በሀገሪቱ የምሥራቅ አካባቢዎች ጉዳት ሊያስከትል የሚችል የዝናብ ሁኔታ ማስጠንቀቂያ
ረቡዕ፣ ሰኔ 18 2017
ለዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት በኢንስቲቲዩቱ የሶማሌ ክልል እና አጎራባች አካባቢዎች የሜትሮሎጂ ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዴስክ መሪ አቶ አሸናፊ ሙሉነህ ቀደም ባሉ ዓመታት በድሬደዋ እና ሌሎች ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ቀውስ ያስከተሉ የጎርፍ አደጋዎች ዓይነት ሊከሰት እንደሚችል ትንበያ መኖሩን በመግለፅ አስፈላጊው የቅድም ጥንቃቄ ሥራ መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የክረምቱን ወራት የሜትሮሎጂ መረጃዎችን ለዶይቼ ቬለ በስልክ የገለጡት የሶማሌ ክልል እና አጎራባች አካባቢዎች የሜትሮሎጂ ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዴስክ መሪ አቶ አሸናፊ ሙሉነህ በክረምቱ በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የከፋ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የዝናብ ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁም ትንበያ መኖሩን ገልፀዋል።
«የዘንድሮው ክረምት ከፍተኛ የዝናብ ሁኔታ እና በጎርፍ አደጋ ሳቢያ ከፍተኛ ቀውስ የተመዘገበባቸውን እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1998 እና 2010ዓ.ም የነበሩትን ጊዜያት ይመስላል ተብሎ ይጠበቃል» ብለዋል።
«ድሬደዋ እና በድሬደዋ ዙርያ እንዲሁም በሰሜን ሶማሌ የጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ የእግር ተዳፋት ፣እንዲሁም ከጭናክሰን እስከ ጅግጅጋ ባሉ የጎርፍ መፋሰሻ መስመሮች ላይ የክረምቱ የከባድ ዝናብ አዝማሚያ ጎርፍንን ያስከትላል። ቀውሶች የሚደገሙበት ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ተብሎ ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያዎች» እየተላለፉ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ አሸናፊ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል። «በተለይ ለፍርድ ተጋላጭ በሆኑ በድሬደዋ እንዲሁም ወደ ጅግጅጋ አካባቢዎች ቅድመ ማስጠንቀቂያው በተጠናከረ መልኩ ወረዳ ድረስ ተደራሽ በማድረግ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቃል»
በድሬደዋ እና አካባቢው በአሁኑ ወቅት እየታየ ስለሚገኘው ከፍተኛ የሆነ የሙቀት ሁኔታ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አሸናፊ «ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ካለው የአየር ንብረት አለመረጋጋት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል» ጠቁመዋል።
መሳይ ተክሉ
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር