1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጉግልና ቻይና፣

ሐሙስ፣ መጋቢት 9 2002

የኢንተርኔት መረጃ ፈላጊው «ማሺን» (ጉግል)፣ ሳንሱርን በመቃወም በመጀመሪያ ባለፈው ጥር ወር ቻይናን ለቅቄ እወጣለሁ ሲል ከዛተ ወዲህ አሁንም በማንገራገር ላይ ነው።

ምስል picture alliance/dpa

በቅርቡም፣ በቻይናውያንና በአሜሪካውያን መካከል የተካሄደው ድርድር ሳይሠምር መቅረቱ ነው የተነገረው። ከቤይጂንግ የዶቸ ቨለ ባልደረባ ፔትራ አልደንራት የላከችውን ዘገባ፣ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

የኢንተርኔቱ ኩባንያ ፣ ጉግል፣ ቻይና ውስጥ አገልግሎት መስጠት የጀመረው እ ጎ አ ፣ በ 2006 ዓ ም ነው። የድረ ገጹ አድራሻም http://WWW.google.cn ሲሆን፣ በኢንተርኔት አገልግሎት ረገድ በቻይና ገበያ ከፍተኛውን ሥፍራ መያዙ እንደማይቀር ነበረ የተነገረለት። የገበያው ተሳታፊ ለመሆንም ፣ ጉግል ፣ የቻይናን የሳንሱር ህግ አክብሮ ነው የተሠማራው። በቻይና የተከለከሉ ድረ ገጾች፣ በጉግል የሚከፈቱ አልነበሩም። ያም ሆኖ፣ ቻይናውያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች፣ ጉግልን እንደ አንደ በረከት ነበረ የሚመለከቱት። የአጭር ድረ-ገጽ አገልግሎት አቅራቢው Michael Anti እንደሚሉት፣ ቻይናውያን ስለተለያዩ ጉዳዮች መረጃ ለማግኘት በአገራቸው የመረጃ አገልግሎት ሰጪ ማሺን «ባይዱ» ብቻ አልነበረም መመካት የሚችሉት።

«በእርግጥ ጉግል በቻይና የሚዘጋ ከሆነ፣ ከ 2006 ዓ ም በፊት ወደነበርንበት ነው የምንመለሰው። ባይዱን የምጠቀምበት የአገር ውስጥ የሆነ፤ ስለቻይና ማለት የአገር ውስጥ መረጃ ለማ ኘት ብቻ ነው። የፖለቲካ ንቃተ ኅሊና ያለኝ ጋዜጠኛ እንደመሆኔ መጠን፣ በዚያ ልትማመን አልችልም። መረጃዎቼን የምሰበስብ ከጉግል ነው።»

ምስል google

ባለፈው ጥር ጉግል፣ የቻይናን የሳንሱር ደንብ ማክበር መቀጠል ግዴታው ከሆነ ፣ ከዚያች ሀገር ለቆ እንደሚወጣ ዛቻውን ማሰማቱ የሚዘነጋ አይደለም። ከዚያን ጊዜ አንስቶም ነበረ፣ ውይይት አሜሪካውያንና በቻይናውያን መካከል ሲካሄድ የቆየው። ቻይና ከመመሪያዬ ንቅንቅ እንደማትል፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ቺን ጋንግ በድጋሚ ነው ያስገነዘቡት።

«ጥያቄአችሁን በተመለከተ፣ ጉግል ከቻይና ቢወጣ ምን ዓይነት ሁኔታ ያስከትላል ለሚለው፣መልሱ፣ ይህ የአንድ የንግድ ኩባንያ የግል ውሳኔ ነው የሚል ነው። ቻይና ውስጥ ገንዘብን ሥራ ላይ በማዋል ረገድ አንዳች ተጽእኖ አያሳርፍም፣ አብዛኞቹ የውጭ ሃገራት ኩባንያዎች ቻይና ውስጥ ጥሩ ንግድ በማካሄድ ላይ የሚገኙበትን ተጨባጭ ሁኔታ አይለውጠውም። የውጭ ሀገር ሆኑ የቻይና ኩባንያዎች ፣ ሁሉም፣ የአገሪቱን ህግ ማክበር አለባቸው።»

ጉግል፣ በእርግጥ እስካሁን ይከተል የነበረውን መርኅ ለመተው ከመረጠና ሳንሱሩን ከአንግዲህ አልቀበልም የሚል አቋም ካልያዘ የቻይናው ድረ-ገጽ መዘጋቱ አይቀሬ ነው። አሁን ከጉግል ጋር የተያዘው ውጣ-ውረድ፣ የቻይና መንግሥት ምን ዓይነት የመቆጣጣ,ር ኃይል እንዳለው ያሳያል የሚሉት አንዲት ስማቸው እንዲገለጥ ያልፈለጉ ቻይናዊት ናቸው።

«ይህ ሐሳብን በነጻ በመግለጽ ረገድ ያለብንን መጥፎ ገጽ እንደገና አጉልቶ ያሳያል። ለቻይናውያን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች፣ ጉዳት ነው። አንዳች አስተማማኝ ሁኔታ አለመኖሩንም ያረጋግጣል። ማንኛውንም የምናገኘውን ነገር እንደገና ልንቀማ እንደምንችልም ያሳያል።»

በዚህ ሂደት፣ የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሆኑ ቻይናውያን ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ፣ የቻይና ኩባንያዎችም ከተጽእኖው አያመልጡም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ የጉግል አግልግሎቶች፣ የኢ-ሜይል አገልግሎት gmail.cn ጭምር ሊቀር ይችላል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚጠቀሙ ቻይናውያን፣ የጉግል የካርታ አገልግሎት ሊቋረጥባቸው ይችላል። ይህን ክፍተት መሙላቱ፣ ውድ ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል። በሌላም በኩል አዲስ አገልግሎት ሰጪ ሊቀርብ ይችላል። የቻይና ገበያ ጥብቅ ሳንሱር ቢኖርበትም አማላይነቱ እንዳለ ነው። የጉግል ተቀናቃኞች ያሁና ማይክሮሶፍት፣ የጉግልንና የቻይናን ንትርክ ውጤት በጉጉት በመጠባባቅ ላይ መሆናቸው አልታበለም።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW