1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርትጀርመን

ገፍተው አይሄዱ ችግር ፤ ወጣቶቹን የነጣጠለው የሕይወት ፈተና

ዓርብ፣ ሐምሌ 8 2014

«የተሰበረው ጀልባ ውስጥ ገብቶ እግሬን ይዞኛል መሰል እንዳለ እግሬ ቆስሎ ነበር ፤ እስካሁን ድረስ ራሱ አለ እና በጣም ቆስሎ ነበረ፤ ግማሹ ጓደኞቼ አብዛኛው እግራቸው የተሰበረው ጀልባ ውስጥ ተቀርቅሮ ነበር። ሰው ሰው ላይ ሲጫጫን ደግሞ የተሰበሩ ሰዎች አሉ። መተንፈስ አቅቷቸው ራሳቸውን የሳቱ ሰዎች ነበሩ።» ከጀልባው አደጋ በኋላ ከተናገረችው።

የሶስቱ ሩቅ አዳሪ ወጣቶች ህልም እና የሕይወት ጉዞ

This browser does not support the audio element.


«የተሰበረው ጀልባ ውስጥ ገብቶ እግሬን ይዞኛል መሰል እንዳለ እግሬ ቆስሎ ነበር ፤ እስካሁን ድረስ ራሱ አለ እና በጣም ቆስሎ ነበረ፤ ግማሹ ጓደኞቼ አብዛኛው እግራቸው የተሰበረው ጀልባ ውስጥ ተቀርቅሮ ነበር። ሰው ሰው ላይ ሲጫጫን ደግሞ የተሰበሩ ሰዎች አሉ። መተንፈስ አቅቷቸው ራሳቸውን የሳቱ ሰዎች ነበሩ።»

«በጣም ልብ ይሰብራል፤ ተመለስን፤ ምንም ማድረግ የምንችለው ነገር ስላልነበር ወደ ጫካ ተመለስን እና አዕምሯችን ያንን አስቦ አልመጣም ፤ ማደርን እዚያ መቆየትን ፈጽሞ አናውቀውም  ። እንዳልኩህ ነው ፤ እንነሳለን እንወጣለን የሚለው ነገር ብቻ ነው አዕምሯችን ውስጥ የነበረው። » እነዚህ ድምጾች ባለፈው የሰኔ ወር መጀመሪያ አካባቢ ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ ሊሻገሩ ሲሉ የጀልባ አደጋ ያጋጠማቸው እና በህይወት ተርፈው ታሪካቸው ያካፈሉን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ናቸው። 
ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን ይህ የከወጣቶች ዓለም ዝግጅታችን ነው ለትምህርት ወጥተው ወደ እንግሊዝ በጀልባ ለመሻገር ሙከራ ሲያደርጉ የጀልባ መስጠም አደጋ የገጠማቸውን እና ከአደጋው የተረፉትን 3 ወጣቶች ታሪክ ያካተትንበትን ዝግጅት ይዘናል።
ሶስት ናቸው። በተመሳሳይ የህይወት መስመር ላይ የተገናኙ፤  ህልማቸው ተቀራራቢ ፣ ነገአቸውን ዛሬ መስራት ፣ የተሻለ ተስፋ የሰነቁ ፤ ወደ ፊት መራመድን ርዕያቸው ያደረጉ ።   ሶስቱም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በፖላንድ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ዕድል አግኝተው የመጡት በተለያዩ ዓመታት ነው። ነገር ግን ሶስቱን አንድ ነገር ያሳስባቸዋል። የትምህርት ዕድል የሰጠቻቸው ሀገር ፖላንድ ትምህርቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ሀገርቤት እንደምትመልሳቸው ያውቃሉ። ይህ ለእነርሱ የሚታሰብ አይደለም ።
 ለደህንነታቸው ስንል ስማቸውን ቀይረን ታሪካቸውን የምናካፍላችሁ ወጣቶች በፖላንድ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ናቸው። ሃና ከሐዋሳ ፣ ስምረት ከጅማ ፤  ኃይማኖት ደግሞ ከአዲስ አበባ ከፖላንድ ዩኒቨርሲቲዎች ባገኙት የትምህርት ዕድል ወደ ፖላንድ በማቅናት ትምህርት እና ስራን ጎን ለጎን ሲያስኬዱ ቆይተዋል። ሃና የሶስተኛ ዓመት ፣ ስምረት እና ኃይማኖት ደግሞ የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች ናቸው። 
ወደ እንግሊዝ መሻገር፤ ወደ እንግሊዝ መሻገር ፤ በፖላንድ የሚገኙ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ሕልም ነው ፤ ግን ደግሞ ብርቱ ፈተና ውስጥ ማለፍ የሚጠይቅ ፤ ምናልባትም እስከ ህይወትን ሊያሳጣ የሚያደርስ ብርቱ ውሳኔ የሚጠይቅ ፤ አልፎም ጊዜ ፣ ገንዘብ እና ጽናት የሚጠይቅ ሃሳብ ። 
ከዓመት በላይ የዝግጅት ጊዜ በጠየቃቸው ከፖላንድ እንግሊዝ የመሻገር ፍላጎት አንዳቸውም ባህር ላይ የመስጠም አደጋ ያጋጥመናል ብለው አስበው አያውቁም። እስቲ ታሪካቸውን ነጣጥለን እንይ ። 
ስምረት የመጣችለት ዓላማ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን መከታተል፤ ጎን ለጎን ስራ መስራት ፤ ራሷን መደጎም በቻለችው አቅም ደግሞ ቤተሰቦቿን መርዳት ነበር። ነገር ግን ዛሬ መልስ የሚያሻት አንድ ጥያቄ አለባት ።ለእርሷ ትምህርቴን ካጠናከኩ በኋላ ምን እሆናለሁ ? የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ነበረበት። ምክንያቱም በፖላንድ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ መጡበት ሀገር የመመለስ ግዴታ ስላለባቸው ። ብቸኛው አማራጭ ደግሞ እንደእነርሱ ብዙ አማራጮች አሉ ብለው ወደሚያምኑባት የእንግሊዝ ምድር መግባት።
« ምን አለ መሰለህ፤  ስትኖር ዛሬን ብቻ አይደለም እያሰብክ የምትኖረው፤ በጣም አድርገህ ነው የምታስበው ፤ የወደፊትህን ታስባለህ እና እኛ እዚህ የምንማረው ገንዘብ እየከፈልን ነው። ያን የምንከፍለውን ነገር ደግሞ ቤተሰብ ይክፈልልን ማለት በጣም ከባድ ነው ። ያን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለው እዚህ ልከውን ቤተሰብህን አትጠይቅም ። በዚያው ልክ ደግሞ ያንኑ ማድረግ የማ ይችሉ ቤተሰቦች አሉ። እና ምንድነው የምታስበው እንግሊዝ ብትሔድ በነጻነት ትማራለህ፣ ሁለተኛ ወረቀት የማግኘት ዕድል አለህ ። እዚህ ግን ትማራለህ ፤ ተምረህ ከጨረስክ በኋላ ያለው ህይወት ደግሞ ሌላ ነው። ትቆይ አትቆይ የምታውቀው ነገር የለም። እዚህ ሀገር በህጋዊ መንገድ ልትቆይ የምትችለው ትምህርት እስኪያልቅ ብቻ ነው። »
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአንደና ዓመት ትምህርቷን አቋርጣ ወደፖላንድ የመጣችው እና ለደህንነቷ ስንል ስሟን የቀየርነው ሃናም ፖላንድን ለቃ ወደ እንግሊዝ ለማቅናት የተነሳችው ዘላቂ መኖሪያ እና የተረጋጋ ህይወትት ለመኖር ከመሻት የመነጨ እንደሆነ ነው የምትገልጸው።  
« ያው ተረጋግቶ ለመኖር ነው ። አሁን እዚህ ተምረን ከዚያስ ምን እንሆናለን ብለን በጣም ነው የምንጨነቀው ። ተምረን ጨርሰን በወረቀታችን እዚሁ ይቀጥሩናል አይቀጥሩንም የሚለው ነገር ያስጨንቃል። ሌላው ደግሞ ቋንቋው በራሱ እዚያ ብንሄድ የምንግባባበት ነው። የውጭ ዜጎች እዚያ በስፋት ስላሉ ማለት ነው። የውጭ ዜጎች እዚህ ቢኖሩም እንደዛ አይሆኑም። ዞሮ ዞሮ የተረጋጋ ኑሮ ለመኖር ነው ።»
ያለፉትን ሁለት ሶስት ዓመታት በፖላንድ ያሳለፉት ወጣቶቹ ከፊታቸው ያለው ጊዜ በእርግጥ የሚያረጋጋ ሆኖ አላገኙትም። በቋንቋ ተግባብተው ፤ ትምህርታቸውን ከመግፋት በተሻገረ የተሻለ ስራ ሊያገኙ ወደ ሚያስችል ምድር ማቅናት ፤ ለጊዜው ለበርካቶቹ ኢትዮጵያውያን መዳረሻነት የተመረጠችው አውሮጳዊቷ ታላቋ ብሪታኒያ ሆናለች። ባህር መሻገር የህይወት ፈተና አንድ፤  ሀገሪቱ ስደተኞችን ወደ አፍሪቃ የማጓጓዝ ዕቅድ ሌላ ብርቱ ፈተና ሁለት። ለዚያውን ወደ እነዚህ መዳረሻዎች ለመድረስ የሚታለፉ ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን በርካታ ስደተኞችን ለዘማናት የተፈታተኑ ፈተናዎች እንደተጠበቁ ሆነው። 
ከፖላንድ ወደ እንግሊዝ ለመሻገር  ሲነሱ ስድስት ሆነው እንደተነሱ የምትናገረው ሃና ፖላንድ ውስጥ ሕጋዊ ሆነው መኖራቸው ያለአንዳች ችግር ፈረንሳይ እንዲገቡ እንዳስቻለቸው ነው።
« ከዚህ ስንነሳ ከስድስት ጓደኞቼ ጋር ነው። ስድስቱም እንደ እኔ በትምህርት ነው የመጡት ። እና እስከ ፈረንሳይ ስንሄድ ቪዛ ስላለን ቀጥ ብለን ነው የገባነው ። ምንም ያስቸገረንም ነገር የለም። ትንሽ የከበደን ከፈረንሳይ በኋላ ጫካ ውስጥ ገብተን ስላለው ነገር ነው። እንጂ ፈረንሳይ እስክንደርስ ድረስ ሁሉ ነገር ጥሩ ነበር። »
  አዎ የህይወት ግብ ግቡ አሁን ይጀምራል። አብዛኞቹን ተሰዳጅ ኢትዮጵያውያንን እንደሚያጋመው ሁሉ የሞት ሽረት ፈተና ከፊት ተደቅኗል። ከጂቡቲ ተነስተው በጀልባ ቀይ ባህርን አቆራርጠው በየመን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት እንደሚደረገው ጉዞ ፤ በሱዳን ሊቢያ ከዚያም በጣሊያን ወደ ተቀረው የአውሮጳ ክፍል ለመድረስ ከሞት ጋር ግብግብ እንደሚደረግበት የባህር ላይ ጉዞ ሁሉ ፤ አውሮፓም ተደርሶ ተደረሰ አይባልም ። አንዱ የደረሰበት ሌላው የሚናፍቀው የሕይወት መንገድ  እንዲህም አይደል ? ሃና እና ጓደኞቿ ወደ እንግሊዝ ለመሻገር ፖላንድ ውስጥ የቋጠሯትን ጥሪት ይዘው ለደላላ ከፍለው ባህሩን ሊሻገሩበት ወደ ሚያስችላቸው የፈረንሳይ የድንበር አካባቢ መጥተዋል።
ስምረት የገጠማትን ትናገራለች።
 «ይኼ ስራ እየተሰራ ያለው ደንኪር ውስጥ ነው ፤ ወደ ደንኪር ነው የሄድነው ማለት ነው። ደንኪር ከሄድን በኋላ ቦታው ጫካ ነው። እዚያ ቁች ብለህ ነው ሙከራ አለ ተነሱ ይላሉ ፤ አረቦች አሉ ደላሎች ፤ ሀበሻም ደላሎች አሉ፤ ሁሉም ደግሞ ደረጃ አላቸው። ከእና ጋር ግንኙነት ካደረጉት በላይ ደግሞ ሌሎች ትልልቆች አሉ፤ ከእነርሱ ጋር አትገናኝም እና እነዚህ አረቦች ናቸው እየመጡ የሚያሰማሩት ። ተነሱ ሲሉ ትነሳለህ ተቀመጡ ሲሉ ትቀመጣለህ። አንድ ግዜ ከፍለህ ገብተሃል። እና የምትከተለው የእነርሱን ህግ ነው።»
ይህ ከፈርንሳይ ወደ እንግሊዝ የሚደረጉ የስደተኞች ፍልሰት በ,ተለይ በአውሮጳውያኑ የበጋ ወራት አይሎ እንደሚስተዋል ይነገራል። ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ መዳረሻቸውን እንግሊዝ ለማድረግ በዚያ ስፍራ የደረሱ ሁሉ ገንዘብ እስከ ከፈሉ ድረስ ተራቸውን ጠብቀው አስፈሪውን ዕድል ይሞክራሉ ። በአየር በሚሞላ የፕላስቲክ ከረጢት ጀልባ የተሳካላቸው ይሻገራሉ፤ አልያም ህይወታቸውን እስከማጣት የሚያደርስ አደጋ ሊያጋጥማቸውም ይችላል። ስደተኛው ያልፋል፤ ስደተኛው ይሻገራል። ይህ የስደት ዓለም የተለመደ ህይወት ነው። 
ዕድል አይነት አላት ሃና ከ2100 በላይ ዩሮ በሰው ከከፈሉ በኋላ ወዲያው የሚያሻግራቸው ማግኘታቸው እንደ ዕድለኛ እንዳደረጋቸው ትናገራለች። ለመጀመሪያ ቀን ያደረጉት ሙከራ ጀልባ የለም ተብለው ቀርተዋል። በሁለተኛው ሙከራቸው ግን ስድስቱ ጓደኛሞች  ከፊታቸው ስለተጋረጠ ብርቱ ፈተና እና የህይወታቸው ምናልባትም እጅጉን አስጨናቂ ጊዜ ስለመድረሱ ልብ አላሉም። 
«  በዚህ አጋጣሚ እኛ እንዲሁም ዕድለኞች ሆነን ነው እንጂ አንድ ወር ሁለት ወር የተቀመጡ ሰዎች አሉ ። እየሞከሩ ሲመልሷቸው ፤ ተማሪዎች አሉ ፤ በጣም በጣም ነው የሚያስግረው ፤እና በማግስቱ ደግሞ ሄድን የአምስት ሰዕት የእግር ጉዞ ነው ያለው፤ ስትሄድ ከፖሊስ እየተደበቅክ ነው። ቻካው ውስጥ ቢያንስ ለሶስት ሰዓት ቁጭ አልን ጊዜው በጋ ስለሆነ እና ቶሎ ስለማይጨልም እስከሚጨልም ጠብቀን እርሱ ጊዜ በጣም በጣም የሚከብድ ጊዜ ነበረን። እንደምንም ብለን ውሃውጋ ደረስን። »
ባህሩጋ ከደረሱ በኋላ የአስጨናቂው ጊዜ መድረሱን ሁሉም በውስጡ ያውቀዋል። ግን ደግሞ ወደ ኋላ አይመለሱ ነገር ቆርጠው ተነስተዋል። ለጉዞ ከተሰናዱ በኋላ ከሌላ ቦታ የመጡ አረቦች እንደተቀላቀሏቸው የምትናገረው ስምረት የባህር ዳርቻውን የምሽት ትዕይንት እንዲህ ታስታውሳለች። 
« አረቦችም ነበሩ የተቀላቀሉን ፤ አናውቅም ስንወጣ እኛ 40 እንሆናለን ከሚነዱት ጋር ፤ ነገር ግን በዝተን 50 እንሆናለን በሰዓቱ  ። ከዚያ  ባህሩጋ ደረስን ፤  ሴቶቹን ለይተው ወደ ፊት አስጠጉን እና ወንዶቹን ግዴታ የፕላስቲክ ጀልባውን ሄደው ማምጣት አለባቸው። አንዳንዴ ተቀብሮ ይቀመጣል፤ አንዳንዴ ደግሞ በመኪና ይዘው ይመጣሉ፤ ቶሎ ጥለው አልፈው ይሄዳሉ። እና ወምንዶቹ  ነዳጅ እና እርሱን ተሸክመው ይመጣሉ። ወንዶቹን አንድ ላይ ሰብስበው ይሄን ያሰሯቸዋል። ሴቶቹ ደግሞ ተቀምጠን እንጠብቃለን። ከዚያ ሩጡ ተባልን ወደ ውሃውጋ ፤ እኛ እንሮጣለን ወንዶቹ ከኋላ እየሮጡ ይከተሉናል ማለት ነው ። ሞተሩን ካስተካከሉ በኋላ። ማለት ነው »
ብርሃን ለጨለማ ስፍራውን ሲለቅ ፤ ምድርም ስትጨላልም ያ የማይቀረው፣ የባህር ላይ ጉዞ ተጀመረ ። በአየር የተሞላችው የፕላስቲክ ጀልባ ፤ እንደ እነርሱ አባባል ለወትሮ ከአርባ በላይ ሰው የማይጫንባት ዛሬ ያለወትሮዋ ከሃምሳ በላይ ሰዎችን አችቃ ይዛለች። ቀጥሎ የተፈጠረውን ከ,ራሳቸው በጀልባ ላይ ከነበሩት አንደበት ብንሰማስ።
«ብቻ በጣም ብዙ ሰው ነበር ። ልክ ገና አስር ደቂቃ እንደሄድን ተሰበረ ማለት ነው። ሰው አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርቦ ሲዘል፣ ሲዘል ሃይለና ጩኸት ተፈጠረ። ግማሹ እግሬን ይላል ግማሹ እጄን ይላል፤  ከዚያ ጀልባው ይመለስ ተብሎ ሊመለስ ሲል ሞተሩ ጸጥ አለ። ከዚያ ወደ መሃል እየገባን ሄድን ፤ ንፋሱ ጀልባዋን ወደ ባህሩ መሃል እየገፋን ሄደ።»
«መጮህ ተጀመረ፣ አንዷ ውሃ እየገባ ነው አለች፤ እኔ ቁጭ ብዬ ነበር እና ውሃው ሞልቶ ወደ ደረቴ እየተጠጋ መጣ፣ ከዚያ ቁሙ ቁሙ ተባለ፣ ከዚያ ውሃው እየሞላ እየሞላ መጣ፤ኮምፐርሳቶው እየተሰነጠቀ መጣ፣ በጣም ብዚ ሰው ነው ያለው ፤ ሃምሳ አምስት ሰው ማለት አስብ አርባ ሰው በምትጭን ጀልባ ላይ፤ ሴቶች ይጮሃሉ ፣ ወንዶች ይጮሃሉ፤ በጣም ሄደናል ተጉዘናል፤ እንዴት ነው የምትይዘው የምትጨብጠው ነው የሚጠፋህ፤ መሬት ነው የሚናፍቅህ በዚያ ሰዓት ፤ማንም አይደርስልህም ፤ በቃ እዚያ ቦታ ፈጣሪህን ነው የምትለምነው። ስልክ ቢደወልም ማንም የሚመጣ ሰው የለም። » 
በህይወት እና በሞት መካከል የነበረው ግብግብ ለሁለት ሰዓታት ከዘለቀ በኋላ ፤ ተዓምር በሚመስል መልኩ የፈረንሳይ የነብስ አ,ድን መርከብ ደርሳ እንደታደገቻቸው ወጣቶቹ በግርምት ያወራሉ። የነብስ አድን ቡድኑ እንደገና ወደ  ፈረንሳይ ድንበር ሲመልሳቸው እውነት አልመሰላቸውም ፤ ሃና እና ስምረት ዳግም የባህሩን አይን ላያዩ ፣ ከዚህ ከተረፍን በእጃችን ባለ ዕድል እንጠቀም ሲሉ በመጡበት መንገድ ወደ ተነሱበት ፖላንድ ተመልሰዋል። እንደወጣቶቹ ከሆነ  ፖላንድ ለመመለስ ያደረጉት ጉዞም እንዲሁ ቀላል እንዳልነበረ ነው። ከእርዳታ ድርጅቶች ባገኟቸው አልባሳት ጫማ የተዳከመ ሰውነት ይዘው ፣ በእጃቸው ያለውን ሊያድሱ ።
ለደህነቷ ስንል ስሟን የቀየርነው እና የሁለቱ ተመላሽ ተማሪዎች ጓደና የሆነችው ሳራ ግን በፖላንድ የነበራት እህል ውሃ እንዳቃ በመረዳቷ ስድስት ሆነው ከወጡት ጓደኛሞች ከተቀሩት ጋር ያንኑ አስፈሪ የባህር ላይ ጉዞ እንደገና ለመጋፈጥ መወሰኗን ትናገራለች። 
«እኛው ነን የሰመጥነው፤ ከሰመጥን በማግስቱ ደግሞ ወደ ጫካ ተመለስን ከሰዓት ነው የወጣነው አልተኛንም ሁላ እንቅልፍ  ስንወጣ ተመልሰን ማለት ነው። ግን እንደዚህ አይነት ውሳኔ የሚያስወስንህ ምን እንደሆነ ታውቃለህ ? ሕይወትህን ኖረህ ነው አይደል ያየኸው ? ያ ህይወት እንደማይሆን ታውቃለህ። ፖላንድ ላይ ለምን አትመለሺም ብትለኝ እርሱ አይሆንም።» ባህር ላይ ያለው አደጋስ ? (በመሃል የተጠየቀ ጥያቄ ) ነገርኩህ እኮ ባህር ላይ ያለው አደጋማ እንድትመለስ ያደርግሃል። ፖላንድ ተመልሼ እንዳልሄድ ፖላንድ ጥገኝነት ካልጠየኩ በስተቀር ወረቀቴ የመጠቀሚያ ጊዜው አልፏል። አዲስ ወረቀት ለመጠየቅ ጌዜ ይወስዳል። ፈረንሳይ እጅ እንዳልሰጥ ደግሞ እንደዚያ ከውሃ ውስጥ አውጥተውን እነ ስምረት ነግረውሃል በባዶ እግራቸው ፣ ግማሹ ራቁቱን ፣ ሆኖ እሰሩን እንኳ ብንላቸው  አውጥተው ነው መንገድ ላይ የጣሉን ።» ህይወት እንዲህ ናት ስድስት ሆነው ወጡ ብርቱውን ፈተና አብረው ተፈተኑ  ፣ ሁለቱ ይብቃን ብለው በእጃቸው ላይ ያለውን ዕድል ለመጠቀም ሲመለሱ አራቱ ግን ሞት ቢመጣ ሊጋፈጡ ወስነው ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ እንግሊዝ መድረስ ችለዋል። ነገር ግን ሌላ ማዕበል ፣ ሌላ ፈተና ከፊታቸው አለ። የእንግሊዝ መንግስት ስደተኞችን ወደ ርዋንዳ የማጓጓዝ አስፈሪ ዕቅድ ። ከውሃው ማዕበል  የተረፉቱ እነዚሁ ሩቅ አዳሪዎች  ፤ በእርግጥ በአየር ጭኖ ከሚወስደውስ ይተርፉ ይሆንን ? ጊዜው ሲደርስ አብረን እናያለን።   

ምስል፦ Ben Stansall/AFP


ታምራት ዲንሳ


እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW