1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ጆ ባይደን ከፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ፉክክር ወጡ

ሰኞ፣ ሐምሌ 15 2016

ጆ ባይደን ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ፉክክር ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ፣ ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ ከዲሞክራቶች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ እየተቸራቸው ነው። ባይደን፣ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ሆነው መመረጣቸውን ላለመቀበልና ሙሉ ኃይላቸውን በቀሪው የፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ለማዋል መወሰናቸውን ያስታወቁት በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ነዉ።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፤ ለቀጣይ ፕሬዚደንትነት ምርጫ እንደማይወዳደሩ ገለፁ
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፤ ለቀጣይ ፕሬዚደንትነት ምርጫ እንደማይወዳደሩ ገለፁ ምስል Caitlin Ochs/REUTERS

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፤ ለቀጣይ ፕሬዚደንትነት ምርጫ እንደማይወዳደሩ ገለፁ

This browser does not support the audio element.

ጆሴፍ ባይደን ከፕሬዚዳንታዊ ዘመቻው መውጣታቸው  

ጆሴፍ ባይደን ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ፉክክር ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ፣ ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ ከዲሞክራቶች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ እየተቸራቸው ነው። ባይደን፣ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ሆነው መመረጣቸውን ላለመቀበል እና ሙሉ ኃይላቸውን በቀሪው የፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ለማዋል መወሰናቸውን፣ትላንት በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ለዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል። የ81 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን፣እዚህ አትላንታ ጆርጂያ በሚገኘው የሲኤንኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የምርጫ ክርክር፣ዐሳባቸውን ለመግለጽ ተስኗቸው ሲደነቃቀፉ ከታዩ በኋላ ከምርጫው እንዲወጡ ከየአቅጣጫው ጫና ሲደረግባቸው ቆይቷል። እርሳቸው ግን፣ግድየለም ከዕድሜ መግፋት ጋር ጥበብ ይመጣል እያሉ እስከመጨረሻው ለመቆየት ሲታገሉ ቆይተዋል።

የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ

በኋላ ግን፣በኮቪድ ተይዘው ዴልዌር በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እያገገሙ ባለበት ሁኔታ፣በፕሬዚዳንትነት ለመመረጥ ሲያካሂዱ የነበረውን የምርጫ ዘመቻን ማቋረጣቸውን ይፋ አድርገዋል። የሚጠበቅ ግን ደግሞ አንዳንዶችን ድንጋጤ ላይ የጣለው ውሳኔያቸውን ባይደን፣" ለፓርቲዬ እና ለሃገሬ  የተሻለ ጥቅም ነው።" በማለት ገልጸውታል። ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ሆነው መመረጣቸውን ላለመቀበልና ሙሉ ኃይላቸውን በቀሪው የፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው፣ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ለማዋል ወስኛለሁ ነው ያሉት ባይደን። ፕሬዚዳንቱ፣ከምርጫው ለመውጣት መወሰናቸውን በተመለከተ፣በዚህ ሳምንት ውስጥ ለአሜሪካ ሕዝብ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ነገር ግን፣የሪፐብሊካኑ ዕጩ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ባይደን ለምርጫ መወዳደር ካልቻለ፣ ሃገራችንን መምራት አይችልም በማለት ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል። 

ባይደን ሃሪስን መደገፋቸው

ባይደን፣አንድ ሆነን ትራምፕን የማሸነፊያ ጊዜው አሁን ባሉበት መልዕክታቸው፣የፓርቲያቸውፕሬዚዳንታዊ ዕጩ እንዲሆኑ ሙሉ ድጋፍ የሰጧቸው ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ፣ከበርካታ የፓርቲዎው ሰዎች ድጋፍ እየጎረፈላቸው ይገኛል። ለፓርቲው የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍም እየጨመረ መጥቷል።  የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወሰን ቁልፍ ናቸው ከሚባሉት ግዛቶች አንዷ በሆነችው ኤሊኖይስ፣ ለረጅም ዓመታት የኖሩትና  የፖለቲካ ኤኮኖሚ ባለሙያው ፕሮፌሰር ተሾመ አበበ፣ የዲሞክራቲክ ፓርቲው አባል ናቸው። ስለ ባይደን ውሳኔ እና ስለ አሜሪካ ምርጫ ሂደት ጠይቀናቸው፣የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተውናል።

"የአሜሪካ ምርጫ ጉዳይ አሁን ትንሽ የተደበላለቀ ይመስላል።ነገር ግን ወደ ኋላ ሄደን ብናየው የዛሬ አራት ዓመት ምርጫ በተደረገበት ጊዜ፣ፕሬዚዳንት ባይደን ወጣት አለመሆናቸውን ማንም ሰው ያውቅ ነበር።በዚህ ምክንያት ነው ካማላ ሃሪስን ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው ያስቀመጡት። ይሁን እንጂ ከዛሬ ሦስት ሣምንት በፊት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በተደረገው ክርክር፣ ብዙ ድክመት ታይቶባቸዋል፤ድክመቱንም ለመሸፈን አልተቻለም።ባይደን ያጠፉት አንድም ነገር የለም፣ የተሳሳቱበት  ነገር የለም፣ ነገር ግን እንደ ሁሉም ሰው ዕድሜ ነው ያስቸግራቸው።" የጆሴፍ ባይደን ውሳኔ ትክክለኛ እርምጃ ቢሆንም፣ዘግይቷል የሚሉ በርካታ የዲሞክራሲ ፓርቲው መራጮችም አልጠፉም።

የዴሞክራቲክ ፓርቲው አንድነት

ኘሮፌሰር ተሾመ፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲው አባላት አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ መሆን ያለባቸው ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ። "የዲሞክራቲክ ፓርቲው አባላት፣አሁን አንድ መሆን አለባቸው።አንድ ለመሆን ደግሞ ከሴትዮዋ ጋር እንደግፋለን ማለት አስፈላጊ ስለሆነ ሁሉም ሰው ድጋፍ ካማላ ሃሪስ ማሸነፍ ስለማትችል የሚተባበሩ ይመስለኛል። ይሄ ግን ማንን ምክትል አድርጋ እንደምታስቀምጥ ወሳኝ ነው። እሷ ምክትል አድርጋ የምታስስበው ሰው ወሳኝ ይመስለኛል።እና እርሷ የምትመርጠው እርሷ ምክትል አድርጋ የምታስበው ሰው ወሳኝ ይመስለኛል።የእርሷ ድጋፍ በእዛ ላይ ተመሰረተ የሚሆን ይመስለኛል።በዛሬና በዛሬ ሁለት ሦስት ሣምንት በሚደረገው ጉባዔ መኻከል ብዙ ነገሮች እንደሚደረጉ ብዙ ውይይቶች እንደሚደረጉ እንጠብቃለን።"

ወላጆቻቸው ከህንድና ከጃማይካ የሆኑት የቀድሞ ዐቃቤ ህግ ካማላ ሃሪስ፣የፕሬዚደንትነት ዕጩነቱን ለማግኘትና ትራምፕን ለማሸነፍ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣በርካታ የአገር መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች፣ ባይደንን አወድሰው መልዕክት በማስተላለፍ ላይ ናቸው። ከነዚህም መኻከል፣ቁልፍ የምዕራቡ ዓለም አጋራቸው የሆኑት የጀርመኑ መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ፣"ባይደን ለሃገሩ፣ለአውሮፓና ለዓለም ብዙ አሳክቷል።" ብለዋቸዋል።

 

ታሪኩ ኃይሉ

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW