1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጅቡቲ ፤ የትንሿ ትልቅ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ጥሪ

ሰኞ፣ ግንቦት 5 2016

በአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር እንዳላት የሚነገርላት ጅቡቲ ለዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ጥሪ አቀረበች። ሀገሪቱ በዛሬው ዕለት ዓለም አቀፍ ባለሃብቶችን ያሰባሰበ አንድ የኢኮኖሚ ጉባኤ አዘጋጅታለች። ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ሰባት ሃገራት ወታደራዊ የጦር ሠፈር የገነቡባት ጅቡቲ አብዛኛው የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ ይሳለጥባታል።

የጅቡቲ የኤኮኖሚ ጉባኤ
ዓለም አቀፍ ባለሃብቶችን ያሰባሰበው የኢኮኖሚ ጉባኤ በጅቡቲምስል፦ Solomon Muche/DW

የጅቡቲ የኢኮኖሚያዊ ጉባኤ

This browser does not support the audio element.

መረጋጋት በተሳነው የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር እንዳላት የሚነገርላት ጅቡቲ ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ሀብታቸውን ፈሰስ አድርገው እንዲያለሙ ጥሪ አደረገች። ሀገሪቱ በዛሬው ዕለት ዓለም አቀፍ ባለሃብቶችን ያሰባሰበ አንድ የኢኮኖሚ ጉባኤ አዘጋጅታለች። በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ የጂኦ ፖሊቲካ ቀውስ በጅቡቲ ውስጥ በጎ ያልሆነ ጥላ ማሳረፉን ገልፀዋል።

ይህ ክስተት ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋን መልከ ብዙ እንድታደርግ ግፊት ማድረጉን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ጅቡቲ በዓለም አቀፍ መድረክ የቀጣናው የንግድ መስመር ቁልፍ ተዋናይ ሆና እንድትቀጥል መንግሥታቸው ለቱሪዝም፣ ለፋይናንስ እና ለዲጂታል ዘርፍ ልማት ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል። ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ሰባት ሃገራት የየራሳቸውን ወታደራዊ የጦር ሠፈር የገነቡባት ጅቡቲ አብዛኛው የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ የሚሳለጥባት ቁልፍ ሀገር ናት።

ዋና ዋና መሠረተ ልማቷን ቻይና የምትገነባላት፣ የአረብ ሃገራት ኩባንያዎችና የመርከብ ድርጅቶች በስፋት የሚንቀሳቀሱባት ትንሿ ግን በቀይ ባሕር መስመር ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላት ጅቡቲ ዛሬ በዋና ከተማዋ ጅቡቲ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የትልልቅ ኩባንያዎች ባለቤቶች፣ አስተዳዳሪዎች እና የሥራ ኃላፊዎችን አሰባስባለች። ኤኮኖሚዋ በመሠረታዊነት ከወደብ አገልግሎት ኪራይ በሚገኝ ገቢ የተመሰረተው ወይም ጥገኛ የሆነችው ጅቡቲ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ፣ ቻይና ፤ ፈረንሳይ እና ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ጃፓን እና እንግሊዝ የጦር ሰፈር ገንብተውባታል።

ሀገሪቱ ዛሬ ባደረገችው ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት ያደረገ ጉባኤ መረጋጋት በተሳነው የአፍሪካ ቀንድ ከባቢ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ያላት መሆኑ፣ ይህም ለባለሃብቶች ሀብታቸውን በሀገሪቱ ፈሰስ የማድረግ ፍላጎት ይብልጥ መተማመን እንዲጨምር ማድረጉን፣ ከምንም በላይ የሀገሪቱ ገንዘብ የተረጋጋ መሆኑን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ጅቡቲ ኢኮኖሚዋን በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ የማሳደግ ውጥን መያዟም ተነግራል። ለዚህ ደግሞ በቀዳሚነት ጅቡቲን የቱሪዝም ማዕከል ማድረግ በሚል ለተያዘው እቅድ ሰፋፊ የባሕር ዳርቻዎች ለባለሃብቶች መዘጋጀታቸው ተነግሯል። የፋይናንስ ዘርፍን ማሳደግ እና የጨው ሃብትን በአግባቡ መጠቀምም በወደብ ገቢ ጥገኛ ለሆነው የሀገሪቱ ኢኮኖም አጋዥ እንዲሆኑ እይታ ውስጥ የገቡ እቅዶች መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ዑመር ጊሌ አብራርተዋል።

የጅቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጊሌ ባለሀብቶች በሀገራቸው መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ እንዲያለሙ ዓለም አቀፍ ጥሪ አቅርበዋል። ምስል፦ Solomon Muche/DW

«የጂኦፖሊቲካ ቀውስ በጅቡቲ ውስጥ በጎ ያልሆነ ጥላ አሳርፏል፣ ይኖረዋልም። ይህ ኢኮኖሚዋንም መልከ ብዙ እንድታደርግ እና በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ሆና እንድትቀጥል፣ ከውጭ የሚመጡ አደጋዎችን የመቋቋም አቅሟን እንድትፈጥር አድርጓል።»

አፍሪቃ ፣ አውሮጳ እና ኤስያ የሚገናኙበት የቀይ ባሕር፣ በተለይም የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ሥር የምትገኘው ጅቡቲ ኢኮኖሚዋ ላለፉት ሃያ ዓመታት በ 5.6 በመቶ ማደጉን ሀገሪቱን ለረጅም ዓመታት የመሯት ኢስማኤል ዑማር ጊሌ ለተሰብሳቢ ባለሃብቶች ነግረዋል። የየትኛውም ሀገር ገንዘብ በነፃነት የሚመነዘርበት ዕድል መፈጠሩም የራሱን በጎ ተጽእኖ ማሳደሩን አመልክተዋል።

«በአፍሪቃ እና በእስያ መተላለፊያ መንገድ ላይ የምንገኝ እንደመሆናችን፣ የስዊስ ካናል እና የአውሮጳ መገናኛ መስመር ላይ ያለን እንደመሆናችን እና የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ጠባቂዎች እንደመሆናችን፤ ጅቡቲ በዓለም የንግድ ልውውጥ ሥርዓት ውስጥ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ነው ቀጣናዊ ማዕከል ለመሆን የሚያስችሉንን የሎጅስቲክስ፣ የወደብ እና የዲጂታል ገበያ ልማትን ለማስፋፋት የሚያስችል የተለጠጠ ራዕይ ያቋቋምነው።»

ጅቡቲ ከተማ ውስጥ በተደረገውና እስከ ነገ በሚቀለው ጉባኤ በአልሚዎች ዘንድ ትብብርን እና ስምምነትን ለማመቻቸት ታቅዷል። እስከ 30 ዲግሪ ሞቃታማና ወበቃማ የአየር ጠባይ ሁኔታ ያላት ጅቡቲ ዓይን በተገለጠበት ሥፍራ ሁሉ የቀይ ባሕር ዳርቻዎች ላይ የተገነቡ ቤቶች፣ ግዙፍ ዕቃ ጫኝ መርከቦች፣ አነስተኛ ጀልባዎች ይታያሉ።

ከአንድ እና ሁለት ዓመት በፊት ሀገሪቱን ማየታቸውን የገለፁ ያነጋገርኳቸው ሰዎች፣ በሀገሪቱ የሥራ ባህል እና ተነሳሽነት ብዙ የሚቀረው ቢሆንም በመሠረተ ልማት ዝርጋታ መሻሻል እየታየባት መሆኑን ገልፀዋል። 

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW