1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግማሽ ሚሊዮን ዜጎች ወደ ውጭ አገራት መላክ የሚጨምረው የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ፈጠራ ዕቅድ

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ መስከረም 30 2016

ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ “በ2016 በሕጋዊ መንገድ በአምስት የመዳረሻ አገራት ለ500 ሺሕ ሰዎች የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ለመፍጠር” እንደሚሰራ ገልጸዋል። ይኸ በዓመቱ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሥራ ለመፍጠር የወጠነው የመንግሥት ዕቅድ አካል ነው። በመካከለኛው ምሥራቅ ኢትዮጵያውያን የሚገጥማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ግን ለመብት ተሟጋቾች አሳሳቢ ነው።

በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመጓዝ የሚጠባበቁ ኢትዮጵያውያን
ምስል Eshete Bekele/DW

ግማሽ ሚሊዮን ዜጎች ወደ ውጭ አገራት መላክ የሚጨምረው የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ፈጠራ ዕቅድ

This browser does not support the audio element.

በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሥር በሚገኘው “የውጭ ሃገር የሥራ ዕድሎች በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት” እስከ ዛሬ መስከረም 30 ቀን 2016 ድረስ ብቻ ከ269 ሺሕ በላይ ሥራ ፈላጊዎች ተመዝግበዋል። ይኸ ሥርዓት ወደ ውጭ አገራት የሚጓዙ ሥራ ፈላጊዎችን የእጅ እና የአይን አሻራ ይሰንዳል። ኢትዮጵያውያኑ ከቀጣሪዎቻቸው ጋር የሚኖራቸውን የሥራ ውል ጭምር ይቀበላል። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድረ-ገጽ የሰፈረ መረጃ እንደሚጠቁመው ይኸ ሥርዓት “የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል” የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአውሮፓ አገራትን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለማሰማራት የተበጀ ነው።

ይኸ ሥርዓት የኢትዮጵያውያንን “ደህንነት እና ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንዲሁም ብልሹ አሰራርን መቀነስ” የሚያስችል እንደሆነ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ያትታል። በዚህ ሥርዓት ከ100 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈላጊዎች ወደ ውጭ አገራት እንደተጓዙ በድረ-ገጹ የሠፈረው መረጃ ይጠቁማል።

ጦርነት አማራጭ ሆኖ መቅረብ የለበትም"ርዕሠ-ብሔር ሣኅለወርቅ ዘውዴ

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ለሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት መስከረም 28 ቀን 2016 ባደረጉት ንግግር ባለፈው ዓመት “የውጭ አገር የሥራ ስምሪትን ሕጋዊ ማዕቀፍ በማበጀት 102 ሺሕ ዜጎች ተጠቃሚ” መሆናቸን ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቷ “በ2016 በውጭ አገራት በሕጋዊ መንገድ በአምስት የመዳረሻ አገራት ለ500 ሺሕ ሰዎች የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ለመፍጠር የሚሰራ ይሆናል” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን መንግሥት ዕቅድ ጠቁመዋል።

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ “በ2016 በውጭ አገራት በሕጋዊ መንገድ በአምስት የመዳረሻ አገራት ለ500 ሺሕ ሰዎች የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ለመፍጠር የሚሰራ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በ2016 የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያተኩርባቸውን አንኳር ጉዳዮች ባስረዱበት ንግግራቸው አምስቱ አገራት የትኞቹ እንደሆኑ አልጠቀሱም። ኢትዮጵያውያን ለሥራ ይጓዙባቸዋል ከተባሉት መካከል ሊባኖስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዮርዳኖስ፣ ባህሬን፣ ኦማን፣ ጀርመን እና ደቡብ ሱዳን ይገኙበታል።

ኢትዮጵያውያን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚጓዙበትን ሒደት ለመቆጣጠር የዘረጋው ሥርዓት ሥራ ፈላጊዎች በመንገድ ላይ የሚገጥማቸውን እንግልት ሊያስቀር እንደሚችል የምትስማማው ባንቺ ይመር በቀጣሪዎቻቸው ቤት ከሚጠብቃቸው ፈተና ግን እንደማይታደጋቸው ትሞግታለች። ኢትዮጵያውያኑ በሕጋዊ መንገድ መጓዛቸው “መንገድ ላይ የሚደርስባቸውን አስገድዶ መድፈር እና ድባደባ የመሳሰሉ ችግሮች ያስቀረዋል” የምትለው ባንቺ ከመዳረሻቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ያለውን ፈተና እንደማያስቀረው ታስረዳለች።

ኢትዮጵያውያኑ ዶላር፣ ሥራ እና መመለሻ በጠፋባት ሊባኖስ

ባንቺ ለሰባት ዓመታት በሊባኖስ ከመስራቷም ባሻገር ባቋቋመችው “እኛ ለእኛ በስደት” የተባለ ድርጅት በኩል በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ለሚገኙ የቤት ሠራተኞች መብት የምትሟገት ናት። ኢትዮጵያውያኑ ተቀጥረው በሚሰሩባቸው ቤቶች ውስጥ “ያለውን ችግር የከፋላ ሥርዓት እስካልተነሳ ድረስ ወይም ልጆቹ አገራቸው እስካልተቀመጡ ድረስ ማንም ሊፈታው አይችልም” የምትለው የእኛ ለእኛ በስደት መስራች እና ዳይሬክተር “ድብደባ አለ። አስገድዶ መደፈር አለ፤ የሰሩበትን መከልከል አለ” ስትል ተናግራለች።

“አብዛኛዎቹ ልጆቻችን በሩ ተቆልፎ ነው የሚቀመጡት። ‘የት ነው ያላችሁት?’ እንኳ ብትላቸው [ተቀጥረው] የሚገቡበትን ቤት እንኳ አያውቁትም” በማለት ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች የሚኖሩበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ተናግራለች።

በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በርካታ ልጅ እግር ወጣቶች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚያጉዛቸውን አውሮፕላን ለመሳፈር ሲጠባበቁ ይታያል። ወጣቶቹ የሚጓዙባቸው አገራት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች ላይ አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች የተፈጸመባቸው ናቸው። ምስል Eshete Bekele/DW

ሰሚ ያጡ የወሲባዊ ትንኮሳ ሰለባዎች በሊባኖስ

ባንቺ በዋና ዳይሬክተርነት የምትመራው ተቋም በሊባኖስ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት ባከናወነው ጥናት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በሊባኖስ የሚገኙ ሴት የቤት ሠራተኞች አስገድዶ መደፈርን ጨምሮ የተለያዩ ወሲባዊ ትንኮሳዎች እንደሚፈጸሙባቸው አጋልጧል። ሥራ ፍለጋ መደበኛ እና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተጓዙ ኢትዮጵያውያን ስድብ፣ ድብደባ እና እስር እንደተፈጸመባቸው ከዚህ ቀደም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ሊባኖስ እና ሳዑዲ አረቢያን በመሳሰሉ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውን በደል እንዲህ በቀላሉ ለየአገራቱ መንግሥታት አቤት ማለት አይችሉም። ለዚህ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ በመሳሰሉ አገራት የውጭ አገራት ሠራተኞችን ለመቆጣጠር የሚከተሉት “ከፋላ” የተባለ ሥርዓት ፈተና ነው። ባንቺ ይመር ይኸን ሥርዓት “ከዘጠኝ በላይ አገራት የሰው ልጅን እንደ ባሪያ የሚገዙበት ሥርዓት” ስትል ትገልጸዋለች።

ባንቺ እንደምትለው ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ከአንድ ሰው ጋር ውል ፈጽመው ወደ አንድ የአረብ አገር ካመሩ በኋላ ያለ አሰሪዎቻቸ ፈቃድ ወደ አገራቸው መመለስም ይሁን ሥራ መቀየር አይችሉም። ኢትዮጵያውያኑ የመደብደብ፣ አስገድዶ የመደፈር አሊያም አንዳች ችግር ደርሶባቸው ከሚሰሩበት ቤት ቢወጡ አሰሪዎች “በማንኛውም ሰዓት ደውለው ማሳሰር ይችላሉ።” የእኛ ለእኛ በስደት መስራች እና ዳይሬክተር የከፋላ ሥርዓትን የሚከተሉ አገራት “ዘመናዊ ባርነትን ሕጋዊ አድርገው ዜጋቸው የሚጠቀምበትን እኛ [ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች] የምንጎዳበትን መንገድ ነው ያመቻቹት” ስትል ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች።

ሊባኖስ እና ሳዑዲ አረቢያን በመሳሰሉ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውን በደል እንዲህ በቀላሉ ለየአገራቱ መንግሥታት አቤት ማለት አይችሉም። ለዚህ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ በመሳሰሉ አገራት የውጭ አገራት ሠራተኞችን ለመቆጣጠር የሚከተሉት “ከፋላ” የተባለ ሥርዓት ፈተና ነው።ምስል Eshete Bekele/DW

ከድህነት ግብግብ ገጥመው የከሸፉ ህልሞች- ሳዑዲ አረቢያ ደርሶ መልስ

ፕሬዝደን ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ይፋ ያደረጉት ግማሽ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጭ አገራት የመላክ ዕቅድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የሥራ ፈጠራ ጥረት አንድ አካል ነው። ፕሬዝዳንቷ “በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ 9.15 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚሰራ ይሆናል። በ2016 የበጀት ዓመት ለ3.05 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንሰራለን” ሲሉ ለሁለቱ ምክር ቤቶች አስረድተዋል።

በፕሬዝደንቷ ማብራሪያ መሠረት ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ 3.5 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የተያዘው ዕቅድ እንደ 2015 ሁሉ በዓመት ሦስት ሚሊዮን ገደማ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ ነው። “ኤኮኖሚው እየተንቀሳቀሰ አይደለም። የዋጋ ንረት በጣም እየጨመረ ነው። ሰዎች መኖር እያቃታቸው ነው። ያሉት ኢንቨስተሮች ራሳቸው ተጨማሪ ሠራተኛ መቅጠር ቀርቶ ያለውንም ሠራተኛ በአግባቡ መያዝ አልቻሉም። አንዳንድ ጊዜ ሠራተኞቻቸውን የሚቀንሱበት አጋጣሚዎችም ይኖራሉ” የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ፋንቱ ጉታ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊቸገር እንደሚችል ያምናሉ። ዶክተር ፋንቱ “አሁን ያለው የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ መፍትሔ ካላገኘ እኔ ይኸን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ይቻላል የሚል ዕምነት የለኝም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የጸጥታ ቀውስ መፍትሔ ባያገኝም የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት በተያዘው ዓመት በ7.9 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ተናግረዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በበኩሉ ሊገባደድ ሁለት ወራት በቀሩት የጎርጎሮሳዊው 2023 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት 6 ነጥብ 1 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይፋ አድርጓል።ምስል AFP/E. Jiregna

ዶክተር ፋንቱ የጠቀሱት የኢትዮጵያ “የሰላም ሁኔታ” ለዕቅዱ መሳካት በእርግጥም ሁነኛ ፈተና መጋረጡ አይቀርም። በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት በበረታበት የአማራ ክልል እንኳ 1,226 ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዳስትሪዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸው ሥራ ማቆማቸውን የአማራ ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል።

በአማራ ክልል 1,226 ፋብሪካዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ሥራ አቁመዋል

መንግሥት ሊፈጥር የሚችለው የተወሰነ የሥራ ዕድል ሊሆን እንደሚችል የገለጹት ዶክተር ፋንቱ “ለግሉ ዘርፍ አመቺ ከባቢ ተፈጥሮ ሰዎች ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ ካልተደረገ አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር ቀርቶ የነበረውንም ማስቀጠል ይከብዳል” ሲሉ ተናግረዋል። “እንኳን አዳዲስ ኩባንያዎች [ለኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ] ሊገቡ ቀርቶ ያሉትም እየተንቀሳቀሱ አይደለም” ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሐብት ምሁር የፋይናንስ፣ የጸጥታ፣ የግብዓት እጥረት ፈተናዎች ጭምር እንዳሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የጸጥታ ቀውስ መፍትሔ ባያገኝም የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት በተያዘው ዓመት በ7.9 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ተናግረዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በበኩሉ ሊገባደድ ሁለት ወራት በቀሩት የጎርጎሮሳዊው 2023 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት 6 ነጥብ 1 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይፋ አድርጓል።ድርጅቱ ትላንት ማክሰኞ ይፋ ባደረገው የአገራት የምጣኔ ሐብት ዕድገት ትንበያ መሠረት በ2024 የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ 6 ነጥብ 2 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW