

ጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጉዳዩ ላይ ከጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር መወያየቱን አስታውቋል። ኤምባሲው በጅቡቲ የሚኖሩና ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች ብዛት ስላላቸው፣ ትምህርት በመከታተል ላይ ያሉ ዜጎች ልጆቻቸው ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ መደረግ ስላለበት፣ የንግድ ድርጅት ያላቸው ዜጎች እቃቸውን አጣርተው መሸጥ ስላለባቸው፣ በተለያዩ ሥራዎች ተቀጥረው ለሚሰሩ ዜጎች ያልተከፈሉ ውዝፍ ከፍያዎች ካሉ እንዲከፈላቸው እንዲሁም በፍርድ ቤት ያላለቀ ጉዳይ ያላቸው ዜጎች ሁኔታን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለሻው ቀን ቢያንስ በሦስት ወር እንዲራዘም ጥያቄ ማቅረቡን ገልጿል።

የጅቡቲ ዋና ከተማ ከፊል ገፅታምስል፦ Solomon Muche/DW

የጅቡቲ ባለሥልጣናት ለዚህ በሰጡት ምላሽ «በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎችን ለማስወጣት የተያዘው ዕቅድ የሚሻሻልበትና በልዩ ሁኔታ የሚታይ ሀገር እንደሌለ» በግልጽ ማመልከታቸውን ኤምባሲው አስታውቋል።  

ጅቡቲ ለረጅም ዓመታት እዚያው የሚኖሩ «ኢትዮጵያዊያንን ስደተኞች ናችሁ፣ ሰነድ የላችሁም እና አባርራለሁ የሚል አቋም ስታራምድ ታይቶ አይታወቅም» ያሉት የዲፕሎማሲ ተንታኙ ሀገሪቱ የተፈጠረባት ሥጋት የዚህ መነሻ ሳይሆን እንዳልቀረ አብራርተዋል።

«ኢትዮጵያዊያንን ሰነድ አልባዎች ናችሁ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ድንበሬን አቋርጣችሁ ገብታችኋል፣ አሁን አባርራለሁ ማለቷ ከኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችለው ጥቅሟ ሊከበርላት ስላልቻለ ነው። በየዓመቱ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የምታገኝበት የወደብ አገልግሎት፣ የወደብ ኪራይ እና ከወደብ ጋር ተያይዞ የምታገኝበት ጥቅም ሊቀብስ ወይም ሊቋረጥ የሚችልበት ዕድል እንዳለ የሚጠቁሙ ጉዳዮች አሉ።»

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ቀይ ባሕርን አቋርጠው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና የበለፀጉ የአውሮፓ ሃገራት ለመግባት መሸጋገሪያ የሆነችው ጅቡቱ፣ ድህነትን እና ግጭትን የሚሸሹ በተለይ ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ የሚነሱ ስደተኞች በብዛት የሚንቀሳቀሱባት፣ ብዙ ሰደተኞችም ባሕር ሲያቋርጡ የሚያልቁባት ሀገር ናት።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW