1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት በሱዳን ጦር ሠራዊትና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 7 2015

ሱዳንን በጋራ በሚመሩት የሀገሪቱ ጦር ሠራዊት እና የፓራሚሊታሪ ኃይል መካከል የተከሰተው ግጭት ነዋሪዎችን እጅግ ማሥጋቱ ተዘግቧል ። የሱዳን ጦር በሀገሪቱ ጠንካራ የሆነው እና ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) የሚል ስያሜ ያለው የፓራሚሊታሪ ኃይል እንቅስቃሴ ማድረጉ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል ።

Sudan | Unruhen in Khartoum
ምስል - /AFP

የጦር ሠራዊቱና የፈጥኖ ደራሹ ግጭት

This browser does not support the audio element.

ሱዳንን በጋራ በሚመሩት የሀገሪቱ ጦር ሠራዊት እና የፓራሚሊታሪ ኃይል መካከል የተከሰተው ግጭት ነዋሪዎችን እጅግ ማሥጋቱ ተዘግቧል ። የሱዳን ጦር በሀገሪቱ ጠንካራ የሆነው እና ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) የሚል ስያሜ ያለው የፓራሚሊታሪ ኃይል እንቅስቃሴ ማድረጉ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል ሲል አስጠንቅቆ ነበር ። የተባለውም አልቀረ ። ዛሬ ካርቱም ውስጥ በጦር ጄቶች ጭምር የታገዘ ውጊያ ነበር ። በጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በቅጽል ስማቸው «ሔሜድቲ» የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር «ግልፅ የሆነ የሕግ ጥሰት እየፈጸመ ነው» ሲል ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚያዙት ጦር ሠራዊት አስጠንቅቆ ነበር ። በሁለቱ ኃይሎች መካከል ያለው የረዥም ጊዜ ፍትጊያ እና ፍጥጫ ወደለየለት ግጭት ማምራቱ ነዋሪዎችን አሳሳስቧል ። ናፊሳ ሱሌይማን የሁለቱ ጄኔራሎች ፍትጊያ የሥልጣን ነው ይላሉ ።

«አል ቡርሃን እና ሔሜድቲ የሚናቆሩት ለሥልጣን ነው ። እኛ የምንታገለው ደግሞ የሚላስ የሚቀመስ ለማግኘት ነው ። እነሱ የሚነታረኩት ለሥልጣን፤ ሀገሪቷን እና ሕዝቡን ለመዝረፍ ነው ። የእኛ ትግል እነሱ ያላቀረቡልንን ለማግኘት ለምግብ፣ ለመጠጥ ፣ ለትምሕርት እና ለጤና አገልግሎት ነው ። ታዲያ ለምንድን ነው የሚጣሉት?»

በርካታ ሱዳናውያን በሁለቱ ጄነራሎች የሚመሩት ኃይሎች ፍጥጫ ሥጋት ወደ ግጭት ማምራሩ እጅግ አሳስቧቸዋል ። ወጣት ዓሊ ሲዲንግ ሥጋታቸውን አስቀድመው ከገለጡ የሱዳን ዜጎች መካከል አንዱ ነው ።

«ሀገራችን ጎዳናዎቿ በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እና ወታደሮች ተሞልታ ወደ ጦርነት ስታመራ ማየት አንፈልግም ። ይህ ሁኔታ ህዝቡን አሥግቷል ። ሁኔታው ዜጎች እፎይ እንዲሉ ይረጋጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ። »

ተደጋጋሚ ጸረ መንግሥት ተቃውሞ የማያጣት የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ውስጥ የተቃውሞ ሰልፈኞች በምሽትምስል picture-alliance/AA/M. Hjaj

የሱዳን የረዥም ዘመን መሪ ፕሬዚደንት ዖማር ሐሰን ኧል በሽርን መንግሥት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2019 ለመጣል በሱዳን ዓመጽ ሲቀጣጠል የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ከሀገሪቱ ጦር ሠራዊት ጋር አብሮ ነበር።  የሁለቱ ጥምረት በ2021 ሌላ የመፈንቅለ መንግሥት ሲደረግም ተጠናክሮ ነበር ።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ከ20 ዓመት በፊት ብቅ ያለው በዳርፉር ቀውስ ወቅት ነው ። ከዚያን ጊዜ በኋላም በሒደት አቅሙን እያጎለበተ የመጣ ብርቱ ኃይል ሆኗል ።  በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፓራሚሊታሪው መካከል ፍጥጫው እያየለ መምጣቱ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደገፈው የሲቪል አስተዳደር እንዳይመሠረት እንቅፋት ሆኗል።

በሱዳን ኃይላት ስምምነት መሠረት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሲቪል አስተዳደር ሥልጣኑን ሊይዝ ይገባ ነበር።  የሱዳን ዋናው የዴሞክራሲ ጥምረት ቀውሱን የሚፈጥሩት የዖማር አል በሽር ደጋፊዎች ናቸው ይላሉ ። የፈጥኖ ደራሹ አዛዥ ሔምዴቲ በምእራቡ ዓለም የሚደገፈው የሲቪል መንግሥትን ከጦሩ ጋር ተባብረው በመፈንቅለ መንግሥት ማስወገዳቸው እንደሚጸጽታቸው ገልጠዋል ። በምንም መልኩ ቢሆን የዖማር አል በሽር ደጋፊዎች ወደ ሥልጣኑ እንዲመጡ አይፈልጉም ። ጦሩ ደግሞ ከፈጥኖ ደራሹ ጋር በማድርገው ድርድር ፖለቲከኞች ጣልቃ እንዳትገቡ ሲል አሳስቧል ። የሱዳን ውጥረት ወደ ግጭት አምርቶ ዛሬ ካርቱም ውስጥ በአየር መንገዱ እና  ሌሎች ቁልፍ ታዎች ብርቱ ውጊያ ነበር። ሱዳን ወደየት እያመራች ይሆን?

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW