1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተለያዩ ሃገራት ጉዳታቸው የከፋው የአየር ጠባይ ክስተቶች መደጋገም

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 9 2015

የደቡብ አውሮጳ ሃገራት ከፍተኛ ሙቀትና ሰደድ እሳት፣ ሰሜን አውሮጳ ሃገራት ደግሞ ወቅቱ በጋ ቢሆንም ከባድ ዝናብ ያስከትለውን ጎርፍ እያስተናገዱ ነው። ሰሜን አሜሪካ በሙቀት ማዕበል፤ በሰደድ እሳት እንዲሁም በጎርፍ፣ እስያም እንዲሁ ሙቀት እና ጎርፍ ተደጋግመው ጉዳት እያደረሱ ነው። መንስኤው ምን ይሆን?

የሰደድ እሳት በሃዋይ
በሃዋይ ደሴት ማዊ ላይ የደረሰው ከባድ ሰደድ እሳት በዩናይትድ ስቴትስ ካጋጠመው እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ መሆኑ ተገልጿል። የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም እየተነገረ ነው። ምስል Zeke Kalua/County of Maui//REUTERS

ጉዳታቸው የከፋው የአየር ጠባይ ክስተቶች መደጋገም

This browser does not support the audio element.

ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ካለው ከፍተኛ ሙቀት ጋር ተያይዞ የሰደድ እሳት በአንድ ወገን፤ በሌላው ደግሞ ከባድ ወጀብ የሚገፋው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረትም ወድሟል። ሰሞኑን የብዙዎችን ቀልብ በሳበው የሃዋይ ደሴትን ያጋየ ሰደድ እሳት ተጎጂዎችን ለመርዳት ማኅበረሰቡ እየተረባረበ ነው። በእሳት ከወደመው የሃዋይ ደሴት ኗሪዎች ተወስደው ለጊዜው ባረፉበት ሆቴል በምግብ አብሳይነት ከሚያገለግሉት አንዱ ከአደጋው ስለተረፉት ወገኖች ሲናገር፤ «እያንዳንዱ ሰው የየራሱ ታሪክ አለው ምክንያቱም ሁሉም ሰው የሆነ ነገር አጥቷል።» ነው ያለው። በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ሰው ለሌላው አጽናኝ እና ደጋፊ መሆን ይችላል፤ ምክንያቱም አንዱ በሌላው ሕይወት ውስጥ ምን እንዳለፈ ይረዳል። ስለዚህ መርዳት ከባድ አይደለም።»ብሏል።

የሟቾች ቁጥር 100 መድረሱን የሚገልጹት ወገኖች ለጉዳቱ መባባስ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ አልወሰደም በማለት ይወቅሳሉ። የተጠቀሰው ቁጥር እስከ እሑድ ምሽት ድረስ ያለውን የሚያመለክት ብቻ መሆኑን የሚናገሩት የአካባቢው ባለሥልጣናት ሰደድ እሳቱ ደሴቲቱን እንዳልነበረች አድርጎ በማውደሙ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። 

የተፈጥሮ አደጋ በስሎቬንያ፣ ኦስትሪያ እና ክሮኤሺያ

የሃዋይ ሀገረ ገዢ፤ በደሴቲቱ ታሪክ ይኽ አይነቱ የተፈጥሮ አደጋ የመጀመሪያ መሆኑን ነው የተናገሩት። ሰደድ እሳቱ ማኒ ላይ በአንድ ቦታ ሲከሰት ያ ከመጥፋቱ አስቀድሞ በርካታ የሰደድ እሳት በተለያዩ አካባቢዎች መነሳቱን ነውም አስረድተዋል። እሳቱን ለማጥፈታ የደረገውን ጥረትም ኃይለኛ ንፋስ እያደናቀፈ መሆኑንም አልሸሸጉም። ትናንት የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱትም በሰደድ እሳቱ ከ2000 የሚበልጡ ሕንጻዎች ወድመዋል፤ ባጠቃላይ በደሴቲቱ የደረሰው የጉዳት መጠንም 6 ቢሊየን ዶላር ተገምቷል። በእሳቱ ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው በአካባቢያቸው እርዳታ የሚያስተባብሩት ወገኖች ለተፈናቀሉት የተገኘውን ሁሉ እያሰባሰቡ መሆኑን ይናገራሉ።

በሰደድ እሳቱ ከ2000 የሚበልጡ ሕንጻዎች ወድመዋል፤ ባጠቃላይ በደሴቲቱ የደረሰው የጉዳት መጠንም 6 ቢሊየን ዶላር ተገምቷል። ምስል Rick Bowmer/AP Photo/picture alliance

በሰሜን አሜሪካ ብቻም አይደለም ከፍተኛው ሙቀት ሰደድ እሳት ያስነሳው፤ የደቡባዊ አውሮጳ ሃገራት እና ሰሜን አፍሪቃም ተመሳሳይ ችግር ተጋፍጠዋል። ፖርቱጋል ውስጥ ሰፊ አካባቢን መያዙ የተነገረለት ሰደድ እሳት ሰባት ሺህ ሄክታር መሬት ሲያዳርስ፤ ስፔን ውስጥም በተለያዩ አቅጣጫዎች ላይ እሳት መቀስቀሱ ተነግሯል። በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር ይፈጥናል በተባለው ንፋስ የታገዘው የሰደድ እሳት ከ500 ሄክታር በላይ ማንደዱም ተመልክቷል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የቀድሞ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መድረክ ሊቀመንበር ሮበርት ዋትሰን እንደሚሉት የሰዎች እንቅስቃሴ የበኩሉን አስተዋጽኦ በሚያደርግበት በዚህ ክስተት በተለይ ሰፊ የደን ሀብት ያላቸው ሃገራት ወደ ፊትም የሰደድ እሳት እንደሚከሰት አስበው አስቀድመው የየበኩላቸውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል። «ቀደም ብለን ካናዳ ላይ አይተናል። ግሪክም እንዲሁ ተመልክተናል። አሁን ደግሞ ሃዋይ የሆነውን እያየን ነው። እንዲያለውን ክስተት በመላው ዓለም ደኖች ባሉበት ቦታ ሁሉ ማየታችንም ይቀጥላል።»የተፈጥሮ አደጋ በስሎቬንያ፣ ኦስትሪያ እና ክሮኤሺያ 

ወትሮም በሞቃታማ የአየር ሁኔታ በሚታወቁት የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት የሙቀት መጠኑ እጅ ከፍ በማለቱ ሰዎች ለመተንፈስ እስኪቸገሩ ማድረሱ ነው የተሰማው።

ኖርዌይ ውስጥ ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በመሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ አቅራቢያ በጎርፍ የደረሰውን ጉዳት ለመጎብኘት በስፍራው የተገኙት የሀገሪቱ ንጉሣዊ ቤተሰብ ልዑል ሃኮን፤ ኃይለኛ የአየር ጠባይ በኖርዌይ እንግዳ ባይሆንም የአሁኑ ግን ይለያል ነው የሚሉት።ምስል Stian Lysberg Solum/NTB/picture alliance

ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ

በተቃራኒው የሰሜን እና ምሥራቅ አውሮጳ እንዲሁም እስያ ሃገራት በከባድ ወጀብ የታገዘ ዝናብ ጎርፍ አስከትሎባቸዋል። የስካንዴኒቪያ ሃገራትን የመታው «ሃንስ» የሚል ስያሜ የተሰጠው ወጀብ ከባድ ዝናብ እና ኃይለኛ ንፋስ አስከትሎ የመሬት መንሸራተት እንዲሁም በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት አድርሷል። ስዊድን ላይ ጀምሮ ወደ ኖርዌይ ከዚያም ዴንማርክ እና ፊንላንድን ያዳረሰው ወጀብ ቤቶችን ከመሠረታቸው እየገረሰሰ በርካታ አካባቢዎችን እንዳልነበሩ አድርጓል። በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ አቅራቢያ በጎርፍ የደረሰውን ጉዳት ለመጎብኘት በስፍራው የተገኙት የሀገሪቱ ንጉሣዊ ቤተሰብ ልዑል ሃኮን፤ ኃይለኛ የአየር ጠባይ በኖርዌይ እንግዳ ባይሆንም የአሁኑ ግን ይለያል ነው የሚሉት።

«ኖርዌይ ውስጥ ለበርካታ አስቀያሚ የአየር ጠባይ እንግዳ አይደለንም፣ እናም አዲስ ነገር የለም። ሆኖም ግን አዲስ የሚሆነው በጣም አስከፊ እየሆነ መምጣቱ እና ከዚህ በፊት በማይከተትባቸው ጊዜያት እንዲሁም በአዳዲስ ቦታዎች ላይ መታየቱ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ብዙ ዝናብ፤ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ካፊያ በብዙ ቦታ ይኖራል። ብዙውን ጊዜ ደግሞ በበርካታ ቦታ ይከሰትና የሚያስከትለው ጣጣም መጠነኛ ይሆናል አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጣም ብዙ ዝናብ በትንሽ አካባቢ ይኖርና ሰፋ ያለ ችግር ያስከትላል። ይኽ የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮት ነው።»

ሰሜናዊ ጣልያን እና በደቡብ ጀርመንም እንዲሁ ከኃይለኛው ሙቀት ጎን ለጎን ከባድ ዝናብና ትላልቅ በረዶ ያደረሰው ጉዳት ቀላል እንዳልሆነ ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት። የሁለቱ ሃገራት አጎራባች የሆነችው ኦስትሪያም ደቡባዊ ግዛቶቿ በከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ተጥለቅልቀዋል።

ደቡባዊ ጀርመን ግዛት ሩቲልንገን ከተማ እና አካባቢው በበጋው ከከባድ ዝናብና ጎርፍ በተጨማሪ ትላልቁ በረዶ ባልተለመደ መልኩ ወርዶ እንቅስቃሴ አደናቅፏል።ምስል Schulz/SDMG/picture alliance/dpa

ወደ እስያም ብንሻገር በሰሜናዊ ቻይና ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ያጋጠመው የመሬት መንሸራተት እስከ ትናንት ለ21 ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ ተነግሯል። በሕንድ ሂማሊያ ግዛትም የመሬት መንሸራተት በእሑድ ምሽት ብቻ የ16 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። በርካቶችም ከአካባቢው ለመውጣት እንዳልቻሉ ተዘግቧል።

ተለዋዋጩ የአየር ክስተት 

በየጊዜው በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ የሚለዋወጡት ኤሊ ኒኞ እና ላ ኒኛ የተሰኙት የአየር ንብረት ክስተቶች በመላው ዓለም የአየር ጠባይ ሁኔታ ላይ ከባድ ተጽዕኖ እንደሚያስከትሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሃገራት ከባድ ጉዳት ላስከተለው የአየር ሁኔታም መንስኤው የኤሊ ኒኞ ክስተት ነው እያሉ ነው። የዓለም ሜትሪዎሎጂ ድርጅት ላለፉት ሦስት ዓመታት ዓለም በላ ኒኛ ተጽዕኖ አስቸጋሪ ጊዜያትን ማሳለፉን አስታውሶ፤ ካለፈው ሐምሌ ወር አንስቶ ወደ ኤሊ ኒኞ ተጽዕኖ መሸጋገሩን አረጋግጧል። ኤሊ ኒኞ ሲከሰት ድርቅ እሱን ተከትሎም ረሃብ እንዲሁም በሽታ ሊስፋፋ እንደሚችል የዘርፉ ተመራማሪዎች በበኩላቸው እያስጠነቀቁ ነው።

ከባድ ዝናብ እና የዝናብ እጥረት ያስከተለዉ አደጋ

ዓለም አቀፉ የረድኤት ድርጅት ኦክስፋም እንደሚለው በፓስፊክ ውቅያኖስ አቅራቢያ የሚገኙ እንደ ፓፓዋ ኒው ጊኒ ያሉ ሃገራት ከወዲሁ በዚሁ ተጽዕኖ ምክንያት ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል። ድርጅቱ እንደሚለው በተጠቀሰው ሀገር ብቻ 3 ሚሊየን ሕዝብ ሊጎዳ ይችላል።

ድንገት የሚከሰተው እንዲህ ያለው ኃይለኛ ሙቀትም የበርካቶችን ጤና በማቃወስ፣ ለድንገተኛ የደም ዝውውር መታወክ ብሎም ለሕልፈተ ሕይወት ሊያደርስ እንደሚችል ነው የተገለጸው። በአሜሪካ ቦስተን ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት እና የዜና ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ግሪጎሪ ዌልኒዩስ፤ «ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሙቀት ማዕበል ያስከተለው ከባድ የአየር ሁኔታ በርካቶችን ለሞት መዳረጉን ይናገራሉ። ባለፈው ዓመት ብቻ አውሮጳ ውስጥም ከኃይለኛው ሙቀት ጋር በተያያዘ የጤና እክል የ60 ሺህ ሰዎች ሞት መመዝገቡን አስታውሰዋል። የዓለም ሜቴሬዎሎጂ ድርጅት እንደሚለው ከሆነም የኤል ኒኞ ተጽዕኖ ለምሳሌም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እስከ መጪው ዓመት የካቲት ወር ድረስ መዝለቁ የማይቀር ነው።

ደቡባዊ ጀርመን ግዛት በበጋው የወረደው ከከባድ ዝናብና ጎርፍ ያልበገራቸው የጃዝ ሙዚቃ አድናቂዎች ወደ ተዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ለመሄድ በጭቃ ውስጥ ዳክረዋል።ምስል Christian Charisius/dpa/picture alliance

ከሰሜን አሜሪካ እስከ እስያ፣ ከሰሜን አውሮጳ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ የከፋ ጉዳት ማስከተሉን የቀጠለው አደገኛ የአየር ሁኔታ የየዕለት ዜና ከሆነ ሰነባብቷል። በመላው ዓለም የሙቀት መጠኑ መጨመርም ሆነ ከባድ ሞገዶችና ዝናብ እሱንም ተከትሎ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው ጎርፍ የአየር ንብረት ለውጥ ማሳያዎች እንደሆኑ የሚገልጹ ቢኖሩም፤ የዘርፉ ባለሙያዎች በዋናነት የኤሊ ኒኞ ተጽዕኖ የክስተቶቹን መደጋገም እና አደገኛነት አባብሶታል ባይ ናቸው።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW