1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብጽ የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትን ተቃወመች

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ ነሐሴ 27 2016

ግብጽ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አምስተኛ ዙር የውኃ ሙሌትን ተቀባይነት የለውም በማለት ውድቅ ማድረጓና ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አቤት ማለቷ ተሰምቷል። የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ባድር አብደላቲ ለምክር ቤቱ ጻፉት በተባለው ደብዳቤ «ግብጽ በዓለማቀፍ ሕግ መሠረት ሁሉንም ሕጋዊ ርምጃዎች ትወስዳለች» ይላል።

የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት
የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ምስል Angela Weiss/AFP/Getty Images

ግብጽ የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትን ተቃወመች

This browser does not support the audio element.

ግብጽ የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትን ተቃወመች


ግብጽ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አምስተኛ ዙር የውኃ ሙሌትን ተቀባይነት የለውም በማለት ውድቅ ማድረጓና ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አቤት ማለቷ ተሰምቷል። የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ባድር አብደላቲ ለምክር ቤቱ ጻፉት በተባለው ደብዳቤ "ግብጽ በዓለማቀፍ ሕግ መሠረት ሁሉንም ሕጋዊ ርምጃዎች ትወስዳለች" ይላል። ኢትዮጵያን ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር መፍትሔ ላይ ለመድረስ ፍቃደኛ ሆና አታውቅም በሚል ግብጽ የከሰሰች ሲሆን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው የግድቡን ድርድር ጉዳይ በሰላም ለምፍታት ከመልካም ፈቃድ ጋር ዝግጁዎች ነን፤ ይህም ይቻላል ሲሉ በቅርቡ ተናግረዋል። ግብጽ ለጸጥታው ምክር ቤት ስላቀረበችው ደብዳቤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከግድቡ ተደራዳሪ ቡድን አባላት አስተያየት ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። 


ግብጽ ያቀረበችው ክስ እና የኢትዮጵያ እውነት


ግብፅ የዓባይን ​​ውኃ ወሳኝ ድርሻ አደጋ ላይ ይጥላል ያለችውን የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በመቃወም ትናንት እሑድ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ማስገባቷ ተነግሯል። የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፃፉት በተባለው ደብዳቤ የኢትዮጵያ እርምጃ አካባቢያዊ መረጋጋትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ይላል ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የግድቡን ግንባታ አስመልክተው ባለፈው ሳምንት በሰጡት ማብራሪያ የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት "ሱዳንና ግብጽ ሊደግፉት የሚገባ" ነው ብለው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግድቡ 2800 ሜትር ኪዩብ ውኃ በሰከንድ መፍሰስ መጀመሩ ለተፋሰሱ ሀገራት በጎ ዜና መሆኑንም በወቅቱ ገልፀው ነበር። "የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተርባይን ከሚያገኙት ውኃ በተጨማሪ ይህን ያህል [2800 ሜትር ኪዩብ ውኃ በሰከንድ]

ውኃ የምንለቅላቸው የእኛ መሻት፣ የእኛ ፍላጎት ውኃ ታች በማሳነስ እኛ ልዩ ተጠቃሚ መሆን አይደለም። ይህ ውኃ የጋራ ኃብታችን ነው። የእኛ ኃላፊነት እንደ ሀገር እና ሕዝብ ተሚገባንን ያህል ተጠቅምን የሚገባቸውን ያህል ለወንድሞቻችን ማካፈል ነው"። ግብጽ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በፃፈችው ደብዳቤ ግን የኢትዮጵያ አካሄድ በጎረቤቷቿ ላይ የምትከተለው ላለችው ጠብ አጫሪ አካሄድ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል። ከዚህም አልፎ በግድቡ ድርድር ዙሪያ ኢትዮጵያን መፍትሔ ላይ ለመድረስ ፖለቲካዊ ፍቃድ የሌላት በሚል ይከሳል። በጉዳዩ ላይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከግድቡ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ምላሽ ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "የድርድሩን ጉዳይ በሰላም ለምፍታት ከበጎ እምነት ጋር ዝግጁዎች ነን፤ ይህም ይቻላል" ብለው ነበር። አክለውም ግድቡ ሥራ በመጀመሩ ደስተኛ የመሆናችንን ያህል የቀሩ ያልፈታናቸውን የድርድሩን ጉዳዮችም ለመፍታት እንፈልጋለን" ሲሉ የመንግሥትን ፍላጎት ግልጽ አድርገው ነበር። 

ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images


የውኃ ምህንድስና ባለሙያ አስተያየት


የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለፀጥታው ምክር በፃፉት ደብዳቤ ሀገራቸው "ኅልውናዋን ለመከላከል እና የሕዝቦቿን ጥቅም ለማስከበር በመንግሥታቱ ድርጅት ሕግ መሠረት ሁሉንም እርምጃዎች ለመውሰድ ዝግጁ ናት" ብለዋል። ከዚህ አስቀድመው ለዶቼ ቬለ ማብራሪያ የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምርህ እና የድርድሩ የግድቡ የቴክኒክ ቡድን አባል ዶክተር በለጠ ብርሃኑን ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የአቋም ለውጥ ሊኖር እንደማይችል አመልክተዋል።
ግብጽ ከጅምሩ የሕዳሴ ግድብ እንዳይገነባ፣ ግድቡ ከሚይዘው የውኃ መጠን እና ከሙሌቱ ጋር በተያያዘ አስገዳጅ ስምምነት እንዲኖር ያልተቋረጠ አቋም በማራመዷ በግድቡ ላይ ይደረግ የነበረው ድርድር ውል አልባ ሆኖ ያለ ትምምን ተቋርጧል። የውኃ መሃንዲሱ እንደሚሉት ይህ የግብጽ አቋም ኢትዮጵያ ወደፊትበምታለማቸው መሰል ግዙፍ የልማት መሠረተ ልማቶች ላይ የሚንፀባረቅ ነው። ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የወደብ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ የመግባቢያ ስምምነት ከመፈራረማቸው ማግስት ጀምሮ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት በእጅጉ ሻክሯል። ይህንን ተከትሎ ግብፅ የጦር መሣሪያ የጫኑ ሁለት የጦር አውሮፕላኖቿን ሰሞኑን ወደ ሶማሊያ ሞቅዲሾ መላኳ በአካባቢው ተጨማሪ ውጥረት እንዲኖር አድርጓል።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW