ግዙፉን የባቱ የወይን እርሻን ለቱሪዝም
ቅዳሜ፣ ጥር 13 2015
“አሁን ያለንበት ቦታ 400 ሄክታር የመሬት ቆዳ የሚሸፍነው የካስትል ወይነሪ የእርሻ እና ማምረቻ ስፍራ ነው፡፡ አሁን የምትመለከቱት ምርት ላይ ያለው የወይን ተክል ብቻውን 250 ሄክታር ስፋት አለው፡፡ በዋናነት የቀይና ነጭ ወይን ዝርያዎችም በዚህ ግዙፍ እርሻ ይመረታሉ፡፡” ይህን ማብራሪያ የሰጡን፤ ዳዊት ዳኒኤል ይባላሉ፡፡ በፈረንሳይ አገር በግብርናው እና በቱሪዝም ዘርፍ ሰፊ ልምድ አካብተው ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው በመስኩ ተሰማርተው እንደሚንቀሳቀሱም ያወሳሉ፡፡ በትውልድ መንደራቸው በባቱ ከተማ አሁን ላይ ከተሰማሩበት የሆቴል ዘርፍ ስራ በተጨማሪ በአስጎብኚነት እና በግብርናው ዘርፍ ተሳትፎያቸውም ስማቸው ይነሳል፡፡
ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከሚገኘው የወይን እርሻ እና ፋብሪካ በመቀጠል በአፍሪቃ በስፋትና በይዘቱ ትልቁ ነው በሚባለው ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ባቱ ከተማ አጠገብ በሚገኘው የካስትል ወይን እርሻ እና ፋብሪካን የማስጎብኘት ኃላፊነት ወስደውም ይንቀሳቀሳሉ፡፡
በዚህ በግዙፍ የወይን እርሻ ስፍራ የተተከሉ የወይን ተክሎች ከተተከሉ አስር ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ አንድ የወይን ዛፍ ድግሞ በየሶስት ዓመታት ምርት መስጠት የሚችሉ ሲሆን ለተከታታይ 45 ዓመታት ገደማም ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይታመናል ተብሏል፡፡ በዚሁ ስፍራ የተገነባው የወይን ፋብሪካም ቢያንስ 1.6 ሚሊየን ጠርሙዝ ወይን በያመቱ የማምረት አቅም ያለው ነው፡፡ የተለያዩ 11 ጣዕም ያላቸው የወይን ምርቶች በሚመረቱበት በዚህ ውስጥም 800 ያህል ሰዎች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተነግሮናል፡፡
ይህ ግዙፍ የወይን እርሻ እና ፋብሪካ ከምርት አሰጣጥ በተጨማሪ ለቱሪዝም መዳረሻነት እንደሚውልም ተነግሮናል፡፡ ዚያና የተባለች ወጣት ጀርመናዊት ጎብኚን ስፍራውን በጎበኘንበት አጋጣሚ አነጋግረናታል፡፡
“እኔ ወደዚህ ወደ ባቱ የመጣሁት ልዩ ቀለም ያለው የጥምቀት በዓል አከባበርን ለመጎብኘት ነበር፡፡ በጣም ሳቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በጀርመን እንዲህ ያለ ነገር የለንም፡፡ በአድናቆት ነው ያየሁት፡፡ የመጀመሪያየም እንደመሆኑ አስገርሞኝ ነው የተመለከትኩት፡፡ ዛሬ ደግሞ እዚህ የወይን ማምረቻ እና እርሻ ቦታን እየተመለከትኩኝ ነው፡፡ እኔ ከጀርመን በተለይም በወይን ምርት ከምታወቅ አከባቢ እንደመምጣቴ እቤት እንዳለሁ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ በኢትዮጵያ እንዲህ ያለ ነገርም የሚኖር አልመሰለኝም ነበር፡፡ ኢትዮጵያም በወይን ምርት የምትታወቅ አገር አይመስለኝም ነበር፡፡ ይህን ሁሉ በማየቴ ተደንቀያለሁ፤ እየተደሰትኩበትም ነው፡፡”
ይህን ግዙፍ የወይን እርሻን ባቱ ካላት የቱሪስት መዳረሻዎች በተጨማሪ በማስተዋወቅ ለቱሪስት መዳረሻነት ውጤት እያመጡበት መሆኑን የሚገልጹት የቱሪዝም ባለሙያው አቶ ዳዊት ዳኒኤል ግዙፉን የወይን እርሻ ከቱሪዝም ጋር የሚያገናኘው ሲያብራሩ። “ባቱ ከዚህ ቀደም ካሉዋት የቱሪዝም መዳረሻዎች በተጨማሪ ይህን ግዙፍ የወይን እርሻ ራሱን ችሎ የቱሪዝም ግብዓት እንዲሆን በሰራነው ስራ ውጤታማ እየሆንን፤ ሰዎችም በተለያየ መልኩ ወዲህ እየመጡ እየገበኙን ነው” በማለት እርሻው ከአምራች ግብዓትነት በተጨማሪ ለቱሪዝም ስለሚውልበት ሁኔታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ባቱ ከተማ ኢትዮጵያን በስተምስራቅ በሚከፍላት ታላቁ ስምት ሸሎቆ ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች ተጠቃሽ ስትሆን በፍራፍሬ ምርቶችና የቱሪስት መስዕብ በሆነው የደንበል ሃይቅ እና ደሴቶቹ ትታወቃለች፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ