የገራዶ ተፈናቃዮች «ለልማት በሚል» ዳግም መፈናቀላቸው
ረቡዕ፣ ግንቦት 20 2017
በአማራ ክልል ደቡበ ወሎ ዞን «ገራዶ» በተባለ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች «ተለዋጭ ቦታ ሳይዘጋጅልን አካባቢው ለባለሀብት ተስጥቷል በሚል መኖሪያ ድንኳናችን እየፈረሰብን ነው» አሉ ። የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት «ችግሩ መፈጠሩን አረጋግጫለሁ» ብሏል ። የደሴ ከተማ አስተዳደር በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጥ ጥረት ቢደርግም ከንቲባው ምላሽ ለመስጠት አልፈለጉም ።
ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በ2014 ዓ ም ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን "ገራዶ” በተባለ አካባቢ ሰፍረው የነብሩ ከ700 በላይ ተፈናቃዮች "ቦታው ሌላ አካል ተሰጥቷል” በሚል ተለዋጭ መጠለያ ሳይዘጋጅላቸው መጠለያቸው ቦታውን በተሰጠው አካል እየፈረሰ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን ተፈናቃዮች መካከል አንዷ "ወደ 13 የተፈናቃይ መጠለያ ቤቶች ፈርሰዋል” ነው ያሉት፡፡
የተፈናቃዮች ተጠሪ አቶ ይመር ለገሰ የባለሀብቱ ተወካይ ቦታው ለልማት ይፈለጋል በሚል መጠለያዎችን በማፍረስ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ መፍርሔ እንዲፈለግ የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባን ትናንት ለማናገር ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው አመልክተዋል፡፡
"ለተፈናቃዮቹ ተለዋጭ ቦታ አልተሰጣቸውም” የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል ጽ/ቤት
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ መሐምድ ሰኢድ ከተማ አስተዳደሩ እርማጃውን ሲወስድ ተለዋጭ ቦታ ማዘጋጀት እንደነበረበት ጠቁመው፣ ተፈናቃዮቹ "ቦታውን ልቀቁ” በመባላቸውና መኖሪያቸው እየፈረሰባቸው ስለመሆኑ ተፈናቃዮቹ አቤቱታ ለጽ/ቤታቸው ማመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
«የተፈናቃይ መጠለያ አላፈርስኩም» ባለሀብት
ቦታው በመንግሥት እንደተሰጠው የገለፀልን የገራዶ ዶሮ እርባታና እንስሳት መኖ ድርጅት ኃላፊ አቶ ኢብራሒም አደም፣ ቦታውን ከወሰዱት ዓመታት እንዳለፈው ጠቁመው፣ በሰሜኑ ጦርነትና ቀደም ሲል ደግሞ በአካባቢው በነበሩ አለመረጋጋቶች ወደ ለማት ሳይገቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁን ወደ ለማት ለመግባት ቦታው መለቅቀ ስላለበት ተፈናቃዮች ቦታውን እንዲለቁ ማሳሰባቸውን አመልክተው፣ መኖሪያቸውን ግን እንዳላፈረሱባቸው ተናግረዋል፣ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ማነኛውም እንቅስቃሴ ለማገዝ ደግሞ ዝግጁ እንደሆኑ አቶ ኢብራሂም አስረድተዋል፡፡
ጉዳዩን አስመለከተን ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ብንደውልም በመጀመሪያው ቀን ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ገልፀዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በተለያዩ ቀናት በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም አያንሱም፣ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ብንልክም ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡
በአማራ ክልል 37 የተፈናቃይ መጠለያዎች ሲኖሩ ከ600 ሺ በላይ ደግሞ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ