1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል የተባሉ ተከሰሱ

ዓርብ፣ ሰኔ 7 2016

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሐሰተኛ የፌስ ቡክ ገፅ በመክፈት የጥላቻ መልዕክቶች ሲያስተላልፉ ደረስኩባቸው ያላቸውን 72 ሰዎች ለህግ ማቅረቡን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ገለጹ፡፡እንደ ሃላፊው ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት 276 ሐሰተኛ የፌስ ቡክ ገጾችን በመክፈት ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች በማስተላለፋቸው ነው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሐሰተኛ የፌስ ቡክ ገጽ በመክፈት የጥላቻ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ደረስኩባቸው ያላቸውን 72 ሰዎች ለህግ ማቅረቡን ገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሐሰተኛ የፌስ ቡክ ገጽ በመክፈት የጥላቻ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ደረስኩባቸው ያላቸውን 72 ሰዎች ለህግ ማቅረቡን ገልጿል።ምስል Central Ethiopia Regional state Communications office

ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል የተባሉ ተከሰሱ

This browser does not support the audio element.


የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሐሰተኛ የፌስ ቡክ ገጽ በመክፈት የጥላቻ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ደረስኩባቸው ያላቸውን 72 ሰዎች ለህግ ማቅረቡን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ  ለዶቼ ቬለ ገለጹ፡፡ የቢሮው ሃላፊ እንዳሉት ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት 276 ሐሰተኛ የፌስ ቡክ ገጾችን በመክፈት ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ሲያስተላልፉ በመገኘታቸው ነው ፡፡
የሰላምና ጸጥታ ቢሮው እርምጃ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት አሥር ወራት በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ተከናውነዋል ባላቸው ተግባራት ላይ በሆሳዕና ከተማ እየመከረ ይገኛል ፡፡ ክልሉ በአዲስ መልክ ከተዋቀረበት ጀምሮ አካባቢውን የግጭት ቀጠና ለማድረግ በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ አውታሮች አፍራሽ ዘመቻዎች መከናወናቸው በምክክር ጉባዔው ላይ በቀረበው ሪፖርት ተጠቅሷል ፡፡
በክልሉ ከ500 በላይ በሚሆኑ የፌስ ቡክ ገጾች ላይ ክትትል ማድረጉን የጠቀሰው የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ “ ከእነኝህም መካከል 276 ያህሉ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ሆነው ተገኝተዋል “  ብሏል፡፡ እነኝህኑ ገጾች ሲያንቀሳቅሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ 72 ሰዎች አሁን ላይ በህግ ተይዘው ክስ እንደተመሠረተባቸው ነው የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ  ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ፡፡
የክስ እርምጃው ሀሳብን ከመግለጽ መብት አንጻር
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወሰደው እርምጃ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ትችቶችን በሚያቀርቡ ዜጎች ላይ ሥጋት አይፈጥርም ወይ ?  ሀሳብን በነጻነት ለመግለጽ ከተደነገጉ ህገ መንግሥታዊ መብቶች ላይስ አሉታዊ ተፅእኖ አያሳድርም ወይ ? ሲል  ዶቼ ቬለ የቢሮ ሃለፊው አቶ ተመስገንን ጠይቋል ፡፡
ተጠያቂዎችን የመለየትና የክስ እርምጃዎች የመውሰዱ ሂደት በሚዲያ ነጻነት ላይ ጫና እንዳይፈጥር ጥንቃቄ መደረጉን የጠቀሱት አቶ ተመስገን “ ለምሳሌ በራሳቸው ሥም በግልፅ የክልሉን አስተዳደር የሚተቹ አሉ ፡፡ መረጃ በመያዝ የሚታዩ ክፍተቶችን በመጥቀስና ሊታረሙ ይገባል የሚሏቸውን ጉዳዮች የሚናገሩ አሉ ፡፡ ይህ እነሱን አይመለከትም ፡፡ ነገር ግን አንዱ ማህበረሰብ በሌላው ላይ ጥርጣሬ የሚፈጥርና ወደ  ግጭት የሚወስዱ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉት ላይ ነው ትኩረት የተደረገው ፡፡ እነኝህን ገጾችና የሚንቀሳቅሷቸውን ግለሰቦች ተጠያቂ ለማድረግ እየሠራን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡የፍትህ ተደራሽነት ጥያቄ በደቡብ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች
የግንዛቤ ሥራ
በቀጣይ ህብረተሰቡ ማህበራዊ መገናኛ አውታሮችን በአግባቡ እንዲጠቀም ያስችላሉ ያሏቸው ሥራዎች ለማከናወን መታቀዱን የጠቀሱት የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊው  “ ህብረተሰቡም ሆነ ግለሰቦች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚችሉባቸው ሥልጠናዎችን ለመስጠት አቅደናል፡፡ ይህም እርስ በእርስ ለመማር ሀሳብና ትችቶችን በአግባቡ ወደ መንግሥት ለማድረስ የሚያስችል የመማማሪያ መድረክ ለመፍጠር ያስችላል ብለን እናምናለን “ ብለዋል ፡፡
በኢትዮጵያ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም ዙሪያ አዎንታዊም አሉታዊም አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ይደመጣል ፡፡ አንዳንዶች ሀሳባቸውን በመደበኛ መገናኛ ዘዴዎች ለመግለጽ ዕድል ለተነፈጉ ዜጎች ጥሩ አማራጭ መሆናቸው ሲጠቅሱ ሌሎች ደግሞ በአንጻሩ የጥላቻ ንግግሮችና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ለመቆጣጠር ጠበቅ ያለ የመንግሥት ክትትል ወሳኝነት እንዳለው ይናገራሉ ፡፡

አቶ ተመስገን ካሳ፤የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ፀሀይ ጫኔ

ሂሩት መለሠ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW