1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ገዳዩ የማርበርግ ተሃዋሲ ስጋትና ሳይንሳዊ የምርምር ተስፋው

ረቡዕ፣ ነሐሴ 18 2014

ከአፍሪቃዊቷ ዩጋንዳ በተለምዶ «አረንጓዴ ጦጣዎች» ከሚባሉ ወርቃማ አረንጓዴ የሆነ የቆዳ ጸጉር ቀለም ያላቸው፤ የአደገኛው የማርበርግ ተላላፊ ተሃዋሲው ተሸካሚ ከሆኑ የጥንት ዘመን የጦጣ ዝርያዎች ተሰራጨ የተባለው ማርበርግ ተሐዋሲ ስያሜውን ያገኘው ከጀርመኗ ማርበርግ ከተማ ነው። ተሐዋሲው ለመጀመሪያ የተገኘውም በከተማዋ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ነው።

Marburg-Virus
ምስል፦ Bernhard-Nocht-Institut/Bni/dpa/picture alliance

ሳይንስ እና ቴክኒዎሎጂ

This browser does not support the audio element.

በምዕራብ ጀርመን ሄሰን ክፍለ ግዛት ከቱሪስቶች መናኸሪያዋ ፍራንክፈርት 77 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው ማርበርግ ከተማ እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በነሐሴ ወር 1967 ዓ.ም በአንድ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የምርምር ቤተሙከራ ያጋጠመው ክስተት በወቅቱ ዓለምን ክፉኛ ያስደነገጠ ነበር:: ከአፍሪቃዊቷ ዩጋንዳ በተለምዶ «አረንጓዴ ጦጣዎች» ከሚባሉ ወርቃማ አረንጓዴ የሆነ የቆዳ ጸጉር ቀለም ያላቸው፤ የአደገኛው የማርበርግ ተላላፊ ተሃዋሲው ተሸካሚ ከሆኑ የጥንት ዘመን የጦጣ ዝርያዎች ተሰራጨ የተባለው ይህ ወረርሽኝ የምርምር ቤተ ሙከራው የጤና ባለሙያዎችን፣ አስታማሚ ቤተሰቦቻቸውንና ከእነሱ ጋር ንክኪ የነበራቸውን 32 ያህል ሰዎች በዛው በማርበርግና ፍራንክፈርት ከተሞች ማጥቃቱ ይፋ ሆነ::

 በወቅቱ በተሃዋሲው ከተጠቁት ህሙማን ሰባቱ ወዲያው ሕይወታቸው ሲያልፍ በአካላቸው ውስጥ የሚገኝ ፈሳሽና ደም በሰውነታቸው ቀዳዳ እና በዓይናቸው ጭምር ያለማቋረጥ መውጣቱ እንዲሁም ግሉኮስ ለመስጠት እና የደም ናሙና ለመውሰድ መርፌ በተወጉበት የደም ሥራቸው ሳይቀር ደም ፈሶ ለሞት መዳረጋቸው ዓለምን ክፉኛ ድንጋጤ ውስጥ የከተተ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል:: ተሃዋሲው ብዙም ሳይቆይ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ቤልግሬድ ከተማ በአሁኗ የሰርቢያ ግዛት ተስፋፍቶ የሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ተነገረ:: እንደ ሌሊት ወፍ ያሉ እንስሳትም የማርበርግ ተሃዋሲ ከፍተኛ ተሸካሚ መሆናቸውን  በ2018 ዓ.ም የተደረገ ጥናትን ዋቢ አድርጎ የገለጸው የአሜሪካው ቦስተን ዩኒቨርሲቲ የምርምር ተቋም፤ በተለይም ሮሴቱስ ኢጂፕቲከስ የሚባሉት የግብጽ የፍራፍሬ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች ተሃዋሲው የሚያደርሰውን ጉዳት የመከላከል አቅም እንዳዳበሩ ጠቅሷል::

ዶክተር ስንታየሁ አሰፋምስል፦ Endalkachew Fekade/DW

ማርበርግ ተሃዋሲ በአንዳንድ ጥናቶች ብዙ ደም እንዲፈስ የሚያደርግ የትኩሳት /Marburg hemorrhagic fever/ በሽታ መሆኑ ይጠቀሳል:: ተሃዋሲው ስያሜውን ያገኘው ወረርሽኙ በዜጎቿ ላይ የሞት አደጋ ካስከተለ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ስለ ተሃዋሲው ይፋ ባደረገችው የጀርመኗ ማርበርግ ከተማ ነው:: በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን ፈሳሽና ደም በህሙማኑ አካል ላይ በሚገኝ የቀዳዳ ክፍል ፈሶ እንዲወጣ በማድረግና የውስጥ የሰውነት ክፍሎችን ከጥቅም ውጭ አድርጎ ሕይወትን የሚቀጥፉት ኤቦላም ሆነ ማርበርግ "ፊሎቪርዴ" ወይም "ፊሎ ቫይረስ" የተሰኘው ተመሳሳይ ተሃዋሲ ዝርያ ቤተሰቦች መሆናቸው ይጠቀሳል:: ለመሆኑ ላለፉት 55 ዓመታት ፈውስ የሚሰጥ መከላከያ ህክምና መድሃኒት አልያም ክትባት ያልተገኘለትና በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ጭምር አሳሳቢ አደገኛና ገዳይ ተብለው ከተመዘገቡ ወረርሽኞች ተርታ የተመደበውን የማርበርግ ተሃዋሲ ወረርሽኝ ለመከላከል ላለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት የጤና ባለሙያዎች ምን ዓይነት ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር አከናውነዋል? የተገኘ አጥጋቢ ውጤትስ ይኖር ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ዛሬም ድረስ ብዙዎች ደጋግመው ያነሱታል:: ተሃዋሲው ስለሚያሳያቸው የበሽታ ምልክቶች እንዲሁም ምልክቶቹ ከታዩ መወሰድ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች የባለሙያ ማብራሪያ ያካተተውን የሳይንስ እና ቴክኒዎሎጂ መሰናዶ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ::

እንዳልካቸው ፈቃደ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW