ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረው የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት
ረቡዕ፣ ግንቦት 20 2017
የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት በእንግሊዝኛው ምህፃሩ (ESA) በዚህ ወር 50ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዝግጅት ድርጅቱ ባለፉት 50 ዓመታት በርካታ ውጤቶች አስመዝግቧል።
የድርጅቱ አጀማመር
በጎርጎሪያኑ ግንቦት 30 ቀን 1975 የተመሰረተው የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት በእንግሊዝኛው ምህፃሩ (ESA) በዚህ ወር 50ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው።የአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ ከ50 ዓመት በፊት፤በ10 መስራች ሃገሮች ስምምነት በይፋ የተመሰረተ ቢሆንም፤ ታሪኩ ግን ከዚህ ቀደም ይላል።
ድርጅቱ የተመሰረተው በ1960ዎቹ የተመሰረቱ ሁለት የአውሮፓ የጠፈር ድርጅቶችን በማዋሃድ ነው። የመጀመሪያው የአውሮፓ የጠፈር ልማት ድርጅት (ELDO) ሲሆን፤ ከባድ ሳተላይቶችን ለማምጠቅ የሚያስችሉ ሮኬቶችን ለመስራት በስድስት የአውሮፓ ሀገራት የጋራ ጥረት የተመሰረተ ነበር።ሁለተኛው፣ የአውሮፓ የጠፈር ምርምር ድርጅት (ESRO) ደግሞ ፤በብዛት የሚያተኩረው ሳተላይት ማምጠቅ ይልቅ፤ በኅዋ ሳይንስ ላይ ነበር። ድርጅቱ የተቋቋመው የአውሮፓ የፊዚክስ ትብብር እና የአውሮፓ የኑክሌር ምርምር ድርጅትን ወይም ( CERN)ን ባቋቋሙት የሳይንስ ተመራማሪዎች ነበር።
የዓለም አቀፉ የአስትሮናውቶች ህብረት ምክትል ሊቀመንበር እና የህዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ሰለሞን በላይ፤እንደሚሉት የድርጅቱ መመስረት በዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ የድርጅቱ መመስረት የአውሮፓ ሳይንቲስቶች ሩቅ ሳይሄዱ አውሮፓ ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ እና እንዲመራመሩ ጥሩ እድል መፍጠሩንም ገልፀዋል።
የድርጅቱ የሃምሳ ዓመታት ስኬቶች
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የተመሰረተው ይህ ኤጀንሲ በቁልፍ ተግባራት ላይ የመተባበር ራዕይን ይዞ ነበር የመጣው።ይህም የሳይንስ እና የሥነ-ፈለክ ፣ የሳተላይት ማምጠቅ አቅም እና የህዋ አሰሳን ያካትታል።ባለፉት 50 ዓመታትም በሳይንስ ፣ በጠፈር አሰሳ ፣በቴክኖሎጂ እና አውሮፓ ጉልበት በሆነው የህዋ መሠረተ ልማት እና ኢኮኖሚ ላይ አዳዲስ ግኝቶችን እና የጋራ ስኬቶችን አስመዝግቧል። የአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት እና ተጨማሪ አባል ሀገራትን በማካተት ከፍተኛ እድገት አሳይቷል።በአሁኑ ወቅት ከመላው አውሮፓ 22 አባላት አሉት።ስሎቬኒያ ባለፈው ጥር የመጨረሻዋ ሙሉ አባል ሀገር ሆና ተቀላቅላለች።
ከአውሮፓ የጠፈር ድርጅት ሚሼል ዴብራይን፣ በድርጅቱ አስፈላጊነት ላይ አፅንኦት ይሰጣሉ።«አሁን ብዙ ተዋናዮች አሉ ። ቻይና ፣ አሜሪካ የራሳቸው ፖሊሲ አላቸው። ሩሲያ ፣ ከአሁን በኋላ ከዚህ አታመጥቅም። ስለዚህ የራሳችን የህዋመዳረሻ እና ስልት መኖሩ አስፈላጊ ነው።»ብለዋል።
የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት ስራዎች በከፊል
ድርጅቱ፤የአውሮፓ ሀገራትን በአንድነት በማሰባሰብ፤ ህዋን እዲያስሱ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲጠቀሙበት ያደርጋል። ድርጅቱ ሳይንሳዊ ምርምርን ያካሂዳል፣ ሳተላይቶችን ያንቀሳቅሳል እና የምርምር ሮኬቶችን እና እንደ ንግድየጠፈር ጉዞያሉ የህዋ መርሃ ግብሮችንም ያስተባብራል።የምንኖርባትን ፕላኔት መሬትን እና ከዚያ ባሻገር ያለውን አፅናፈ ዓለም ወይም «ዩኒቨርስ» ለማሰስ ተልእኮዎችን ያዘጋጃል።በማርስ ዙሪያ ምህዋር እንዲሁም ወደ ሜርኩሪ እና ጁፒተር በሚወስደው መንገድ ደግሞ ፍተሻዎች አሉት። የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት የጠፈር ቴሌስኮፖች የአጽናፈ ሰማይን እና የጋላክሲዎችን/ የክዋክብት ጥርቅም/ ታሪክ ይመረምራሉ።ሳተላይቶቹ የምድርን ጂኦሎጂ እና ስነ-ምህዳር ይቆጣጠራሉ።የድርጅቱ የጠፈር ተመራማሪዎችም ወደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ (ISS) መንኮራኩር ይዘው ይመጥቃሉ። ያም ሆኖ የኖቫስፔስ የተባለው የግል የሳተላይት ጣቢያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፓኮሜ ሬቪሎን እንደሚሉት ከሌሎች ጋር ሲነፃጸር የተሰራው ስራ በቂ አይለም።
«ስፔስ X በዓመት ቢያንስ 100 ሮኬቶችን ያመጥቃል። አውሮፓ ግን በዓመት 10 ያህል ሮኬቶችን ለማስወንጨፍ አቅዳለች ።ይህ የሚወዳደር አይደለም። እና አብዛኛዎቹ ጥቃቅን ጅማሬዎች እስካሁን ንግድ ደረጃ ላይ አልደረሱም ። ዝግጁም አይደሉም።»በማለት ገልፀዋል።
በቅርቡም የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት «አርጎኖውት» የተባለው ፕሮግራሙ አካል በማድረግ የመጀመሪያውን የጠፈር መንኮራኩር በጨረቃ ላይ ያሳርፋል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም ድርጅቱ የማርስን ያለፈ ታሪክ በተሻለ ለመረዳት ይሰራል ። በጎርጎሪያኑ በመጭው 2026 ዓ/ም ደግሞ፤በሌሎች ክዋክብት ዙሪያ አዳዲስ ዓለሞችን ለማግኘት ፕሉቶ /PLATO /የተባለውን ተልዕኮ ይጀምራል።
የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት እንደ አሪያን 6 /Ariane 6/እና ቪጋ-ሲ /Vega-C/ያሉ ኃይለኛ የጠፈር መንኮራኩሮችን እና አዲስ የሳተላይት ግንኙነት እና የአሰሳ ቴክኖሎጂዎችን ያዳብራል።ከአሰሳ ባሻገር፣ ድርጅቱ፤በመሰረታዊ ጥናትና ምርምር እና የግል ኢንዱስትሪን በመደገፍ የአውሮፓን አቅም ለመገንባት ይሰራል።ዶክተር ሶለሞን እንደሚሉት ለአዳጊ ሀገራት ጠቃሚ በሆነው የምድር ምልከታ ላይ ድርጅቱ የሚሰራው ምርምር ከሌሎቹ የጠፈር ድርጅቶች የተሻለ ነው ይላሉ።
ድምፅ2- ዶክተር ሶለሞን በላይ
የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት አባል ሀገራት
የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት በአውሮፓ እስካሁን ትልቁ ድርጅት ቢሆንም ብቸኛው ግን አይደለም። ብዙዎቹ የድርጅቱ አባል ሀገራት የራሳቸው ብሄራዊ የጠፈር ድርጅቶች አሏቸው።በሌላ በኩል የአውሮፓ ህብረት የህዋ መርሃ ግብር(EUSPA) ያሉ አህጉራዊ ድርጅቶችም አሉ።ይህም በአሰሳ እና የሳተላይት ሲስተሞችን ማስተዳደር ባሉ ስራዎች ላይ የበለጠ ያተኩራል፣ የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት ደግሞ በህዋ መሠረተ ልማት ዲዛይን እና ልማት ላይ የበለጠ ያተኩራል።ምክንያቱም ይላሉ ፈረንሳይ ጉያና የሚገኘው የጠፈር ማዕከል ዳይሬክተር ፊሊፕ ሊየር ህዋ ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው።
«በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ነገር በሳተላይት ነው የሚከናወነው -ቴሌኮሙኒኬሽን, የአየር ሁኔታ ትንበያ፣ የአየር ንብረት ጥናት ወዘተ. እና ስለዚህ ህዋ ወደ ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፍ ተቀይሯል። ለዚህም የራሳችን መዳረሻ እና ለስራው ተስማሚ የሆነ የጠፈር መዳረሻ እንፈልጋለን።» ብለዋል።
ምንም እንኳ የድርጅቱን በጄት 20 በመቶ የአውሮፓ ህብረት የሚሸፍነው ቢሆንም፤ የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት ከህብረቱ የተለዬ ነው።ከዚህ አኳያ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ያሉ ነገር ግን በድርጅቱ ውስጥ የሌሉ ሀገራት አሉ።አንዳንድ አገሮች ደግሞ በአውሮፓ ህብረት አባል ሳይሆኑ፤በድርጅቱ ውስጥ በአባልነት ይሳተፋሉ።
በአንድ ወቅት ግን የጠፈር ምርምር ድርጅቱን የአውሮፓ ህብረት ኤጀንሲ ለማድረግ እቅድ ነበረው።የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ፈረንሳይ በፓሪስ፣ ሲሆን፤ ኤጀንሲው በአውሮፓ ዙሪያ ሌሎች በርካታ ማዕከላት እና በፈረንሳይ ጊያና የጠፈር ምርምር ጣቢያ አለው።የጠፈር ማዕከሉ ዳይሬክተር ፊሊፕ ሊየር ድርጅቱ አቅም የማሳደግ እቅድ አለው።
«በሚቀጥለው ዓመት ዘጠኝ በረራዎችን ይፋ እናደርጋለን። በረዥም ጊዜ ዕቅድ ደግሞ በየዓመቱ 15 ወይም ከዚያ በላይ በረራዎችን ኢላማ እናደርጋለን። በምንገነባው ጣቢያ ላይ ማይክሮ-ላውንቸርን እናካትታለን። እነዚህ የግል ሮኬቶች አነስተኛ አቅም አላቸው። ነገር ግን ወደ ህዋ ብዙ ተጨማሪዎችን በየዓመቱ መላክ ይችላሉ።»ብለዋል።
የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት ባለፉት 50 ዓመታት ያስመዘገባቸው ጥሩ ውጤቶች ቢኖሩም ዘርፉ ከመተባበር ይልቅ ውድድር የሚያመዝንበት በመሆኑ፤እንደ አቶ ሰለሞን ለአውሮፓ የጠፈር ድርጅት ተግዳሮቱ ቀላል አይደለም።በመሆኑም ድርጅቱ ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት ችግሮች በመገምገም ከሌሎች ጋር ተባብሮ የሚሰራበትን መንገድ መፍጠር የተሻለ መሆኑን የህዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ሰለሞን በላይ ገልፀዋል።
የድርጅቱ አሰራር
የአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ በብዙ ሀገሮች መካከል የሚካሄድ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከመላው አውሮፓ 22 አባላት አሉት።ከዚህ በተጨማሪ አራት ተባባሪ አባላት ያሉት ሲሆን ካናዳ ከድርጅቱ ጋር በትብብር ትሰራለች።ድርጅቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ፣ በጀት እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ለመወሰን እነዚህ ሀገራት እያንዳንዳቸው በድርጅቱ የአስተዳደር ምክር ቤት አንድ ድምጽ ያገኛሉ።
ፀሐይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ