1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግንቦት 15 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 15 2014

ፋሲል ከነማ የቅዱስ ጊዮርጊስን ያለመሸነፍ ጉዞ ትናንት መግታት ችሏል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አስደማሚ እና ልብ አንጠልጣይ በሆነ መልኩ ትናንት ሲጠናቀቅ ማንቸስተር ሲቲ ሲመኘው የነበረውን ዋንጫ በእጁ አስገብቷል። ሊቨርፑል በመጨረሻውና በወሳኙ ፌሽታ በሻምፒዮንስ ሊግ መፈንደቅ ይችል እንደሁ አምስት ቀናት መጠበቅ ይኖርበታል።

Fußball | Premier League | Manchester City - Aston Villa
ምስል Stu Forster/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ፋሲል ከነማ የቅዱስ ጊዮርጊስን ያለመሸነፍ ጉዞ ትናንት መግታት ችሏል።  የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አስደማሚ እና ልብ አንጠልጣይ በሆነ መልኩ ትናንት ሲጠናቀቅ ማንቸስተር ሲቲ ሲመኘው የነበረውን ዋንጫ በእጁ አስገብቷል። ሊቨርፑል በድንቅ ሁኔታ ተጋጣሚውን ቢያሸንፍም የስታዲየም ሜዳውን ጥሶ እስከ መግባት ያደረሰ ፌሽታ እና ፍንደቃው ግን ለማንቸስተር ሲቲ ነበር። ሊቨርፑል በመጨረሻውና በወሳኙ ፌሽታ በሻምፒዮንስ ሊግ መፈንደቅ ይችል እንደሁ አምስት ቀናት መጠበቅ ይኖርበታል። የእነ ካሪም ቤንዜማ እና ቪንሺየስ ጁኒየር ሪያል ማድሪድ በፍጻሜው የፊታችን ቅዳሜ ይጠብቀዋል። በጣሊያን ሴ ሪ ኣም ኢንተር ሚላን ተጋጣሚውን አሸንፎም አንገት ሲደፋ ኤስ ሚላን ደጋፊዎችን አስፈንድቋል። ሪያል ማድሪድ እና ሊቨርፑል ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ የፊታችን ቅዳሜ ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ተቀጣጥረዋል። በዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር ላይ ድል በመቀዳጀት ብቸኛው ጥቁር አፍሪቃዊ የኤርትራው ብስክሌተኛ ድሉን በሚያከብርበት ወቅት የሻምፓኝ ቡሽ ተፈናጥሮ ዐይኑን በመምታቱ ከውድድር ወጥቷል። በርካቶችን አስቆጭቷል።

አትሌቲክስ

ቤልጅየም ሎከረን ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የ800 ሜትር የፍላንደርስ ካፕ አቭሎ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ኤርሚያስ ግርማ በ1ኛነት ለድል በቅቷል። ኤርሚያስ ለድል የበቃው 1:44.36 በመሮጥ ነው። ኤርሚያስ ከሦስት ወራት በፊት ጀርመን ዶርትሙንድ ከተማ ውስጥ በተከናወነው የፒኤስዲ ባንክ የቤት ውስጥ የ1500 ሜትር የሩጫ ፉክክር 1ኛ መውጣቱ የሚታወስ ነው።  ኢትዮጵያዊው አትሌት ኤርሚያስ ግርማ በዚህ ውጤቱ የዓመቱ 2ኛ ፈጣን ሰዓቱ ተብሎ ተመዝግኖለታል። የገባበት ሰአትም ከአትሌት መሐመድ አማን ቀጥሎም ምርጡ ኢትዮጵያዊ የርቀቱ አትሌት አድርጎታል።

ምስል picture-alliance/imageBROKER/M. Dietrich

ስዊድን ውስጥ ቅዳሜ እለት በተከናወነው የ21 ኪሎ ሜትር የግማሽ ማራቶን የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ተከታትለው በመግባት አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል። በስዊድን የጎይተቦርግስፋርፌት የግማሽ ማራቶን የሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ በ4ኛ ደረጃ መሀከላቸው ያስገቡት ኬንያዊቷ አትሌት ሉድዊና ቼፕንጌቲችን ብቻ ነው። ከእዛ ውጪ ትግስት አሰፋ 1:08:20 በመሮጥ በአንደኛነት አጠናቃለች።  ጥሩዬ መስፍን 1:08:25 በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። 1:08:26 የሮጠችው አሚነት አህመድ ደግሞ የሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።  ጌጤ አለማዬሁ 1:09:24,6.በመሮጥ ከኬንያዊቷ ሯጭ ተከትላ የአምስተኛ ደረጃን ይዛለች።  በወንዶች ተመሳሳይ ርቀት ፉክክር ኬንያውያን አትሌቶች ከመሀላቸው በ4ኛ ደረጃ እስራኤላዊው ሯጭ ማሩ ተፈሪን ከማስገባታቸው በስተቀር ከ1ኛ እስከ 9ኛ ድረስ ያለውን ደረጃ ተቆጣጠረው በውድድሩ ነግሠውበታል። ኢትዮጵያዊው ሯጭ ዓለምነህ ይርሳው የስዊድኑ ሳሙኤል ሩሶም እና የጀርመኑ ዮሐነስ ሞትሽማንን ከፊት እና ከኋላ አድርጎ በ11ኛነት አጠናቋል።

ብሪታንያ ቢርሚንግሐም ውስጥ በተከናወነው የ2022 ዋንዳ ዳይመንድ ሊግ የሩጫ ፉክክርም ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች   በ5000 ሜ ከ1ኛ - 3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። በቅዳሜው ውድድር 1ኛ የወጣችው ዳዊት ስዮም በአሸናፊነት የገባችበት ሰአት 14:47:55 ነው። አትሌት ሃዊ ፈይሳ 14:48.94 በመሮጥ 2ኛ ስትወጣ፤ 3ኛ የወጣችው አትሌት ፋንቱ ወርቁ ደግሞ 14:49.64 ሮጣ አጠናቃለች።

እግር ኳስ

ትናንት ባሕርዳር ከተማ ውስጥ እጅግ በርካታ ታዳሚያን በተገኙበት በተከናወነው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ፋሲል ከነማ መሪው የቅዱስ ጊዮርጊስን ያለመሸነፍ ጉዞ መግታት ተሳክቶለታል።  በትናንቱ ግጥሚያ ኦኪኪ ኦፎላቢ በ3ኛው ደቂቃ ላይ በሦስት ተከላካዮች መሀል ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ፋሲል ከነማ ለድል በቅቷል። ሁለተኛ የግብ እድል ያጋጠመው ኦኪኪ ኦፎላቢ በድንቅ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ኳሷን በመግፋት ቢጠጋ እና ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ቢወድቅም ፍጹም ቅጣት ምት አልተሰጠም። ቻርልስ ሉኳጎ የኦኪኪን እግር ሁለት ጊዜ አጨናግፎ የጣለ ይመስላል። ኦኪኪ ትናንት ያስቆጠራት ግብ በውድድር ዓመቱ 8ኛ ሆና ተመዝግባለታለች። ጢም ብሎ በሞላው ስታዲየሙ ውስጥ የሕዝቡ የቡድን ድጋፍ ተስተጋብቷል፤ የተቃውሞ መፈክሮችም ታይተዋል። በትናንቱ ድል አጼዎቹ አምስት ጨዋታ እየቀረ ነጥባቸውን 49 አድርሰው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ 5 ማጥበብ ተሳክቶላቸዋል።  

ምስል Alex Livesey/Getty Images

ፕሬሚየር ሊግ

የዘንድሮ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ፍጻሜው እጅግ በሚያጓጓ እና ልብ አንጠልጣይ በሆነ መልኩ በማንቸስተር ሲቲ የበላይነት ተጠናቋል። በትናንቱ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ በአስቶን ቪላ 2 ለ0 ሲመራ በ1 ነጥብ ልዩነት ብቻ ተበልጦ የዘንድሮ ውድድሩን ያጠናቀቀው ሊቨርፑል የማታ ማታ ዋንጫውን የማንሳት እድል በእጁ የገባ መስሎት ነበር።  ሊቨርፑል በ3ኛው ደቂቃ ላይ በፔድሮ ኔቶ በተቆጠረበት ድንገተኛ ግብ በዎልቨርሀምፕተን ሲመራ ቢቆይም፤ የአስቶን ቪላ ማንቸስተር ሲቲን 2 ለ0 መምራት ግን ለዋንጫው ይበልጥ እንዲጓጓ አድርጎት ነበር። ለዚህም ይመስላል የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ለሻምፒዮንስ ሊግ ረፍት ያደርጉ የነበሩትን ሳይቀር አራት ምርጥ አጥቂዎቻቸውን ባልተለመደ መልኩም ወደ ሜዳ ያስገቡት። በእርግጥም ተሳክቶላቸው ዎልቨርሀምፕተንን 3 ለ1 አሸንፈዋል። በዚያኛው ጨዋታ ግን ማንቸስተር ሲቲ ጥርሱን ነክሶ እስከ መጨረሻው በመጫወቱ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል።

ምስል Oli Scarff/AFP/Getty Images

የሊቨርፑል የቀድሞ ተጨዋቾች የአስቶን ቪላው አሰልጣኝ ስቴፋን ዤራርድ እና አጥቂው ፊሊፕ ኩቲንሆ የቀድሞ ቡድናቸው ዋንጫ እንዲያነሳ የቻሉትን አድርገው ነበር። የአስቶን ቪላው ማቲ ካሽ በ37ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ግብ ካስቆጠረ በኋላ፤ ፊሊፕ ኩቲንሆ ሁለተኛውን ግብ ከእረፍት መልስ በ69ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል። የማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾች፤ አሰልጣኝ እና ደጋፊዎች ከገቡበት ጭንቀት በስተመጨረሻ ለመውጣት ግን የፈጀባቸው አምስት ደቂቃ ብቻ ነው። በ76ኛው እና 81ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያዋን እና የማሸነፊያ ማሳረጊያ ግቦች ኢካይ ጉንዶዋን ከመረብ ሲያሳርፍ ሁሉም ነገር ተቋጭቷል። ማንቸስተር ሲቲም በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ሊቨርፑልን በልጦ የዘንድሮ የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን እንደተመኘው ከእጁ አስገብቷል። ለማንቸስተር ሲቲ ሁለተኛውን ግብ ያስቆጠረው ሮድሪጎ በ78ኛው ደቂቃ ላይ ነው። በትናንቱ ድል የማንቸስተር ሲቲ ኢስትሀድ ስታዲየም ሜዳ በደስታ በፈነጠዙ ደጋፊዎች ተሞልቶ ታይቷል።

ምስል Alex Livesey/Getty Images

አራቱን ዋንጫዎች ይወስዳል ተብሎ ተገምቶ የነበረው ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫን ቢያጣም ለመጨረሻው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ሊፋለም አምስት ቀናት ብቻ ይቀሩታል። ከዎልቨርሐምፕተን ጋር በነበረው የፕሬሚየር ሊጉ የመጨረሻ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ የሚሸነፍ እና ዋንጫውን የሚያነሳ መስሎት ሊቨርፑል የተጨዋቾቹን ብዙ ኃይል አስጨርሷል። ምናልባት ያ በሻምፒዮንስ ሊጉ የፍጻሜ ግጥሚያ ላይ የራሱ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችል ይሆናል። የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣን ፔፕ ጓርዲዮላ በአምስት የጨዋታ ዓመታት አሁን አራተኛ ዋንጫቸውን ማንሳት ችለዋል። በአንጻሩ የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ በአንድ የጨዋታ ዓመት ሦስተኛ ዋንጫ ለማንሳት ተዘጋጅተዋል። እስካሁን የካራባዎ እና ኤፍ ኤ ካፕን አሸንፈዋል። ቀሪው የሻምፒዮንስ ሊግ ነው። ቅዳሜ ሊቨርፑል ሪያል ማድሪድን ድል ካደረገ አሰልጣኙ ሦስተኛ ዋንጫቸውን በእጃቸው አስገቡ ማለት ነው። የስፔን ላሊጋ ዋንጫን በሰፊ የነጥብ ልዩነት ዘንድሮ ያነሳው ሪያል ማድሪድ ግን ለሊቨርፑል ስጋት መሆኑ የማይቀር ነው።

ላሊጋ

የስፔን ላሊጋ በአንጻሩ እንደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና ጣሊያን ሴሪኣ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ብዙም ልብ አንጠልጣይ ክስተቶች ዐልታዩበትም። ሆኖም የፓሪ ሳንጃርሞ ወሳኝ አጥቂ ኬሊያን እምባፔ ወደ ሪያል ማድሪድ ይዛወራል የሚባለውን ዜና ችላ ብሎ ቆይታውን በፓሪስ እንደሚያራዝም መናገሩ በሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ዘንድ ቀዝቃዛ ውኃ ቸልሷል። ኬሊያን እምባፔ ከወራት በፊት ወደ ሪያል ማድሪድ ሊዛወር የቃላት ስምምነት አድርጎ ነበር ያሉ የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች እና የስፖርት ተንታኞች ፈረንሳዊው አጥቂ ሐሳቡን በስተመጨረሻ ቀይሯል ሲሉ «ከሐዲ» ነው ብለውታል። «ሪያል ማድሪድ ውስጥ ለመጫወት ደረጃህ ከፍ ሊል ይገባል» ሲል ዴይሊ ማርካ የተባለው የስፖርት ጋዜጣ ርእሱን አጉልቶ ጽፏል። «የጎደለበት እሱ ነው» ሲል ኬሊያን እምባፔን የተቸው ደግሞ ኤኤስ የተሰኘው ጋዜጣ ነው። እንዲህ ያለው ዘገባ እና አስተያየት ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊግ በፍጻሜው ከሊቨርፑል ጋር ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ውስጥ ቅዳሜ በሚያደርገው ግጥሚያ ላይ ጥላውን ሊያጠላ ይችል ይሆናል ተብሏል።

ሴሪኣ

ምስል Elisabetta Baracchi/ZUMA Wire/IMAGO

ዘንድሮ እጅግ አጓጊ በነበረው የጣሊያን ሴሪኣ የአሰልጣኝ ስቴፋኖ ፒዮሊ ኤሲ ሚላን ዋንጫውን አንስቷል። ኤስ ሚላን ያለፈው ዓመት የዋንጫ ባለድሉ ኢንተር ሚላንን በልጦ ዋንጫውን ያነሳው በ2 ነጥብ ልዩነት ብቻ ነው። ኤስ ሚላን ትናንት ሳሱዎሎን 3 ለ0 ሲያሸንፍ ነጥቡን 86 አድርሷል። ኢንተር ሚላን በአንጻሩ ሳምፕዶሪያን በተመሳሳይ 3 ለ0 ቢያሸንፍም በ84 ነጥብ በመወሰኑ ግን ዋንጫ ሳያገኝ ቀርቷል። የትናንቱ የኤሲ ሚላን ድል በተለይአሰልጣኝ ስቴፋኖ ፒዮሊን እጅግ ያስቦረቀ ነው። አሰልጣኙ ከሁለት ዓመት በፊት ለጥቂት ሊሰናበቱ እና በራልፍ ራኚክ ሊተኩ ጫፍ ተደርሶ ነበር። ጀርመናዊው አሰልጣኝ በስተመጨረሻ ሐሳባቸውን ባይቀይሩ ኖሮ የትናንቱ ድል ሌላ መልክ ሊኖረው አሰልጣኝ ስቴፋኖ ፒዮሊም ተባርረው ሌላ ቦታ ይገኙ ነበር። አሰልጣኙ በቡድኑ መቆየታቸው ግን ኤስ ሚላንን ከ11 ዓመት ቆይታ በኋላ የሴሪኣውን ዋንጫ እንዲያነሳ አስችለውታል። ትናንት ሜዳው ውስጥ ተምመው የገቡት የኤስ ሚላን ደጋፊዎች ከአሰልጣኝ ስቴፋኖ ፒዮሊ ጋር ፎቶ ለመነሳት በግፊያ እና በመተራመስ በደስታ ተውጠው ሲያስጨንቁ ታይተዋል። በእርግጥም በ19 የአሰልጣኝነት ዘመናቸው የመጀመሪያቸው የሆነውን እንዲህ ያለውን ዋንጫ ላነሱት አሰልጣኝ ሙገሳው ሲያንሳቸው ነው።  

ቡንደስሊጋ

ኤርቢ ላይፕትሲሽ ፍራይቡርግን በፍጹም ቅጣት ምት 4 ለ2 አሸንፎ የፖካል ዋንጫ ወስዷል። የሁለቱ ጨዋታ የተጠናቀቀው አንድ እኩል ነበር። የላይፕትሲሽ ደጋፊዎች ቤርሊን በሚገኘው ኦሎምፒክ ስታዲየም ደስታቸውን ገልጠዋል። ለፍራይቡርግ 20ኛው ደቂቃ ላይ ግቡን ያስቆጠረው ኤገሽታይን ነው። ለላይፕትሲሽ ደግሞ ከሽንፈት ያዳነውን ግብ ያስቆጠረው እንኩንኩ በ76ኛው ደቂቃ ላይ ነው።

ምስል Matthias Koch/IMAGO

ብስክሌት

ባለፈው ሳምንት የኤርትራው ብስክሌተኛ ቢንያም ግርማይ በብስክሌት ግልቢያ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ባለድል ከሆነ በኋላ ድሉን ለማክበር የከፈተው ሻምፓኝ ቡሽ ተፈናጥሮ ዐይኑን በመምታቱ ከቀጣይ ውድድሩ መውጣቱ በርካቶችን አስቆጭቷል። ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በጂሮ ዲ ኢታሊያ የብስክሌት ግልቢያ የዙር አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪቃዊ መሆን ችሏል። ከድሉ በኋላ የሻምፓኝ ጠርሙሱን መሬት ላይ አስቀምጦ ሲከፍተው ቡሹ ተፈናጥሮ የግራ ዐይኑን መትቶታል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል። ወዲያውኑ ወደ ሐኪም ቤት የተወሰደ ሲሆን፤ ሐኪሞች ጉዳቱ እንዳይባባስ ረፍት ያስፈልገዋል በማለታቸው ለተጨማሪ ድል በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ አጭሮ የነበረው ብንያም ከውድድሩ ለመውጣት ተገዷል።   

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW