1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭትና ወባ በወለጋ

ሐሙስ፣ ሰኔ 29 2015

በምዕራብ፣ምስራቅ ወለጋ፣ቀሌም እና ሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ከ270ሺህ በላይ ሰዎች ስለመጠቃታቸው የቢሮው ዘገባ ያስረዳል፡፡ በአራቱም የወለጋ ዞኖች 45 በመቶ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንደማይሰጡ ከባለሥልጣናት ማረጋገጡን ዘገባው አክለዋል፡፡

Symbolbild Malaria | Spritze
ምስል Brian Ongoro/AFP

የጤና ተቋማት፣መድሐኒት፣ መንገድም የለም-ነዋሪ

This browser does not support the audio element.

       
የኢትዮጵያ መንግሥትና ራሱን የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ብሎ በሚጠራዉ አማፂ ቡድን መካከል ዉጊያ በሚደረግበት በምዕራብ ኦሮሚያ የወባ በሽታ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ። የዓለም አቀፉ ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA በምሕጻሩ እንዳስታወቀዉ) ከፀጥታ መታወክ በተጨማሪ ወባ በአራቱም የወለጋ ዞኖች  በመሰራጨቱ ርዳታ ለማድረስ ተቸግሯል። ቢሮዉ ባለፈዉ ማክሰኞ ባወጣዉ ዘገባዉ የጤና ተቋማት በመዉደማቸዉ ሕሙማንን መታከም አይችሉም።
የምዕራብ ወለጋ ዞን የጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጫላ በዞኑ የወባ በሽታ ስርጭት መጨመሩን ገልጾ በአሁኑ ጊዜ በዞኑ አብዛኛው የጤና ተቋማት ወደ ስራ መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡
የሰብአዊ ጉዳዩች ማስተባበሪያ ቢሮ  እንዳመለከተው ክረምት መግባቱን ተከትሎ እና ከዚህ ቀደም በጸጥታ ችግር የተጎዱ የጤና ተቋማት  አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸው  ወባ በሽታ ስርጭት እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡ በምዕራብ፣ምስራቅ ወለጋ፣ቀሌም እና ሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ከ270ሺ በላይ ሰዎች  ስለመጠቃታቸው  የቢሮው ዘገባ ያስረዳል፡፡ በአራቱም የወለጋ ዞኖች 45 በመቶ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንደማይሰጡ ከባለስልጣናት ማረጋገጡን ዘገባው አክለዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ፌድሉ አብዱላሂ በወረዳቸው አራት ቀበሌዎች ውስጥ  የወባ በሽታ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡ በቂ የሆነ የጤና ተቋማትና አገልግሎት ባለመኖራቸው በሰው ህይወት ላይም ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ 
" ባምዞ እና ሾራ ማራሙ በሚባሉ ቦታዎች ወባ በብዛት እየተስፋፋ ነው፡፡ የህጻናት ህይወት አልፈዋል፡፡ በብዛት እየተስፋፋ ነው ወቅቱ ክረምት በመሆኑ በቂ አገልግሎት የለም፡፡በቂ ጤና ጣቢያ የለም፡፡ ወደ ቤጊ ሆስፒታል ቢንሄድም በቂ መድሀኒት ስለለ በዚህ መሐል የሰው ህይወት ሊያልፍ ይችላል፡፡ "   
በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ስመ አይጠቀስ ያሉ ነዋሪም በወረዳቸው አጋምሳ በሚባል ከተማ በርካታ የተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ስፋራ የድጋፍ እጥረትን ጨምሮ ወባ በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት ያልሰጡ የጤና ተቋማት እንዳሉ የነገሩን ነዋሪው መንገድም ዝግ በመሆኑ ለተሻለ ህክምና ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ጠቁመዋል፡፡
የምዕራብ ወለጋ ዞን የጤና ጽህፊት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጫላ በዞናቸው የወባ ስርጭት መጨመሩን አረጋግጠዋል፡፡
"በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በዞናችን የወባ ስርጭት እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ በውሀ ማቆር ምክንያት ማናስቡ ወረዳ እና ባቦ ጋምቤል በሚባል ወረዳ በብዛት ወባ ታይቷል፡፡ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም ስርጭቱ ከፍተኛ ነው፡፡  ኬሚካል በመርጭት መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ በዞናችን ከሚገኙት 69 የጤና ተቋማት መካከል  2ቱ ነው በስራ ላይ የሉም ሌሎች ደግሞ ወደ ስራ ተመልሰው በቻሉት አቅም አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡"
በየአካባቢው የወባ በሽታ ስርጭትን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡን ወደ ሆሮ ጉደሩወለጋ  ዞን  እና ምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር ስራ ኃላፊዎች ቢንደውልም ስልካቸውን ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልቻለም፡፡

ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ተፈናቃዮች ምስል Seyoum Getu/DW

ነጋሳ ደሳለኝ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW