1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጅቡቲ፣ የትንሺቱ ሐገር ትልቅ ሚና

ሰኞ፣ ሚያዝያ 4 2013

በምጫዉ ዋዜማ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተባባሰዉ የአፋርና የኢሳ ጎሳዎች ግጭት የጅቡቲ ወታደሮች ከኢሳዎች ጎን ተሰልፈዉ መዋጋታቸዉ በተደጋጋሚና በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ሌ ኑቬል ደ ጅቡቲ የተሰኘ ጋዜጣ ወይም መፅሔት እንደፃፈዉ ደግሞ የጁቡቲ ፕሬዝደንታዊ ዘብ የኢሳ ተወላጆችን እያሰለጠነና እያስታጠቀ ወደ ኢትዮጵያና ወደ ሶማሊ ላንድ እያሰረገ ያስገባል።

Dschibuti Einweihung Internationale Freihandelszone
ምስል Getty Images/AFP/Y. Chiba

ጅቡቲ፣ በአካባቢዉ ያላት ተፈላጊነት

This browser does not support the audio element.

 

ትንሽ ናት።በረሐማ። ግን ቀይ ባሕርን ከሕንድ ዉቅያኖስ የምታገናኝ ሥልታዊ፣ ከዓለም እጅግ ባቴሌ የባሕር መስመር አንዱን የምታስናግድ ተፈላጊ ሐገር ናት።ጅቡቲ።ባለፈዉ አርብ የከ20 ዓመት ዘመን ገዢዋን ለተጨማሪ 5 ዓመት ዘመነ-ሥልጣን መርጣለች።ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌን።ጌሌ ሥልታዊቱን፤ ጠቃሚይቱን ትንሺቱን ሐገር ለ20 ዓመት የገዙት እንደ ስልጣኑ ሁሉ የአገዛዝ ብልሐት-ስልቱንም ከአጎታቸዉ በመዉረሳቸዉ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።ይሁንና በዘንድሮዉ ምርጫ ዋዜማ ኢትዮጵያ ዉስጥ ኢሳ-ሶማሌን ከአፋር ጋር ደም ባቃባዉ ጦርነት ረጅም እጃቸዉ አለበት መባሉ፤ ኢትዮጵያን በዉኃ አቃቢነት መዉቀስ-መክሰሳቸዉ የሃያ ዓመት አገዛዛቸዉ በነበረበት መቀጠሉን ያጠያይቅ ይዟል።የጅቡቲ ምርጫ ዉጤት መነሻ፣ባካባቢዉ ያላት ተሰሚነት ማጣቀሻ፣ የመሪዋ ያመራር ስልት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

የዩናይትድ ስቴትስ፣ የፈረንሳይ፣ የቻይና የኢጣሊያና የጃፓን ጦር ሠፍሮባታል።የአረብ ኩባንዮችና የመርከብ ድርጅቶች ይራኮቱባታል።መሪዋ ኡስማኤል ዑመር ጉሌ፣ በሕዝብ ተወደዉ፣ ከተፎካካሪዎች በልጠዉ፣ ተመርጠዉ ሳይሆን ሥልጣንን ካጎታቸዉ የወረሱ አምባገነን ናቸዉ።ተቃዋሚ፣ ተቺዎቻቸዉን እየደፈለቁ ከሃያ ዓመት በላይ የገዙ ጨቋኝ ናቸዉ።የፖቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የትንሺቱን ሐገር ሥልጣንና ሐብት ለዘመድ አዝማዶቻቸዉ ያከፋፈሉ፣ ወራሽ ፍለጋ የሚቃትቱ ስግብግብም ናቸዉ።

ምርጫ ላይ ደረሱ።ሐብቱንም ሥልጣኑንም ጠቅልለዉ የያዙት የ73 ዓመቱ አዛዉንት ለአምስተኛ ዘመነ-ሥልጣን ለመመረጥ ሲቀሰቅሱ ሕዝባቸዉ አሁንም እንደ እስካሁኑ ከጎናቸዉ እንዳይለይ ጠየቁ።የሐገራችን ሐብት «እንድንጋራ» ዓይነት ማለታቸዉ ግን  አጠያያቂ ብጤ ነዉ-የሆነዉ።ግን አሉት።«ትንሽ ሐገር ነን።ሐገራችንን ለመገንባት፣ የሐገራችንን ትሩፋቶች ለመጠቀም፣ በአንድነት መቆም አለብን።የሐገራችንን ሠላም ለማስከበር እንጥራለን።»

በርግጥም ጁቡቲ  አንድ ሚሊዮን የሚገመት የኢሳ-ሶማሌና የአፋር ሕዝብ የሚኖርባት ትንሽ ሐገር ናት።23 ሺሕ ስኩየር ኪሎ ሜትር ትሰፋለች።በረሐማ ግን ስልታዊ ሐገር ናት።ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ በወጣች በወሩ ሐምሌ 1969 ሰሜንና ደቡብ አቃርጠዉ የያዝዋት ትላልቅ ፈርጣማ ጎረቤቶቿ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ወደ ሐምሳ ሺሕ ሕይወት ባረገፈ ጦርነት ሲተላለቁ፣ ገለልተኛ መስላ መዓቱን በዘዴ አልፋዋለች።

ምስል Tony Karumba/AFP/Getty Images

ኢትዮጵያ የጅቡቲን ነፃነት የፈቀደዉ መንግስቷን በፈረካከሰዉ፣ ሰሜን ክፍለ-ግዛትዋን ባስገነጠለዉ ጦርነት ስትዋጅ ፍንጣቂ ደም ሳይነካት ግን በቅርብ ታዝባለች።ኢትጵያ ከቀድሞ ክፍለ-ሐገሯ ኤርትራ ጋር ከመቶ ሺሕ በላይ ሕይወት ባረገፈ ጦርነት ስትማገድ እሳትም እንጨትም ሳትሆን አርፋ አልፋዋለች።በዚሕ ሁሉ ዘመን ያቺን ትንሽ ሐገር የገዙት ሐሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን ነበሩ።በ1992 የኦፕቲዶንን ስልጣን የወረሱት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ የአጎታቸዉን ስልት መከተል-አለመከተላቸዉ አንዳዴ እርግጥ እንደሆነ ሌላ ጊዜ እንዳነጋገረ 20 ዓመት ገዙ።

የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት አገዛዛቸዉ አምባገነናዊ ይሁን እንጂ አቶ ዩሱፍ «አንዳድ» እንዳሏቸዉ የአካባቢዉ ገዢዎች «ጀብደኛ» አይደሉም።የጎረቤቶቻቸዉ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ዕዉቅትና ስልትም ወሳኝ ነዉ። የኢትዮጵያና የኤርትራ ጠብና ጦርነት በጋመበት በ1991 ሁለቱን ሐገራት ለመሸምገል የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ዋጋድጉ-ቡርኪና ፋሶ በጠራዉ ጉባኤ ላይ ከተገኙት መሪዎች አንዱ የጅቡቲዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን ነበሩ።

ከጉባኤዉ አዳራሽ ከኦፕቲዶን መቀመጫ ፈንጠር ብለዉ የተቀመጡት የኤርትራዉ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዛዉንቱን መሪ በአረቢኛ፣ ኋላ እንደሰማነዉ «ሰደቧቸዉ።» ኦፕቲዶን ድምፅ ማጉያዉን ከፈቱና በፈረሳይኛ ከበስተግራዬ የተቀመጡት ሰዉዬ----ጤነኝነታቸዉ» እያሉ በሽክሹክታ ለሰሙት ስድብ አፀፋዉን አዳራሹ ዉስጥ ለነበሩት ለሁሉም ሰጡ።

የሁለቱ ተጎራባች ሐገራት መሪዎች ዋጋዱጉ ላይ የጀመሩት ጠብ ተካርሮ በ2000 የኤርትራ ጦር ራስ ዱሜራ ላይ ሲሰፍር ቃታ ያስብ ያዘ።የድንበር ዉዝግቡ ዛሬም ሙሉ በሙሉ አግባቢ መፍትሔ አላገኘም።የዋጋዱጉዉ የቃላት መጎሻሸም ለድንበር ዉዝግቡ መነሻም ሆነ መገለጫ ምክንያቱ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ አዳልታለች መባሉ ነበር።ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ለምትሰጠዉ የወደብ አገልግሎት ባለሙያዎች እንደሚገምቱት በዓመት በአማካይ  2 ቢሊዮን ዶላር ታገኛለች።ይሕ ማለት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በመዋጋትዋ ያን ያሕል ገቢ አጥታለች,።

አዲሱ የኢትዮጵያ መሪ ከኤርትራዉ ፕሬዝደንት ጋር አቶ ዩሱፍ «እፍ እፍ» ያሉትን ወዳጅነት ሲመሰርቱ ደም ያቃባዉን፣ በግለሰቦች ስልጣንና ፍላጎት ላይ የተመሰረተዉን፣ የምጣኔ ሐብት ጥቅም የሚነዳዉን የአካቢዉን የፖለቲካ-ዲፕሎማሲ ዉጥንቅጥ በቅጡ ያጤኑት አይመስልም።የኤርትራና ኢትዮጵያ መሪዎች የሶማሊያዉን አቻቸዉን  ሲጋብዙ የጅቡቲዉን «እንዳያማሕ ጥራዉ» ዓይነት ጠርተዉ ማለፋቸዉ ለትንሺቱ ሐገር አንጋፋ መሪ የሚዋጥ አልሆነም።እንደገና አቶ ዩሱፍ።

ምስል Getty Images/AFP/S.Maina

ፕሬዝደንት ዑመር ጌሌ በምረጡኝ ዘመቻቸዉ ወደፊት ስለሚከተሉት የዉጪ መርሕ በግልፅ ያሉት ነገር የለም።ሕዝባቸዉ ግን ሐገሩን የማልማትና የመጠበቅ ሐላፊነቱን እንዲወጣ አደራ ብለዋል-ከሌላ አትጠብቁ።«ስለሐገራችን ልማት ማሰብ አለብን።ስለልማታችን ማሰብ አለብን።እኛ ለራሳችን ካለሰብን ማንም ሊያስብልን አይችልም።ሐላፊነታችሁን መወጣት አለባችሁ።ወጣትም ሽማግሌም።»

በምጫዉ ዋዜማ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተባባሰዉ የአፋርና የኢሳ ጎሳዎች ግጭት የጅቡቲ ወታደሮች ከኢሳዎች ጎን ተሰልፈዉ መዋጋታቸዉ በተደጋጋሚና በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ሌ ኑቬል ደ ጅቡቲ የተሰኘ የኢንተርኔት ጋዜጣ ወይም መፅሔት እንደፃፈዉ ደግሞ «ፕሬዝደንሻል ጋርድ» የተሰኘዉ የጁቡቲ ፕሬዝደንታዊ ዘብ፣ የኢሳ ተወላጆችን እያሰለጠነና እያስታጠቀ ወደ ኢትዮጵያና ወደ ሶማሊያ በተለይም ሶማሊ ላንድ እያሰረገ ያስገባል።

በዘገባዉ መሰረት ጦሩ የሚያሰልጥንና የሚያስታጥቀዉ የጁቢቲ ኢሳዎችን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያና የሶማሊ ላንድ የተለያዩ የኢሳ ነገድ አባላትን ጭምር ነዉ።የፅሑፉ አዘጋጆች አስተያየት እንዲሰጡን   በኢሜየል ብንጠይቅም እስካሁን መልስ አልሰጡንም።ባለፈዉ ሳምንት የሶማሌ ክልል ባለስልጣናትን በስልክ ለማነጋገር ሞክረን አልተሳካልንም።

ምስል picture-alliance/dpa

ከአምደ መረቡ ዘገባ በተጨማሪ አፋሮች በተደጋጋሚ ለሚሰነዝሩት  ወቀሳ የጅቡቲ መንግሥት እስካሁን በይፋ የሰጠዉ ማስተባባያ የለም።እንዲያዉም ኢስማኤል ጌሌ በምርጫዉ ዋዜማ በቲዊተር ባሰራጩት መልዕክት ኢትዮጵያ የአዋሽ ወንዝ ዉሐን እያቀበችብን ነዉ በማለት ከሰዋል።በአፋርና ኢሳዎች ግጭት የጅቡቲ ወታደሮች ተካፍለዋል ለሚለዉ ወቀሳም ሆነ ለፕሬዝደንት ጉሌ መልዕክት ከኢትዮጵያ በኩል እስካሁን በይፋ የሰማነዉ አፀፋ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በፌስ ቡክ ለፕሬዝደንት ጌሌ ያስተላለፉት «የእንኳን ደስ ያለዎት» መልዕክት ነዉ።እንኳን ደስ ያላቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW