1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብጽን ያንደረደረው ውጥረት በሶማሊያና ኢትዮጵያ መካከል

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 2 2016

ግብጽ ከሰሞኑ የጦር መሣሪያዎችን በወታደራዊ አውሮፕላን ጭና ሞቃዲሾ ማስገባቷ ይፋ ከሆነ በኋላ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ወታደራዊ ፍጥጫው እጅግ አይሏል ። ሁኔታዎች ወደየት እያመሩ ይሆን?

 በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ወታደራዊ ፍጥጫው እጅግ አይሏል ። ፎቶ፦ ከማኅደር
 በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ወታደራዊ ፍጥጫው እጅግ አይሏል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Solomon Muche/DW

የኢትዮጵያ እና ግብጽን ከፊት ያሰለፈችው ሶማሊያ ፍጥጫ

This browser does not support the audio element.

ግብጽ ከሰሞኑ የጦር መሣሪያዎችን በወታደራዊ አውሮፕላን ጭና ሞቃዲሾ ማስገባቷ ይፋ ከሆነ በኋላ  በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ወታደራዊ ፍጥጫው እጅግ አይሏል ። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ወታደራዊ ጡንቻ ማሳየቱ እና ፉከራው በየፊናው ቀጥሏል ።  ትንታኔውም በየአቅጣጫው እየተሰጠ ነው ። ግብጽም ሆነች ኢትዮጵያ ግን ሶማሊያ ውስጥ እና ሶማሊያ ድንበር ላይ ጡንቻቸውን በተለያየ መንገድ ለማሳየት የሚጥሩት ውስጣዊ የፖለቲካ ውጥረታቸውን ለማስቀየስ ነው የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ ። ሌሎች ደግሞ ግብጽ ወደ ሶማሊያ የተጠጋችው በ«ታላቁ ሕዳሴ ግድብ» ግንባታ እና የውኃ ሙሌት ሒደት ቀድሞም ደስተኛ ባለመሆኗ ነው ሲሉ ይደመጣሉ ። 

የኢትዮጵያ እና ግብጽን ከፊት ያሰለፈችው ሶማሊያ ፍጥጫ

ሣሚራ ጋይድ በአፍሪቃ ቀንድ ተንታኝነት ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱ ባለሞያ ናቸው ። የሶማሊያ ፌዴራል ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚንሥትር ዋና የደሕንነት አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል ።  ግብጽ ወትሮም ቢሆን ሶማሊያ ድረስ የሚያንደረድራት ጥብቅ ምክንያት አላት ባይ ናቸው ።

«ግብጽ ሁኔታውን በጥሩ መልኩ ነው የተቀበለችው ምክንያቱም ግብጽ ከኢትዮጵያ ቀድሞውንም የሚያቆራቁሳት ጉዳይ  አላት ማለት ይቻላል እዚህ በሌላ አቅጣጫ በሚገኘው የኢትዮጵያ ድንበር ላይ መገኘት የፈለገችበት ምክንያት ከናይል ወንዝ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የተያያዘ ፖለቲካም ጭምር ነው »

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ። ፎቶ ከማኅደርምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

ግብጽ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አምስተኛ ዙር የውኃ ሙሌትን ተቀባይነት የለውም በማለት  ውድቅ ማድረጓና ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በቅርቡ አቤት ማለቷ ይታወቃል ። ግብጽ ወደ ሶማሊያ በተጠጋችበት ብሎም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ባሳየችበት ቅጽበት የኢትዮጵያ ወታደራዊ ባለሥልጣናት የአጸፌታ የሚመስሉ ንግግሮችን አሰምተዋል ። የኢትዮጵያ ጦር የምሥራቅ ዕዝ የተመሠረተበት 47ኛ ዓመት በዓል ሐሙስ ዕለት በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ዉስጥ በከፍተኛ ድግስና ወታደራዊ ሥርዓት ሲከበር ለሶማሊያ እና ግብጽ የሚመስል ጠንካራ መልእክት ተላልፏል ። በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም፣ ምክትላቸዉ፣ የልዩ ልዩ ኃይል አዛዦችና የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ባለስልጣናት ተገኝተው ነበር ። የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ሌትናንት ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ጦራቸዉ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል ።

ወታደራዊ ጡንቻ ማሳየቱ እና ፉከራው ቀጥሏል

«በሌላ ቦታ ላይም እንደዚሁ ግዳጁን በሚገባ እየፈፀመ ያለ ዕዝ ነዉ ሥለዚሕ በዉስጥም ሆነ በዉጪ ለሚመጣዉ ጥቃት በሚገባ መምታት በሚያስችል ቁመናና ዝግጅነት ላይ ያለ ዕዝ መሆኑን ነዉ መግለፅ የሚቻለዉ »

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Angela Weiss/AFP/Getty Images

ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፦  ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት በሰላም ለመፍታት  እስከመጨረሻው እንደምትገፋበት ቀደም ሲል ዐሳውቀዋል ። በሶማሊላንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት አዲስ አምባሳደር እንደተሾመለትም ባለፈው ሳምንት ይፋ ሆኗል ።

ዶ/ር ጃማ ሙሴ ጃማ የሶማሌላንድ ፖለቲከኛ፤ የባሕል እና የሒሳብ ባለሞያ ናቸው ። የኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ግንኙነት እንደውም በአሁኑ ወቅት ይበልጥ ይጠናከራል ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። ግብጽ ከሶማሊያ ጋ ወታደራዊ ትብብር ከማድረግም አልፋ ጦር መሣሪያ ለሶማሊያ ማቀበል መጀመሯ ግን ሌላ ዳፋ ማስከተሉ አይቀርም ብለዋል ።

«በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ የአፍሪቃ ቀንድ ላይ እጅግ ወደተዳከመ ሀገር ጦር መሣሪያ ካስገባህ፤ ችግሩን የበለጠ እንደሚያወሳስበው ግልጽ ነው ይህ ችግር ከዚህ ቀደምም ታይቷል የጦር መሣሪያ ሲገባ በሆነ መንገድ አልሸባብ እጅ ላይ ነው የሚወድቀው »

ግብጽ በሌሎች ሃገራት ስለነበራት ጣልቃ ገብነት የዓረቢኛ ድረገጾች

ዘአ አረብ ዊክሊ የተሰኘው ድረገጽ ግብጽ እና ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጉዳይ መወዛገባቸውን በተመለከተ ባቀረበው ሐተታ የግብጽን ቀደም ያሉ በሌሎች ሃገራት የታዩ ጣልቃ ገብነቶች ቃኝቷል ። ግብጽ፦ በ«ምሥራቃዊ ሊቢያ፤ ሱዳን እና በተለይ ደግሞ ጋዛ ውስጥ እንዲያ ድምፁዋን ከፍ አድርጋ ካሰማች በኋላ» በአቋሟ ሳትጸና መወላወሏን ጠቅሶም ትንታኔ አስነብቧል ። እንደውም የካይሮ ባለሥልጣናት ቱርኮች አፍንጫቸው ሱዳን ድረስ መጥተው በሱዋኪን የወታደራዊ ጦር ሰፈር ስምምነት ሲፈራረሙ አንዳችም ያደረጉት ነገር የለም ሲልም አክሏል ። ሱዋኪን በዖቶማን ግዛት ዘመን ቱርክ በሱዳን ቀይ ባሕር ዳርቻ ትቆጣጠረው የነበረ የወደብ ከተማ ነው ።

ከግብፅ ጋ የተወዳጀችው ቱርክ ከሶማሊያ ጋ ጥብቅ ግንኙነት አላትምስል Stuart Price/au-Un Ist/dpa/picture alliance

የቱርክ መንግሥት ሶማሊያ ተጉዞ በጥብቅ ከተወዳጃቸው ካታሮች ጋ በመተባበር ስምምነት ላይ ሲደርስ ግብጽ ምንም ያደረገችው ነገር የለምም ብሏል ። ሆኖም ግብጽ ሶማሊያ ግዛቴ ከምትላት ዓለም አቀፍ የመንግሥትነት ዕዉቅና ከሌላት ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋ ኢትዮጵያ የወደብ ስምምነት የመፈራረሟን አጋጣሚ ተጠቅማበታለች ።   የኢትዮጵያ ጎረቤት ሶማሊያ ድረስም ጓዟን ጭና መጥታለች ። ሣሚራ ጋይድ ።

«በመጀመሪያ  ሶማሊያ ግብጽን ጋብዛ ነው የሚል አንድ መከራከሪያ አለ ሶማሊያ ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ወዳጆቿ የሆኑ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ ስትጠይቅ ነበር ጉዳዩን በመቃወም ከኢትዮጵያ በተቃራኒው እንዲቆሙ ስትወተውትቅ ነበር በቅርቡ በሶማሊያ እና በግብጽ መካከል የተፈረመው የመከላከያ ስምምነት ግብጽ በስልጠናም ሆነ በጋራ የደሕንነት መደጋገፍን በመሳሰሉ  ጉዳዮች ለመርዳት ወደ ሶማሊያ እንድትመጣ የሚጠይቅ ነው ከዚያ ጥያቄ ባሻገርም ሶማሊያ የግብጽ ወታደሮች ሀገሯ ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንዲተኩ ትሻለች »

ከሶማሊያ ወዳጆች መካከል ቱርክ እና ግብጽ ተጠቃሾቹ ናቸው

የሶማሊያ መንግሥት ርዳታቸውን ከተማጸናቸው እና ወዳጆቼ ከሚላቸው ሃገራት መካከል  ቱርክ እና ግብጽ ተጠቃሾቹ ናቸው ። ቱርክ እና ግብጽ የቆየ ፖለቲካዊ ቁርሿቸውን ወደ ጎን ብለው ግንባር ከገጠሙ ሰነባብተዋል ። የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን እና የግብጽ መሪ አብዱልፈታህ አል ሲሲ ሰሞኑን አንካራ ውስጥ ፊት ለፊት በተወያዩበት ወቅት፦ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነትን እና ትብብርን ለማጠናከር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ። በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ካይሮ ውስጥ አብደል ፈታህ አል ሲሲን የጎበኙት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ግብጽ እና ቱርክን በተመለከተ «በሁሉም አካባቢዎች ያለንን ትብብር እናጠናክራለን» ሲሉ ተደምጠዋል ።

ከግራ ወደ ቀኝ የግብፅ ፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አል ሲሲና የቱርኩ አቻቸዉ ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻንምስል Turkish Presidency/Mustafa Kamaci/Anadolu/picture alliance

አንካራ እና ካይሮ ግንኙነታቸውን ያቋረጡት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 የወቅቱ የግብጽ መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አል ሲሲ የቱርክ አጋር እና የሙስሊም ወንድማማችነት ንቅናቄ አባሉን የወቅቱን ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲን ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ ነበር ። ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋኻን በ2014 ከዓረብ ሃገራት በሕዝብ ብዛት ብልጫ ያላት ሀገር ፕሬዝዳንት እንደነበሩት እንደ አል ሲሲ ካሉ «ማናቸውም» ሰው ጋ በፍጹም እንደማይነጋገሩ ምለው ተገዝተው ነበር ። የሶማሊያ እና የቱርክ ስምምነት አንድምታዎች

ረቡዕ ዕለት ግን የግብጽ እና የቱርክ መሪዎች 17 የትብብር ስምምነቶችን መፈራረማቸውን የግብጽ ፕሬዝዳንት ዐሳውቀዋል ። እንደ ፕሬዚደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ከሆነ፦  በሶማሊያ ጉዳይም ከቱርኩ አቻቸው ጋ ተወያይተዋል ። የሶማሊያን አንድነት እና የግዛት ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅም ሁለቱ መሪዎች መስማማታቸውን የግብጹ መሪ ይፋ አድርገዋል ።  ከቱርክ በኩል የተሰማ ነገር የለም ። ቱርክ እና ግብጽ በቅርቡ ከሶማሊያ ጋ ወታደራዊ የትብብር ስምምነቶችን መፈራረማቸው የሚታወስ ነው ። ሁኔታዎች ወዴት እንደሚያመሩ አብረን እንከታተላለን ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW