1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጉደይኦን፤ አሰሪ እና ሰራተኛን የሚያገናኘው ዲጅታል የስራ ገበያ

ረቡዕ፣ የካቲት 29 2015

ይህ መተግበሪያ ስራ ፈላጊን ከቀጣሪ ጋር ለማገናኜት የሚያገለግል ሲሆን፤ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሴቶች ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል።የመተግበሪያው ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትግስት አፈወርቅ እንደሚሉት በዲጅታል መድረኩ በብዛት የሚፈለጉ ሴት ሰራተኞች ቢሆኑም እስካሁን ተጠቃሚ የሆኑት ግን 30 በመቶ ብቻ ናቸው ።

GoodayOn application
ምስል፦ Tigist Afework

አሰሪ እና ሰራተኛን የሚያገናኘው መተግበሪያ

This browser does not support the audio element.

 
ዲጅታል ፈጠራ እና ቴክኖሎጅ ለጻታ እኩልነት በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዛሬው ዕለት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እየተከበረ ነው።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሴቶች ስራ በማፈላለግ  የሚያግዝ መተግበሪያን ያስተዋውቃል።
የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ህይወት ለማቃለል እና ችግሮችን ለመፍታት በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጅ በተለይም መተግበሪያዎች የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች  90 በመቶ የሚሆነውን ጊዜ መተግበሪያዎች ላይ ያሳልፋሉ። ምክንያቱም መተግበሪያዎች ጊዜ እና ጉልበት በመቆጠብ እንዲሁም ጥገኛ ሳይሆኑ ባሉበት  ቦታ ሆኖ ስራን ለማከናወን ተመራጭ ቴክኖሎጅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በኢትዮጵያም መረጃ ለማግኘት፣ ለግብይት፣ ለመዝናኛ፣ ለትምህርት እና ለእርሻ ስራ የሚያገለግሉ የተለያዩ መተግበሪያዎችን የማበልፀግ ጅምሮች አሉ። ከነዚህም መካከል ጉዳይኦን መተግበሪያ አንዱ ነው።ይህ መተግበሪያ  ስራ ፈላጊን  ከቀጣሪ ጋር ለማገናኜት የሚያገለግል ሲሆን፤ የመተግበሪያው ዋና ስራ አስኪያጅ እና  ተባባሪ መስራቾች የሆኑት ወይዘሮ  ትግስት አፈወርቅ እንደሚሉት አጀማመሩም ዕለት ተዕለት ከሚያጋጥሙ  ችግሮች በመነሳት ነው። 

ወይዘሮ ትግስት አፈወርቅ የጉዳይኦን መተግበሪያ ተባባሪ መስራች እና ዋና ሰራ አስኪያጅ ምስል፦ privat

«እንግዲህ ጉዳይኦን ስንመሰርት ከራሳችን ችግር ተነስተን ነው ብል ይቀለኛል። እኛ ሀገር ሰራተኛ መቅጠር ስትፈልጊ ቧንቧ ቢበላሽ፣ ኤለክትሪክ ቢበላሽ ለደረሰ ሁሉ ችግር መፍትሄ የሚሰጡ ሰዎች ማግኘት ቀላል አይደለም።ስለዚህ ቤታችን ችግር አለ ደግሞ ብዙ ተሯሩጠው በየሰፈሩ የጥገና ስራእየሰሩ ኑሯቸውን የሚደግፉ ኢ መደበኛ የምንለው ስራ የሚሰሩ ሰዎች በብዛት እንዳሉ እናውቃለን።እንደገና በየአመቱ ከዩንቨርሲቲ ተመርቀው በስራ ፍለጋ የሚንከራተቱ ወጣቶች አሉ።ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ ትንንሽ ስራዎች ላይ የጥገና ስራዎችን የቤት እርዳታ ስራዎችን እንደሚሰሩ እናውቃለን።ስለዚህ አገልግሎት በመፈለግ ለሚንከራተተውም ስራ ሰርቶ ገንዘብ ለማግኘት ለሚፈልገውም ተደጋጋሚ ስራ እንዲያገኝ መፍትሄ የሚሆን በቴክኖሎጅ የታገዘ ህይወትን ቀላል የሚያደርግ ገበያ እንፍጠር ብለን ነው ጉዳይኦን የተፈጠረው።» በማለት ስለመተግበሪያው አመሰራረት ገልፀዋል።
ይህ መተግበሪያ  «ጉድ ዴይ ኦንላይን» በተሰኘው  ኩባንያ አማካኝነት በ2013 ዓ/ም መጀመሪያ የተመሰረተ ሲሆን፤ የፅዳት እና የምግብ ማብሰል ስራዎችን ፣የቤት ውስጥ እገዛ ፣ ሞግዚቶችን፣ የቤት ሰራተኞችን፣ አስጠኝዎችን፣ የግንባታ ሰራተኞችን  እንዲሁም የቧንቧ እና የኤሌክትሪክ ጥገና አገልግሎት ላይ የሚሰሩ ግለሰቦችን በ3 ኪሎሜትር ርቀት ውስጥ ከቀጣሪዎች ጋር ያገናኛል።ይህም እንደ ወይዘሮ ትግስት በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ሴቶች ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል። አዲስ የስራ ባህልንም ያበረታታል። 
«እና በጣም የሚያበረታታ ነው።የብዙ ሰዎችን ችግር የሚፈታ ነው።ስራ ሰርተው የማያውቁ እናቶች ተቀጥሬ እሰራለሁ ብለው የማያውቁ አሁን ላይ በኛ ፕላት ፎርም ላይ ሁለት ሶስት ቦታ ትንንሽ ስራዎችን እየሰሩ ነው።» ካሉ በኋላ «አሁን አሁን አዲስ የስራ ባህል ከድሮው ኩራት ካለበት የኢትዮጵያ የስራ ባህል ስራ ከሚመረጥበት ባህል ወጥቶ ስራን የሚያከብር አዲስ ትውልድ በኛ «ፕላትፎርም» ላይ እየተፈጠረ እየተበረታታ ነው።» ብለዋል።

ምስል፦ Tigist Afework

«ጉዳያችሁ ጉዳያችን ነው» በሚል መርህ አገልግሎት የሚሰጠው ይህ መተግበሪያ፤ እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች አውርደው እየተጠቀሙበት  ሲሆን፤ 250 ሺህ የሚደርሱ  የአገልግሎት ጥያቄዎችን በመተግበሪያው በኩል መቀበላቸውን  ወይዘሮ ትግስት ገልፀዋል ። ከ 70,000  በላይ የሆኑ ሰዎች ደግሞ በተሳካ ሁኔታ የስራ ዕድል አግኝተዋል። ከነዚህ መካከል ወይዘሮ ወይንሸት ጌታቸው አንዷ ናት። 
«ጉዳይኦን ላይ ገብቼ መስራት የጀመርኩት አምና 2014 ነሀሴ ላይ ነው።እግዚያብሄር ይመስገን እየሰራሁ ነው ያለሁት።ችግር አላጋጠመኝም መጀመሪያ ስጀምር በ«አፕሊኬሽኑ» ነው። አፕሊኬሽኑን ከፕሌይስቶር አወረድን እና እኔና ባለቤቴ ይህንን ነገር እንሞክር ብለን ሞከርን ፖስት አደረኩ።ብዙ ጊዜ እንኳ ሳይቆይ ወዲያው አስተያየት ተሰጠኝ። ወዲያው ሰዎቹን አገናኙኝ። ወዲያው ስራ ጀመርኩ።»ስትል ገልፃለች። 
ወይንሸት አረብ ሀገር ከተመለሰች ወዲህ ስራ በማጣት ቤቷ መቀመጧን ገልፃ  በፅዳት እና በምግብ ማብሰል ስራ  ለመቀጠር መተግበሪያው ረድቷታል።ይህም በኑሮዋ ላይ ለውጥ ማምጣቱን ትገልፃለች።
«ኑሮዬ ላይ ያሳየኝ ለውጥ አንደኛ ነገር እኔ ከአረብ ሀገር ተሰድጄ ረጅም ጊዜ ቆይቼ በብዙ ችግር ነው የተመለስኩት።ተመልሼ ቤት ቁጭ ካልኩኝ በኋላ እዚህ ሀገር ላይ ደላላ ቤት ሄጄ ስራ ፈልጌ አልቀጠረም ነበር ይህንን ባለገኝ ኖሮ።አንደኛ እቤት ከመቀመጥ አድኖኛል ሁለተኛ አነሰም በዛም ከእጅ ወደ አፍ በምንኖርበት ኖሮ ላይ በጣም ህይወቴን ደግሞልኛል።እየሰራሁ ነው መስራት በራሱ ትልቅ ነገር ነው።»ብላለች።
በዚህ ሁኔታ ጉዳይኦን ሴቶችን በሁለት መንገድ የሚጠቅም መተግበሪያ ነው።አንድም እንደ ወይንሸት ተቀጥሮ በመስራት ኢኮኖሚን ለመደጎም በሌላ መንገድ ለሴቶች ብቻ የተተወውን የቤት ውስጥ የስራ ጫናን ለመቀነስ አቅሙ ያላቸው ሴቶች ቀጥረው እንዲያሰሩም ይረዳል።መተግበሪያውን ከጎግል ፕሌይ እና ከአፕ ስቶር  ማውረድ የሚቻል ሲሆን፤ አጠቃቀሙም በሁለት መንገድ ነው። 

ምስል፦ privat

«ጉዳይ በሁለት አይነት መንገድ ይሰራል።ለአገልግሎት ፈላጊዎች ወይም ለአገልግሎት ሰጭዎች በሁለት አይነት መንገድ ፕሮፋይል ይሰራል አፕሊኬሽኑ ወርዶ።አገልግሎት ፈላጊ ስልኩ ላይ አፕሊኬሽኑን ሲጭን በአካባቢው በሰፈሩ ሳይርቅ እስከ 2 ኪሜ የሚኖር ባለሙያ በፈለገው ሙያ ለልጆች አስጠኝ ሊሆን ይችላል።ተመላላሽ ሰራተኛ፣ ምግብ የሚያበስል፣ ጽዳት ሰራተኛ፣ ሊሆን ይችላል።ቴክኒካል ሰራተኛ ቧንቧ ኤለክትሪክ ጥገና ሊሆን ይችላል።በሚፈልገው የስራ ዘርፍ መርጦ  ይፈልጋል። ቅርብ ያለውን ሰው ደውሎ ያናግራል ጠርቶ ያሰራል።አገልግሎት ሰጭዎች የሆነ ባለሙያ ደግሞ አፕሊኬሽኑን ያወርዳል።እንደ ባለሙያ ይመዘገባል።መታወቂያ ያለው መሆን አለበት።ፎቶግራፉም መኖር አለበት።ማንነቱ እንዲመሰከር እንፈልጋለን።በእርግጥ መታወቂያ እና ፎቶ እንዲያስገባ ሲስተሙ ይጠይቀዋል።»በማለት አብራርተዋል። 
ከዚህ በተጨማሪም መተግበሪያውን የሚያወርዱ ሰዎችን ስልክ በመደወል እና በአካል በማግኘት ስለአጠቃቀሙ ተጨማሪ መረጃ እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል።ከመተግበሪያው በተጨማሪ የስማርት ስልክ ተጠቃሚ ላልሆኑ ሰዎችም ነፃ የስልክ የጥሪ ማዕከል መዘጋጄቱን አስረድተዋል።ይህም አዲስ ተመርቀው ስራ ለሚፈልጉ ወጣቶች ጭምር  ትንንሽ ስራዎችን እየሰሩ ለመቆየት መንገድ ይከፍታል።  
ጉዳይኦን ከሁለት አመት በላይ በነፃ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መተግበሪያ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ተጨማሪ ጥቅሞችን የሚሰጥ የክፍያ/የፕሪሚየም/ አገልግሎት ጀምሯል።

ምስል፦ Tigist Afework

ከሁለት ዓመታት በላይ በዘለቀው የጉዳይኦን  የአገልግሎት ጉዞ ገበያው ላይ የሚፈለጉ ዘርፎችን መለየታቸውን የገለፁት ወይዘሮ ትግስት፤ እስካሁን በአብዛኛው  በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተወስኖ የቆየውን አገልግሎት በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ለማስፋት ዕቅድ ይዘዋል።
ያም ሆኖ የሰዎችን ማንነት ለማጣራት የሚረዳ  የተደራጄ ዲጅታል  ውሂብ አለመኖር፣የመብራት እና የበይነመረብ መቆራረጥ ፈተናዎች ናቸው።ከዚህ ባሻገር   በገበያው ብዙ ተፈላጊነት ያላቸው ሴቶች ቢሆኑም፤ በኢኮኖሚ ችግር ሳቢያ የስማርት ስልክ እና የበይነመረብ ተጠቃሚነታቸው እንዲሁም ለቴክኖሎጅ ያላቸው ቅርበት  አነስተኛ በመሆኑ ይህንን ዲጅታል መድረክ በሚፈለገው ደረጃ ለሴቶች ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን ሃላፊዋ ተናግረዋል።በዚህ የተነሳ በዲጅታል መድረኩ ተጠቃሚ የሆኑት ሴቶች 30 በመቶ ብቻ ናቸው ይላሉ።

«እንግዲህ ከኢትዮጵያ በዓመት ስንት ሴቶች በቤት ሰራተኝነት ወደ ሚድል ኢስት እንደሚሄዱ እናውቃለን።እንዴት ተጉላልተው እንደሚመለሱም እናውቃለን።አሁን ዘመኑ ተለውጧል ጥሩ ደሞዝ ይከፈላል።እንደ ዱሮው አይደለም። እዚህ ሀገር ሁለት ሶስት ቦታ ቢሰሩ፤አረብ ሀገር ተንገላተው የሚያገኙትን ያገኙታል።ግን የት እናግኛቸው? በጭራሽ አይገኙም።በሶሻል ሚዲያ ማስታወቂያ እናደርጋለን ወንዶች ናቸው ሴቶች አይመጡም።በአፕሊኪሽናችን 30 ፐርሰንት ብቻ ናቸው ሴቶች።70 ፐርሰንቱ ወንዶች ናቸው።ግን ገበያው የሚጠይቀው ብዙ ሴቶችን ነው።በዚህ አጋጣሚ ስራ ፈቶ ስራ የሚፈልጉ ሴቶች፤ ተቀጥረው መስራት የሚፈልጉ እና ሙያ ያላቸው ሴቶች 9675 በስልክ ቁጥራችን እንዲደውሉንን እና የስራ ገበያውን እንዲቀላቀሉ።» በማለት ወይዘሮ ትግስት አፈወርቅ አሳስበዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ 
ሽዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW