1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ውሎ እና የጸጥታ ይዞታ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 25 2015

ግጭት ሲካሄድባቸው በሰነበተው በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች በዛሬው ዕለት ከሰሞኑ የተሻለ መረጋጋት መኖሩን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ። በአንጻሩ በምዕራብ ጎጃም ፈረስ ቤት በመባል በሚታወቀው አካባቢ በዛሬው ዕለት በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጠናከረ ውጊያ በመካሄድ ላይ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ፎቶ ከማኅደር፤ ላሊበላ ላይ የፋኖ ታጣቂ
ግጭት በሰነበተባቸው የአማራ ክልል ከተሞች በዛሬው ዕለት ከሰሞኑ የተሻለ መረጋጋት ቢኖርም በሌሎች ከተሞች ደግሞ ከትናንት ጀምሮ ውጊያ መኖሩን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ። ፎቶ ከማኅደር፤ ላሊበላ ላይ የፋኖ ታጣቂ ምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

የአማራ ክልል ውሎ እና የጸጥታ ይዞታ

This browser does not support the audio element.

ግጭት ሲካሄድባቸው በሰነበተው በተለያዩ የአማራክልል ከተሞች በዛሬው ዕለት ከሰሞኑ የተሻለ መረጋጋት መኖሩን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ። በአንጻሩ በምዕራብ ጎጃም ፈረስ ቤት በመባል በሚታወቀው አካባቢ በዛሬው ዕለት በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጠናከረ ውጊያ በመካሄድ ላይ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

ካለፈው ሳምንት ዓርብ ማለዳ ጀምሮ ጠንከር ያለ ውጊያ የተካሄደባት የደብረማርቆስ ከተማ ከትናንት ጠዋት ጀምሮ የጥይት ተኩስ እንደማይሰማባት ፤ ዛሬም ሰው ከቤቱ መውጣት መጀመሩን ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ይገልጻሉ። «ከትናንት ከሦስት ሰዓት ጀምሮ ተኩስ የለም ቆሟል፤ ከአንድ ሰዓት እስከ ሦስት ሰዓት ከበድ ያለ ተኩስ ነበር» ያሉት አንደኛው የደብረ ማርቆስ ነዋሪ፤ ከዚያ ወዲያ እስከ ዛሬ ድረስ ተኩስ አይሰማም ነው ያሉት። ተመሳሳይ አስተያየት የሰጡት ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪም ዛሬ ሁኔታው በመረጋጋቱ ሰው ከቤት መውጣት እንደቻለ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከተማ ውስጥ በተለይ እሑድ ዕለት ሕዝብ ከቤተክርስቲያን በሚመለስበት ሰዓት አካባቢ በተካሄደው ውጊያ በርካቶች መጎዳታቸውን፤ የሞቱትም ጥቂት እንደማይባሉም ነው የገለጹልን። ደብረማርቆስ የወትሮው እንቅስቃሴ ከቆመ ወር ገደማ እንደሆነ ያመለከቱት የከተማዋ ነዋሪዎች፤ ከተማዋ ላይ በአየር ጥቃት ደርሷል የሚባለውን ግን አላረጋገጡም።

ካለፈው ሳምንት ዓርብ ማለዳ ጀምሮ ጠንከር ያለ ውጊያ የተካሄደባት የደብረማርቆስ ከተማ ከትናንት ጠዋት ጀምሮ የጥይት ተኩስ እንደማይሰማባት ፤ ዛሬም ሰው ከቤቱ መውጣት መጀመሩን ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ፎቶ ከማኅደር፤ ጭና በአማራ ክልልምስል AP/picture alliance

ደብረማርቆስ ከተማ በከባድ መሳሪያ ተኩስ ስትረበሽ መሰንበቷን ያመለከቱት ነዋሪዎቹ የሚሰሙት ከባድ የጦር መሣሪያ ድምጽ ከምድር ይተኮስ ከሰማይ ማወቅ እንደማይችሉ ነው የተናገሩት። እንዲያም ሆኖ ሄሊኮፕተሮች በከተማዋ ላይ ሲያንዣዝቡ እና ሲመላለሱ መመልከታቸውን ግን ገልጸዋል። ሌላዋ ስለጸጥታው ይዞታ የጠየቅናቸው ነዋሪ በበኩላቸው ከከባድ መሣሪያው ተኩስ ሽሽት በየቤቱ የተከተተው ኅብረተሰብ ለረሃብም መዳረጉን ነው የሚገልጹት።

ይኽ በእንዲህ እንዳለም በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ከተማ የተረጋጋች ቢሆንም በዙሪያዋ የሚገኙ ከተሞች የጸጥታ ይዞታ ግን አስተማማኝ እንደማይመስል ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።  በሰሜን ሸዋ መንዲዳ ላይ ግጭት እንደነበር፤ የመከላከያ ሠራዊት ደነባ መግባቱን የገለጹልን የአካባቢው ነዋሪ፤ «በሕዝባዊ ኃይሉ ስር» በመሆኗ ያመለከቱት እነዋሪ ከተማ የተረጋጋች መሆኑን ይናገራሉ። በአማራ ክልል ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተፋላሚ ኃይሎች ወደ ውይይት እንዲመጡ ቀደም ሲል የአፍሪቃ ኅብረት እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም የአውሮጳ ኅብረት ጥሪ አቅርበዋል። እስካሁን ግን በይፋ ይኽን በተመለከተ እንቅስቃሴ አልታየም። እንደያም ሆኖ ግን የክልሉ መስተዳድር ካቢኔ በዛሬው ዕለት ስለ2016 የበጀት ረቂቅ እና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ በባሕር ዳር ከተማ መወያየቱን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW