የጉሮሮ ህመም እና ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 27 2016
ሄለን ዘማርያ የዶቼ ቬለን የፌስቡክ ማለትም አሁን ሜታ በተባለው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ የቀጥታ ስርጭት ከሚከታተሉ የዘወትር አድማጮቻችን አንዷ ናቸው። የዘወትር አድማጫችን ከቀናት በፊት በዚሁ መድረክ «ጋዜጠኛ እህታችን ሸዋዬ እኔ ሁሌ ቀዝቃዛ ውሃ ስጠጣ፤ አይስክሬምም ሰበላ ጉሮሮዬን ያመኛል» በማለት ጠየቁ። የዘወትር አድማጫችንን በቅድሚያ ስለጉሮሮ ጤና በዚህ አጋጣሚ ከህክምና ባለሙያ ማብራሪያ እንድናፈላልግ ምክንያት በመሆናቸው እናመሰግናለን። ወደ እሳቸው ጥያቄ በቀጥታ ከማለፋችን በፊት የጉሮሮን ጤና ስለሚያውኩ ነገሮች ጥቂት እንበል። ከአንገት በላይ ያለው አካል ጤና የህክምና ባለሙያዎች ጉሮሮ ለምግብ መተላለፊያ አለያም ለመተንፈሻ እንዲሁም ስንነጋገርም ትልቅ ሚና ያለው የሰውነት ክፍል እንደመሆኑ የጉሮሮ ጤናጉዳይ በቀላሉ እንደማይታይ ነው የሚገልጹት። እነዚህን ሁሉ እጅግ ወሳኝ ተግባራት የሚያከናውነው የአካል ክፍል አንድ እንጂ ሌላ ተለዋጭ የሌለው መሆኑን በማስገንዘብም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ። ጉሮሮ በአልርጂ ማለትም በተለያዩ ነገሮች አለመስማማት ምክንያት በሚከተል መቆጣት ሊታወክ ይችላል፤ በተለያዩ ተሀዋስያን የመጠቃት አጋጣሚም ሲኖር እንዲሁ ጉሮሮ ይቆጣል እብጠትና መሰል ችግሮች ሊከተሉ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ከሰውነት ውስጥ ምናልባት የጨጓራ አሲድ ሊሆን ይችላል። አንዳንዴም በሳይነስና ጉንፋን የተጠቃ ሰው ወደ ጉሮሮው የሚመጣ ፈሳሽ የጉሮሮውን ጤና ሊያውክ እንደሚችል ነው ከዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ያገኘነው ማብራሪያ የሚያስረዳው። የአልክሆል መጠጥ አዘውትሮ መጠጣት፤ ትንባሆ ማጨስ፤ ጫት መቃምም ሆነ የመሳሰሉት ነገሮች የጉሮሮን ጤና ሊጎዱ እንደሚችሉ ዶክተር አደፍርስ ደባልቄ በየነ በዋነኛነት አንስተዋል።
ከዚህም ሌላ በተያዩ አደጋዎች ወይም አጋጣሚዎች አንገት ላይ የሚደርስ ጉዳት ጉሮሮን ለህመም እንደሚዳርግም አመልክተዋል። አንገት ላይ የሚያርፍ ምት በመኪና አደጋ ሊሆን ይችላል፤ ማጅራት መቺም አደጋ አድርሶ ሊሆን ይችላል በዚህ ጊዜ የጉሮሮ የመተንፈሻው አካል ሊዘጋ እና ሕይወትንም እስከማሳጣት ሊደርስ ስለሚችል እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች በቶሎ ወደ ሀኪም መሄድን የአንገት በላይ የህክምና ባለሙያው አሳስበዋል።
ወደ አድማጫችን ጥያቄ ስናልፍ «ሁሌ ቀዝቃዛ ውኃ ስጠጣ፤ አይስክሬምም ሰበላ ጉሮሮዬን ያመኛል» ነው ያሉን። የአንገት በላይ ከፍተኛ ህክምና ባለሙያው፤ እንደገለጹት ጉሮሮን ከተለያዩ ባእዳን ነገሮች የሚከላከለው የተፈጥሮ ሽፋን ቀዝቃዛ ነገሮችም በመጠጣትም ሆነ እንደ አይስኬሬም ያሉትንም በመመገብ ስለሚጎዳ ተገቢውን ሥራ ማከናወን ስለማይችል ህመም ሊፈጠር ይችላል። የጉሮሮ ህመም ቀላል ነው ተብሎ ችላ የሚባል እንዳልሆነ የገለጹት ዶክተር አደፍርስ፤ መተንፈስ እስከ መከልከል የሚደርስ ሕመም እንዳለና ያም ለህልፈተ ሕይወት ሊዳርግ እንደሚችልም አመልክተዋል። ሙሉ ጥንቅሩን ለማድመጥ የድምፅ ማይቀፉን ይጫኑ።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ