1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ስለ ግንቦት 20 የተሰጡ አስተያየቶች

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ ግንቦት 20 2017

ላለፉት 27 ዓመታት በልዩ ልዩ አገራዊ ኹነቶች ደምቆ ይከበር የነበረው ግንቦት 20 ባለፈው ዓመት በፀደቀው «የሕዝብ በዓላት እና የበዓላት አከባበር አዋጅ» ከብሔራዊ በዓላት ዝርዝር ውስጥ ባለመካተቱ ዛሬ መደበኛ የሥራ ቀን ሆኖ አልፏል ። በትግራይ ክልል ግን ይህ ዕለት በአደባባይ ተከብሮ ውሏል ። የባለሞያዎች አስተያየት ።

አዲስ አበባ ከተማ፤ ግንቦት 20
የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ድባብ በግንቦት 20ምስል፦ Solomon Muchie/DW

ግንቦት 20 በሕወሓት ብቻ ትግራይ ክልል መከበሩ

This browser does not support the audio element.

ዛሬ ግንቦት 20 ቀን፣ 2017 ዓ. ም የደርግ መንግሥት በኃይል ከሥልጣን ተወግዶ አሸናፊው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ኃይል የተተካበት 34ኛው ዓመት ። ላለፉት 27 ዓመታት በልዩ ልዩ አገራዊ ኹነቶች ደምቆ ይከበር የነበረው ግንቦት 20 ባለፈው ዓመት በፀደቀው «የሕዝብ በዓላት እና የበዓላት አከባበር አዋጅ» ከብሔራዊ በዓላት ዝርዝር ውስጥ ባለመካተቱ ዛሬ መደበኛ የሥራ ቀን ሆኖ አልፏል ። በትግራይ ክልል ግን ይህ ዕለት በአደባባይ ተከብሮ ውሏል ። ይህን ዕለት ተከትሎ የተመሠረተው የኢሕአዴግ መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያጎናፀፈ፣ ኢትዮጵያን በልማት ያጠናከረ በሚል የመሞገሱን ያህል፣ ሀገሪቱን የባሕር በር አልባ በማድረግና አንድነትን በማላላት በብርቱ ይተቻል ። 

ግንቦት 20  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  የሚመሩት መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ  ጎልቶ በብሔራዊ ደረጃ መከበሩ ቀስ በቀስ ቀንሷል። ባለፈው ዓመት "የሕዝብ በዓላት እና የበዓላት አከባበር አዋጅ" መጽደቁን ተከትሎ ደግሞ በዚህ ዓመት ዕለቱ መደበኛ የሥራ ቀን ሆኖ ውሏል። የሀገሪቱ ስመ መንግሥት ከዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ወደ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የተቀየረበት ይህ ዕለት መልካም ውጤቶች እንደነበሩት አስተያየታቸውን ከጠየቅናቸው መካከል ኮሎኔል ፍስሃ ገብረመድህን ገልፀዋል። "ከፍተኛ ለውጦች አሉ። የኢትዮጵያ ብሔር እና ብሔረሰቦች በቋንቋቸው እንዲናገሩ፣ እንዲጽፉ፣ በቋንቋቸው እንዲዳኙ ዕድል ፈጥሯል።"

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና ፌዴራሊዝም መምህሩ ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ በዚህ ይስማማሉ። "የመንግሥት ፣ የመዋቅር፣ የአስተሳሰብ ለውጥ" እንደነበር በመግለጽ። "በዋነኛነት ብሔር ተኮር የሆነ የፖለቲካ አደረጃጀት ይዘው ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ [ኢሕአዴግ] ሀገሪቱ ቀደም ሲል ስትከተለው የነበረውን አሃዳዊ የመንግሥት ሥርዓት የቀየረ ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓት በሽግግር ወቅት እንዲጀመር የተደረገበት ወቅት ነው"

ኮሎኔል ፍስሃ ገብረመድህን እንደሚሉት ኢትዮጵያ የራሷን የውስጥ ሰላም አስከብራ የሌላ ሀገር ሰላምም ማስከበር እንድትችል ያደረገ የሥርዓት ለውጥ የታየበት ዕለት ነበር። "የራሳችን ሰላም አስፍነን የሌላ ሀገርም ሰላም ያሰፈንን ሀገር እንድንሆን ያደረገ ነው ግንቦት ሃያ።" 

ግንቦት 20 ባለፈው ዓመት በፀደቀው «የሕዝብ በዓላት እና የበዓላት አከባበር አዋጅ» ከብሔራዊ በዓላት ዝርዝር ውስጥ ባለመካተቱ ዛሬ መደበኛ የሥራ ቀን ሆኖ አልፏል ። ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ፕሬዝዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ ግንቦት ሃያን ተከትሎ የመጣው መንግሥት እና ሥርዕልት ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ ያደረገ፣ የሕዝብ ትስስርን ያሻከረ በሚል ይገልፁታል። "ኢትዮጵያ ከዚያ ሥርዓት [ከደርግ] በኋላ የባሕር በር ያጣችበት ዘምን ነው። ይህች ሀገር አለኝ የምትለውን ነገር  የባሕር በር ያጣችበት ነው።"

አስተያየት ሰጪዎቹ ግንቦት 20ን ተከትሎ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መታየት፣ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ፣ በቀጣናዊ ሰላም ማስከበር ተልእኮ በጎ ጅምር እንዲታይ በር ቢከፈትም እንደ ኮሎኔል ፍስሃ "ልማታዊ ግን ፀረ ዴሞክራሲያዊ ነበር" ሲሉ አሁን ሀገሪቱ ለገባችበት ውስብስብ የፖለቲካ፣ የፀጥታ፣ የሰላምና ደህንነት ችግር ተጠያቂ አድርገውታል።

ዩናይትድ ስቴትስየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሀገራቸው "ንግድና ኢንቨስትመንትን ለኢኮኖሚ ዕድገት ለማስተዋወቅ፣ ሰላምን በውይይት ለማራመድ" በጋራ ጥረት ለማድረግ እንደምትሻ በመግለጽ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት እንኳን ለግንቦት ሃያ አደረሳችሁ ብለዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW