1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግድያ፣ እገታ፣ ቤት መቃጠል እና ዘረፋ - በኦሮሚያ ክልል

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 18 2016

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በኦሮሚያ ክልል አርሲ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ኅዳር ወር ላይ በታጣቂዎች የተገደሉ 61 ሰዎችን ስም፣ ጾታ፣ ምስል፣ የተገደሉበትን ቀንና ቦታ ጭምር በልዩ መግለጫው ይፋ አደረገ።

(ኢሰመጉ)  አርማ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አርማ ምስል Ethiopian Human Rights Council

«ግድያ፣ እገታ፣ ቤት መቃጠል እና ዘረፋ»

This browser does not support the audio element.

ኢሰመጉ በክልሎ ምሥራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች 53 ሰዎች ተገድለው ሁለት ሰዎች ደግሞ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን፣ እንዲሁም የሦስት ቀበሌ ነዋሪዎች አብዛኛው ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ከቃጠሎ የተረፈው ንብረትም መዘረፉን ገልጿል። 

በቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ዘጠኝ አባላት ላይም የጅምላ ግድያ መፈጸሙን ስማቸውን ጭምር ዘርዝሮ አውጥቷል።
«በታጣቂ ቡድኖች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠናቸውን በመጨመር እየቀጠሉ ይገኛሉ» ያለው ኢሰመጉ «በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ቢሆንም ከመንግሥት በኩል ተገቢው በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱና ዘላቂ መፍትም ባለመበጀቱ ምክንያት እየቀጠሉ ይገኛሉ» ብሏል።

የኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ከሚፈጸምባው አካባቢዎች አንዱ መሆኑን የገለፀው የመብት ድርጅቱ ይህ ጥቃት «በዋናነት ማንነትን መሰረት ያደረገ» መሆኑንም አመልክቷል።


ንጹሐን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አለመቆም 

ኢትዮጵያ ውስጥ ንጹሐን ዜጎችን ላይ ያነጣጠሩ «በታጣቂ ቡድኖች የሚፈጸሙ ጥቃቶች» ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠናቸውን በመጨመር እየቀጠሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ተናግሯል። እነዚህ ጥቃቶች «በአንዳንድ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ቢሆንም ከመንግሥት በኩል ተገቢውን  በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱና ዘላቂ መፍትሔ ባለመበጀቱ ምክንያት» እንደቀጠሉ ይገኛሉ ብሏል የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ፡፡ ኦሮሚያ ክልል ይህን መሳይ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑን የገለፀው ይሄው ድርጅት የሚፈፀመው ጥቃቱ «በዋናነት ማንነትን መሠረት ያደረገ» መሆኑን አብራርቷል፡፡

 
ኢሰመጉ በክልሉ ምሥራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ኅዳር ወር በ53 ሰዎች ላይ ግድያ፤ ሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን የተጎጅዎችን ስም፣ ጾታ፣ ምስል፣ የተገደሉበትን ቀን እና ሥፍራ ጭምር አስደግፎ አውጥቷል። በዚሁ በንጹሐን ዜጎች ላይ የጭፍጨፋ ወንጀል በተፈፀመባቸው ሦስት ቀበሌዎች ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎች አብዛኛው ቤቶች መቃጥላቸውን እና ከቃጠሎ የተረፈውም ንብረት ለዝርፊያ መዳረጉን ድርጅቱ አስታውቋል።

ምሥራቅ ወለጋ ኪረሙ ከተማ ምስል Privat

 
የገዳዮች አለመጠየቅ፣ የፍትሕ መጓደል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ( ኢሰመጉ ) በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ዘጠኝ አባላት ላይም የጅምላ ግድያ መፈጸሙን በማመልከትም የሟቾችን ስም በመዘርዘር አሳውቋል። ኢሰመጉ በእነዚህ አካባቢዎች ባለሙያዎችን በማሰማራት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ምርመራ ካከናወነ በኋላ ይህንን ልዩ መግለጫ ማውጣቱን አስታውቋል። የምርመራ ሥራው በተከናወነባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ስጋት፣ ምሥራቅ አርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ መረጃ ያለማጋራት እና የመጓጓዣ ችግር የምርመራ ሥራውን አዳጋች አድርገውበት እንደነበር ኢሰመጉ ገልጿል። 

የኢሰመጉ የዘላቂ መፍትሔ ጥሪ 
የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት በክልሉ በተጋጋሚ በታጣቂ ቡድኖች ማንነትን መሰረት አድርገው የሚፈጸሙትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ፣ የሕዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በቸልተኝነት ሳይወጡ የቀሩ የመንግሥት አካላትም በሕግ እንዲጠይቁ ኢሰመጉ ጥሪ አድርጓል። 

ሰሎሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW