ጋምቤላ፤ በእንጭጩ ካልተጨ
ሰኞ፣ ነሐሴ 1 2015አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በአራቱም አቅጣጫዎች ደም አፋሳሽ ግጭቶች መስማት እንግዳ ነገር አይደለም። የእርስበርስ ግጭቱ የተለያየ ቅርጽ እና መነሻ ቢኖረውም በውጤቱ ግን ሚልዮኖችን ለሞት እና መፈናቀል ዳርጓል፤ ሐብት ንብረታቸውን አውድሟል፤ ድርጊቱም እየቀጠለ ነው።
ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ ውኃ በመቅዳት ላይ የነበረች እናት በበራሪ ጥይት መገደሏን ተከትሎ እዛ አካባቢ ሁሌም እንደሚሆነው ግጭቱ መልኩን ቀይሮ የጎሳ ቅርጽ በመያዙ ወደሌሎች እየተዛመተ፤ ግጭቱ ሌላ ግጭት እየወለደ ብዙዎችን ለሞት መቁሰል እንዲሁም ለዝርፊያ አጋልጦ ጋምቤላ አሁን በሰዓት እላፊ የእንቅስቃሴ ገደብ ላይ ትገኛለች። የጋምቤላ አሁናዊ ሁኔታ እንዲያስረዱን በርካታ ነዋሪዎችን አነጋግረናል። የተወሰኑትን እናስደምጣችሁ። የጋምቤላ ነጻነት ግንባር አባል አቶ ጆብ ፓል
"እንቅስቃሴ የለም። ከጋምቤላ ወደሌላ የሚወስዱ መንገዶች ተዘግቷል። ቢሮዎች ዝግ ናቸው። የተወሰነ የንግድ እንቅስቃሴ አለ። ኒዌርከሚኖርበት መንደር ወደ አኝዋ የሚኖርበት አትሄድም፤ ከአኝዋ መንደር ወደ ንዌር መሄድ አትችልም።"
የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግኑኝነት እንዲሁም የግጭት አፈታት ሙሁር እና የአካባቢው ተወላጅ አቶማኑስ ሁንደራም የጋምቤላን አሁናዊ ድባብ እንዲህ ይገልጹታል።
"ምንም የሰላም ድባብ አይታያትም። የሰዓት እላፊውም ተግባራዊ አልሆነም። ዘራፊዎች እንደፍላጎታቸው ይንቀሳቀሳሉ። ሰው በዘራፊዎች ጥይት ተመትቶ እርዳታ ማድረግ የማትችልበት ሁኔታ ነው ያለው።"
ሌላው ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈጉ የጋምቤላ ነዋሪም የሰዓት እላፊውም ብዙም እንዳልፈየደ ይባስ ብሎ ለዝርፊያ እየዳረጋቸው እንደሆነ ይናገራሉ። የጸጥታ ኃይሎች ተገቢውን ጥበቃ እያደረጉ እንዳልሆነ በማከል።
በጋምቤላ ክልል ለግጭት መንስኤ ተብለው የሚጠቀሱ እንደየጊዜው ሁኔታ የተለያዩ ቢሆኑም ሥር የሰደደው ችግር ግን በሁለት ነባር ጎሳዎች መካከል የሚነሱ የቦታ ይገባኛል ጥያቄዎች እንደሆኑ ፖለቲከኞቹና ነዋሪዎች ይስማማሉ። ይሁን እና በየጊዜው በግለሰብ ደረጃ ተነስተው ወደ ጎሳ ግጭት ተቀይረው በክልሉ አለመረጋጋት፣ ሞት መፈናቀል በማስከተሉ ሂደት ግን በአካባቢው በየጊዜው የሚሾሙ አንዳንድ ባለሥልጣናት ከዚህ ከጎሳ አስተሳሰብ ቆፈን ያልጸዱ በመሆናቸው ግጭቱን በመጠንሰስ እና በማባባስ፤ ቆምንለት ለሚሉት ጎሳ የመረጃ፤ የጦር መሳሪያና የአመራር ድጋፍ በመስጠት የጎላ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ አስተያየታቸውን ለጣቢያችን የሰጡ ነዋሪዎች እና ፖለቲከኞች ይናገራሉ።
" በዚህ ግጭት እጃቸው ያለበት አመራር ከመንግስት መጋዘን መሳሪያ ለታጣቂዎች የሚሰጡበት ሁኔታ አለ። "ሌላ ትኩረት ያልተሰጠው ጉዳይ ደግሞ በክልሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቅበላ እና አስተዳደር ደካማ በመሆኑ ስደተኞቹ በዘር ሐረግ ከሚመሳሰሉት ጎሳ ጋር በመወገን የግጭቱ ተካፋይ የመሆናቸው ጉዳይ በእንጭጩ ካልተገራ ሀገራዊ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ነዋሪዎች በምሬት ይናገራሉ።
እንደጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2020 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው በጋምቤላ ክልል ወደ 320,000 የሚጠጉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ይኖራሉ። ነዋሪዎች ግን ይህን አሃዝ አይቀበሉትም፤ በዓለም አቀፍ የስደተኖች አያያዝ ደንብ መሰረት በማስተዳደር ክፍተት ስላለ ቁጥሩ ከዚህ ሊልቅ ይችላል ባዮች ናቸው። በድንበር ሾልከው በመግባት ከሚቀርባቸው ጎሳ ቤተሰቦች ጋር የሚጠለሉ እንዳሉ በመግለጽ።
በክልሉ የሚታዩ ግጭቶች በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ስርአት ችግር አካል መሆኑ ባይካድም፤ ፖለቲከኞች ለየቡድናዊ ፍላጎታቸው ማሳኪያነት ግጭቱን እንደሚያግሙት ባይጠረጠርም፤ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በውሱን መልኩም ቢሆን የግጭቱ አካል እየሆኑ ነው መባሉ ግን ነገሩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
"ብዙዎች በካምፕ አደለም የሚኖሩት፤ ለብሄር ብሄረሰቦች በአል ለእንግዳ ማረፊያ በተሰራው ቦታ ነው የሰፈሩት፤ ሲሰፍሩም የሚጠይቁት አካል የለም። የሆነ ነገር ስትል ጦር ነው የሚመዘዝብህ።"
ሌላው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪም የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ላይ ቁጥጥሩ የላላ ስለመሆኑ እንዲህ ያስረዳሉ።
" በደቡብ ሱዳን ካምፖች ላይ የተከማቹ መሳሪያዎች አሉ። ሁለተኛ ደግሞ እንደነዋሪ ሆነው በመንግስት መስሪያቤት እየሰሩ ደመወዝ የሚወስዱ አሉ። በዘመድ አዝማዶቻቸው እየሰፈሩ የኢትዮጵያ መታወቂያ እየወሰዱ ነው። ማነው ኢትዮጵያዊ ማነው የውጭ ዜጋ የመለየት ስራው ደካማ ነው።ይህ በዚህ ከቀጠለ ከጎሳ ግጭት አልፎ ወደ ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ውግያ ነው የሚወስደን።"
የደቡብ ሱዳን ስደተኞች እኛ መረጃ ባገኘንበት ውሱን መልኩም ቢሆን በአገር ውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ የሚገቡት በስልጣን ላይ ያሉ አመራሮች ድጋፍ ጭምር እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።
"የጦር መሳሪያና ዕጾች የሚዘዋወሩት በእነሱ ነው። ለምሳሌ አንድ ስደተኛ 16 ክላሽ ይዞ በሰአቱ ጠቁመን ተያዘ። ከሰአት ቦኋላ ሰውየው ተለቆ መጥቶ እናንተ ናችሁ የጠቆማችሁኝ ብሎ እኛ ላይ ሲዝት ነበር፤ ሰውየውም እቃውም ተለቆ ማለት ነው። ይህ ውስጥ ለውስጥ የራሳቸው ሰዎች ስላሉ ነው።"
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ማኑስም ይህንን ይጋራሉ።
"የጦር መሳሪያ መሸጥ፤ እንደነሐሽሽ እና ሌሎች ነገሮች ማምጣት መሸጥ መኖራቸውን የሚያጠራጥር ነገር የለውም።"
የጋምቤላ ነጻነት ግንባር አባል አቶ ጆብ ፓል ግን ይህ ፍጹም ከሃቅ የራቀ ነው ባይ ናቸው።
"የግጭቱ መነሻ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ቀበሌዎች ናቸው።እነዚህ ደግሞ ከስደተኞe በጣም የራቁ ናቸው። ስለዚህ ሰላም እንዳይወርድ የሚፈልጉ ሃይሎች ቀጥታ ወደ ስደተኞች ነው የሚያላክኩት።"
አቶ ጆብ ፓል ይህን ይበሉ እንጂ የደቡብ ሱዳን ተመላላሽ ነጋዴዎች ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር በማበር በጦር መሳሪያ ንግድ እና ሌሎች ሕገወጥ ተግባራት እንደሚሳተፉ ግን አልሸሸጉም።
የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቅበላ እና አስተዳደር ላይ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የፌደራልም ሆነ የክልል ባለሥልጣናት በኩል ክፍተት በመኖሩ ምክንያት በውስጥ ጉዳይ ላይ በተለያየ መጠን እጃቸውን እንዲያስገቡ በር የከፈተ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ ለወደፊቱ ከተራ የጸጥታ ስጋትነት አልፎ ለሀገሪቱም የደህንነት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችልም ያሳስባሉ። የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ማኑስ ሁንደራ ስጋቱ ትክክለኛ ስጋት መሆኑን ይጋራሉ።
በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በውስጥ ግጭቶች ላይ ስለመሳተፋቸው እና የጦር መሳሪያ ንግድን ጨምሮ በተለያዩ ሕገውጥ ድርጊቶች ስለመሳተፋቸው ከጥርጣሬ የዘለሉ ተጨባጭ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ሊሆን የቻለውም በፌደራል መንግሥት እና በክልል አስተዳዳሪዎች የሚታየው የስደተኞች አያያዝ ክፍተቶች ስለመሆናቸው ነዋሪዎች እና ፖለቲከኞቹ አስረድተዋል። ይህ ለአገር የጸጥታ ችግር ሊሆን የሚችል ነገር በእንጭጩ ካልተቀጨ ነገ ጉዳዩ ሰፍቶ ሌላ መልክ ሊይዝ እንደሚችልም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ማኑስ ሁንደራ ያሳስባሉ። ቁጥጥሩ በዓለምአቀፍ መርሆው መሰረት መተግበር እንዳለበት በማከል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ