1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

"ጊዜው የተግባር እንጂ ውጥረት የሚባባስበት አይደለም"- ጆሴፕ ቦሬል

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 14 2013

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከሰጡት አወዛጋቢ አስተያየት በኋላ የአውሮፓ ኅብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል እንዳሉት "አሁን ጊዜው የተግባር እንጂ ውጥረት የሚባባስበት አይደለም።" ጆሴፕ ቦሬል "በታላቁ የኢትዮጵያ የኅዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ላይ ስምምነት የሚደረሰው በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብጽ መካከል ነው" ብለዋል።

Kroatien Treffen EU-Außenminister in Zagreb Josep Borrell
ምስል፦ Getty Images/AFP/D. Sencar

የአውሮፓ ኅብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ሰበብ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብጽ መካከል ውጥረት ሊባባስ እንደማይገባ አሳሰቡ። ኃላፊው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከሰጡት አወዛጋቢ አስተያየት በኋላ እንዳሉት "በታላቁ የኢትዮጵያ የኅዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ላይ ስምምነት የሚደረሰው በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል ነው።"

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሶስቱ አገሮች ሥምምነት አቅርበው እንደነበር በትናንትናው ዕለት ተናግረው ነበር። "ሥምምነት አቅርቤላቸው ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ ሥምምነቱን ሳትቀበል ቀርታለች። እንደዚያ ማድረግ አልነበረባቸውም። ያ ትልቅ ስህተት ነው" ብለዋል።

በዚሁ ምክንያት አገራቸው ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ዕርዳታ እንዳቋረጠች የገለጹት ትራምፕ ግብጽ ግድቡን "እንደምታፈነዳ" ጭምር ተናግረዋል።

 ግብጽ የኅዳሴ ግድብ እንደምታፈርስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተናገሩ

"አሁን ጊዜው የተግባር እንጂ ውጥረት የሚባባስበት አይደለም" ያሉት የአውሮፓ ኅብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ግን ሶስቱ አገሮች በጀመሩት ድርድር ገፍተው ከሥምምነት የመድረስ ዕድል እንዳላቸው ዛሬ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

"የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበር የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ሁሉንም ወገኖች መፍትሔ እንዲያበጁ ለማደራደር የጀመረችው ጥረት የአውሮፓ ኅብረት ሙሉ ድጋፍ አለው" ያሉት ቦሬል ድርድሩ ቀጥሎ ስኬታማ ፍጻሜ ላይ ይደርሳል የሚል ዕምነት በአውሮፓ ኅብረት ዘንድ እንዳለ ጠቁመዋል።

"በታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ላይ በድርድር ይደረሳል ተብሎ ከሚጠበቅ ስምምነት በውኃ ደሕንነት፣ በመስኖ፣ በግብርና እና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መዋዕለ-ንዋይ ተጠቃሚ ለመሆን በናይል ተፋሰስ አገሮች የሚገኙ ከ250 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እየጠበቁ ነው" ሲሉ ጉዳዩ በርካቶችን እንደሚመለከት ጆሴፕ ቦሬል በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል።

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW