1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ግእዝን በሥርዓተ ትምህርት የማካተት ዝግጅት

ሐሙስ፣ ሰኔ 10 2013

ወጣቱ ትውልድ ለአገሩ ቋንቋ ባይተዋር መሆኑና መንግስትም ለቋንቋው ትኩረት ስለነፈገውና ቋንቋው ባለቤት ስሌለው ሊያድግ እንዳልቻለ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ቋንቋ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ጥበቡ አንተንህ ይናገራሉ።ሌለኛው እንቅፋት ደግሞ ግዕዝ ለቤተክህነት ብቻ የተሰጠ ነው የሚለው የተሳሳተ ሀሳብ መሆኑም ተነግሯል።

Äthiopien | Bildungsbüro in der Amhara Region
ምስል፦ Alemenew Mekonnen/DW

ለኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ እድገት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው

This browser does not support the audio element.

የግዕዝ ቋንቋን በስርዓተ ትምህርት አካትቶ ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡ በቋንቋው በርካታ እውቀቶች የተካተቱባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ መጽሀፍት ቢኖሩም በአግባቡ ያልተሰነዱ እንደሆኑ ምሁራን አመልክተዋል፣ በአገሩ ያልተከበረው የግዕዝ ቋንቋ በአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ማዕከል መሆኑንም በባሕር ዳር ቋንቋውን በስርዓተ ትምህርት ለማካተት በተጠራ ውይይት ልይ ተገልጿል። የግዕዝ ቋንቋ ለኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ እድገት የነበረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ቢሆንም አሁን አሁን ግን በቤተ ክህነት አካባቢ ከሚሰጠው አገልግሎት ውጪ በሌሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች በኩል አስተዋፅኦው ከነጪራሹ እንደሌለ ነው ምሁራንና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የሚናገሩት።ወጣቱ ትውልድ ለአገሩ ቋንቋ ባይተዋር መሆኑና መንግስትም ለቋንቋው ትኩረት ስለነፈገውና ቋንቋው ባለቤት ስሌለው ሊያድግ እንዳልቻለ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ቋንቋ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ጥበቡ አንተንህ ይናገራሉ።ለቋንቋው እድገት ሌለኛው እንቅፋት ደግሞ ግዕዝ ለቤተክህነት ብቻ የተሰጠ ነው የሚለው የተሳሳተ ሀሳብ እንደሆነ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግዕዝ ቋንቋ መምህር አቶ ገብረአብ ቦጋለ ተናግረዋል። በቋንቋው የተፃፉ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ድርሳናት ቢኖሩም ተመዝግቦ የሚገኘው ከ15 ሺህ እንደማይበልጥ ዶ/ር ጥበቡ ተናግረዋል።የግዕዝ መምህሩ አቶ ገብረአብ እንደሚሉት ግዕዝ በአገሩ ደብዛው እየጠፋና በአብያተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ተወስኖ ቢገኝም በአውሮፓ አገራት በተለይ በጀርመን፣ ጣሊያንና ሌሎችም አገሮች በታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠና ነው።ቋንቋው ባህል፣ ፍልስፍና ትምህርት እንደተፃፈበት አመልክተው፣ አንድ የተወሰነ ተቋምን ሲያገለግል አልቆየም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ በሁሉም መስኮች አስተዋፅኦ እንደነበረው የሚገልፁት አቶ ገብረአብ አባ ባሕሪ የሚባሉ መነኩሴ የኦሮሞን ባህል፣ ታሪክ፣ አኗኗርና ትውፊቶችን ጽፈውበታል ሲሉ ለአብነት ጠቅሰዋል፡።ቋንቋውን በትምህርት ስርዐት ማካተቱ ቋንቋውን ከማወቅም በላይ በቋንቋው የተፃፉ እምቅ እውቀቶችንም ለመረዳት ያስችላል ብለዋል ዶ/ር ጥበቡ አስረድተዋል፡።የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ አገር በቀል እውቀቶችን ለመረዳትና ለማወቅ ግዕዝን በስርኣተ ትምህርት ማካተት ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡በቀጣይም የአርብኛ ቋንቋን በስርዐተ ትምህርት ለማካተት በጥናት የተደገፈ ስራ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ 
ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW