1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግሪክ ከምክር ቤታዊዉ ምርጫ ማግስት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2004

የትናንቱ የፈረንሳይ እና የግሪክ ምርጫ ዛሬ ጠዋት የአውሮፓን ገበያ አናግቷል። የአክስዮን ገበያ ወደታች አቆልቁሏል። መንስኤው ደግሞ በተለይ በግሪክ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ነው።

Women casts their ballots at a polling station in Athens, Sunday, May 6, 2012. Greeks are voting in elections critical to getting international bailout support as angry voters appear more than ready to punish both major parties for the country's decimated economy. (Foto:Thanassis Stavrakis/AP/dapd)
ምስል dapd

በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን  በከፍተኛ ዕዳ ተወጥራ በምትገኘው ግሪክም ትናንት ምርጫ ተካሂዷል። የግሪኩ  እንደ ፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሳይሆን የምክር ቤት ምርጫ ነው። ሁለቱም ጠንካራ የግሪክ ፓርቲዎች አብላጫ ድምፅ ካላገኙበት ከትናንቱ ምርጫ በኋላ ፓርቲዎች በመጣመር መንግስት ለማቋቋም ለሶስት ቀናት የሚቆይ ጉባኤ ዛሬ በአቴንስ ከፍተዋል።  በነዚህ ቀናት ውስጥ ጠንካራው ፓርቲ አዲስ መንግስት ለመመስረት ካልተሳካለት ሁለተኛው ጠንካራ ፓርቲ ውክልናውን ያገኛል።ከምርጫ ድምፁ ቆጠራ በኋላ ወግ አጥባቂው ኔያ ዴሞክራቲያ ፓርቲ 18,9 ከመቶ ሲያገኝ ሶሻሊስቱ ፓርቲ «ፓሶክ»  13,2 ከመቶ ብቻ ነው ያገኘው።  ሁለተኛ ጠንካራ ፓርቲ በመሆን 16,76 ከመቶ ያገኘው ደግሞ የግራው ፓርቲ ነው። የግራው ፓርቲ ግሪኪን ከውድቀት ለማዳን የተነደፈዉን አለም አቀፍ  መርሃ ግብር  ያጣጥላል።

በግሪክ ባለው አስከፊ የኤኮኖሚ ድቀትና ጠንካራ የቁጠባ መርሆ የተነሣ ፓርቲዎቹ ብዙ የሕዝብ ድምፅ እንደማያገኙ ቀደም ብሎ ቢታወቅም፤ ወግ አጥባቂዎቹ ግን ይህን ያህል ድምፅ እናጣለን ብለው አልገመቱም። ምንም እንኳ በጥቅል ይዞታዉ ሲታይ ወግ አጥባቂው ፓርቲ ከሁሉም ጠንካራው ቢሆንም የፓርቲው ሊቀመንበር አንቶኒስ ሳማራስ ከህዝቡ የጠበቁትን ማጣታቸዉን አልሸሸጉም « ጠንካራ ኃላፊነት ጠይቀን ነበር። የግሪካውያን ውሳኔ ግን ሌላ ሆኗል። መልዕክቱን አከብራለሁ። ሁለት አላማ ያለው አገር ለማዳን የቆመ ብሔራዊ መንግስት ለመመስረት ዝግጁ ነን። ይኸዉም በዩሮ ተጠቃሚዎች ቀጣና ለመቆየትና  አገሪቷን ከውድቀት አድኖ እድገት ለማስመዝገብ በወጣዉ መርሃ ግብር  ለመደራደር ይሆናል።»

አንቶኒስ ሳማራስምስል picture-alliance/dpa

እሳቸዉ ይህን ሲሉ በምርጫዉ ሁለተኛዉ ጠንካራ ፓርቲ በመሆን ድምፅ ያገኘው የግራው ፓርቲ የበላይ አሌክሲስ ሲፕራስ በበኩላቸዉ ግሪክን ከውድቀት ያድናል በሚል የተቀረፀዉን  መርሃ ግብር ጨርሰው  ውድቅ ያደርጋሉ። « ይህ የምርጫ ውጤት በግሪክ እና በመላዉ አውሮፓ  ለውጥ መምጣቱን አመላካች ነዉ። የአውሮፓ አገሮች ይህንን ኢሰብዓዊ የሆነ የቁጠባ ፕሮግራም መቀበል የለባቸውም። የአውሮፓ የፖለቲካ መሪዎች፤ በተለይም አንጌላ ሜርክል የቁጠባ እቅዱ ሽንፈት እንደገጠመዉ መቀበል ይኖርባቸዋል።»

አሌክሲስ ሲፕራስምስል Reuters

የምርጫዉ ዉጤት ግራ ሊያጋባ አይገባም ያሉትየጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ግሪክ በቁጠባው መርሃ ግብር ብትቀጥል እንደሚያዋጣ  አመልክተዋል። ግሪካውያን ተረጋግተው የምርጫ ውጤቱን ማጤን እንደሚኖርባቸዉም አሳስበዋል።

ተፈላጊዉን አብላጫ ድምፅ ያላገኙት ሁለቱ የግሪክ ፓርቲዎች፤  አዲስ ጥምር መንግስት ለመመስረት ካልቻሉ ሰኔ አጋማሽ አዲስ ምክር ቤታዊ ምርጫ ይካሄዳል።

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW