1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከእገታ የተመለሱትን ለማቋቋም የጋምቤላ ክልል ገቢ እያሰባሰበ ነው።

ማክሰኞ፣ መስከረም 9 2010

በ2008 ዓ.ም. ከደቡብ ሱዳን ድንበር የተሻገሩ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች አፍነው ከወሰዷቸው ሕጻናት መካከል 33ቱ ዛሬም አልተመለሱም። የክልሉ መንግሥት ርዕሰ-መሥተዳድር ታጣቂዎቹ አፍነው ከወሰዷቸው መካከል ወደ 100 ልጆች መመለሳቸውን ተናግረዋል። ክልሉ በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸውን ልጆች ለማቋቋም ገቢ እያሰባሰበ ነው። 

Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

ከእገታ የተመለሱትን ለማቋቋም ገቢ እየተሰበሰበ ነው

This browser does not support the audio element.

የደቡብ ሱዳን  የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው ከ200 በላይ ሰዎች የገደሉበት ጥቃት ከተፈጸመ 17 ወራት አለፉ። ሕጻናት እና እናቶች ላይ በከፋው ጥቃት ከ130 በላይ ታፍነው ተወስደዋል። ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአንድ አመት በኋላ ታፍነው ከተወሰዱት መካከል የተመለሱት 100 ገደማ ሕጻናት ብቻ ናቸው። የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መሥተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ኮች እንደሚሉት መንግሥታቸው ከ33 በላይ ሕጻናት የሚመለሱበትን ጊዜ ገና እየጠበቀ ነው።

"በአሁኑ ሰዓት ወደ 100 ልጆች ተመልሰዋል። 33 ቀሪዎች ናቸው። እነዚህ ይመለሳሉ። የእኛ መንግሥት እና የደቡብ ሱዳን መንግሥት ጥሩ ግንኙነት አላቸው። ስለዚህ ጥሩ ግንኙነት ስላለ አሁን የክረምት ወቅት ስለሆነ በበጋ ወራት አካባቢ እነዚህ ቀሪ የሆኑ ልጆች የሚመለሱበት ዘዴ ይፈጠራል። እሱ ብቻ አይደለም። ባለፈው የተወሰዱ ከብቶች አሉ። እነዚህ ከብቶች ተሰባስበው ለኢትዮጵያ ይመለሳል የሚል ስምምነት አለ።»

ምስል Anywaa Survival Organisation/Nyikaw Ochalla

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጥቃቱን "አሰቃቂ የሆነ ግድያ እና ጭፍጨፋ" ብለዉት ነበር።ይሁንና  የመንግሥታቸው የጸጥታ ኃይል የዜጎቹን ደኅንነት መጠበቅ ተስኖታል የሚል ትችት ሲሰነዘርበት ቆይቷል። ግድያ እና እገታው በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከልም ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት መፍጠሩ አልቀረም።ከ2008ቱ ጥቃት በኋላም የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ተመሳሳይ ድርጊት ፈፅመዋል። ጥር 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በድጋሚ በተፈጸመው ጥቃት አስራ አንድ ሰዎች ተገድለው ሕጻናት እና የቀንድ ከብት አግተው መውሰዳቸው ተሰምቷል።

የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ እንደሚሉት ከዚህ በኋላ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው ጥቃት ማድረስ አይችሉም። የመከላከያ ሰራዊት እና የክልሉ ልዩ ኃይል በጋምቤላ በኩል ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን በምትዋሰንባቸው አካባቢዎች ጥበቃ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።  

"አሁን በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ነው ያለው። በተለይ መዘጋት ያለባቸው ድንበሮች አካባቢ በሰራዊት ካምፖች እንዲዘጋ ተደርጓል። መከላከያ ሰራዊታችን በየድንበር አካባቢ የራሱ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየሰራ ነው። ሁለተኛ የክልሉ ልዩ ኃይል የራሱን ድንበራማ የሆኑ አካባቢዎች ለይቶ የራሳቸው ካምፖች አሉ። ሕዝብንም ጨምሮ የራሳችን ሚሊሺያዎች በየመንደሩ ተደራጅተዋል። ከዚህ በኋላ ሙርሌ ወደ ተፈለገ መንደር መግባት አይችልም ማለት ነው።"

የጋምቤላ ክልል ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በተገኙበት ከእገታ የተመለሱ ሕጻናትን ለማቋቋም ገቢ ማሰባሰብ ጀምሯል። ቤተሰቦቻቸው በጥቃቱ የተገደሉባቸው 100 ሕጻናት አሁን በአኙዋክ ብሔረሰብ ዞን ጎክ ወረዳ፤ በንዌር ብሔረሰብ ዞን ላሬ እና ጀኮብ ወረዳ ይገኛሉ። 

አቶ ጋትሉዋክ ሕጻናቱ ችግሮች እንዳይገጥማቸው የምግብ፤የትምህርት እና የጤና አገልግሎት በአንድ ቦታ የሚያገኙበት አዳሪ ትምህርት ቤት ለማቋቋም መታቀዱን ተናግረዋል። በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት በተጀመረው የገቢያ ማሰባሰቢያ "ከ75 ሚሊየን ብር በላይ በገንዘብና በአይነት"ለመደጎም ቃል መገባቱ ተሰምቷል። 
እሸቴ በቀለ 
ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW