1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት በአጣዬ

ሰኞ፣ መስከረም 26 2012

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን ነዋሪዎችና የመንግስት ባለስልጣናት ተናገሩ፡፡ መንግስት “ለግጭቱ ተጠያቂው ኦነግ ነው” ሲል ገልፆአል። ኦነግ በበኩሉ “ተዋጊ ሰራዊት የለኝም” ባይ ነዉ።

Äthiopien Amhara Nationalpark
ምስል DW/A. Mekonnen

ግጭት በአጣዬ

This browser does not support the audio element.

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን ነዋሪዎችና የመንግስት ባለስልጣናት ተናገሩ፡፡ መንግስት “ለግጭቱ ተጠያቂው ኦነግ ነው” ሲል ገልፆአል። ኦነግ በበኩሉ “ተዋጊ ሰራዊት የለኝም” ባይ ነዉ። አሁንም ተኩስ መኖሩንና ከተማዋ በታጣቂዎች መከበቧን የአካባቢው ባለስልጣናትና የከተማዋ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ታጣቂዎቹ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የተባለው ድርጅት ሰራዊት ናቸው ብለዋል። ኦነግ በበኩሉ የታጠቀ ሰራዊት የለኝም ክሱ መሰረት የለውም ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በአለፈው ዓመት በከተማዋ ተመሳሳ ግጭት ተፈጥሮ የሰው ህይወት አልፏል፣ ንብረት ወድሟል አብያተ ክርስቲናት ተቃጥለዋል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በከተማዋ የአማራ ልዩ ኃይል በሰፈረበት አካባቢ አንድ የታጠቀ ግለሰብ  ሳይፈቀድለት ወደ ወታደሮቹ ሲቀርብ ለመቆም ፈቃደኛ ባለመሆኑ በተወሰደ እርምጃ መገደሉንና ያን ተከትሎ ከተለያዩ የከተማዋ አቅጣጫዎች የኦነግ ሰራዊት አባላት ተኩስ መክፈታቸውንና  የግጭቱ መንስኤም ይህ እንደሆነ የሰሜን ሽዋ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መመሪያ ኃላፊ አቶ ማሙሽ ይልማ ለዶይቼ ቬለ «DW» ተናግረዋል፡፡
ታጣቂው ኃይል የአጣዬን ከተማ እየከበበ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ማሙሽ የመንግስት የፀጥታ አካላት በአካባቢው ቢኖሩም ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው የአጣዬና የኤፍራታ ነዋሪዎች ከተማዎቹን ለቅቀው እየወጡ አንደሆነም አመልክተዋል፡፡
አንድ የአጣየ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ከትናንትናው የተሸለ ቢሆንም የተኩስ ድምፅም ከጠዋት ጀምሮ ይሰማል፤ ወደከተማዋ የሚያስገቡና የሚያስወጡ መንገዶች ዝግ ናቸው፣ የመከላከያ፣ የልዩ ኃይልና የፌደራል መንግስት የፀጥታ ኃይሎች ቢኖሩም መረጋጋት የለም ብለዋል፡፡ ታጣቂው ኃይል ኦነግ እንደሆነ የሚናገሩት እኝሁ ነዋሪ 6 ሰዎች መሞታቸውን ማየታቸውን አመልክተዋል። 
የዞኑ የኮሙዩኒኬሽን መምሪ ኃላፊ አቶ ማሙሽ እንደሚሉት ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር ሦስት ሲሆን የቆሰሉት 5 መሆናቸውን ገልፀዋል። የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ በስልክ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ “ አጣዬ ኦነግ ምን ሊሰራ ይመጣል፣የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሰራዊት እንደሌለው ብዙ ጊዜ መላልሰን ተናግረናል በመሆኑም ስሞታው ውሸት ነው ፡፡” ብለዋል።
በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ትናንት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ-ብርኃን የሚወስደው አቢይ ጎዳና እስከ ምሽት 5 ሰዓት ድርስ ሸኖ ከከተባለ ቦታ ላይ ተዘግቶ እንደነበር የሰሜን ሽዋ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መመሪያ ኃላፊ አቶ ማሙሽ ይልማ ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን በታጣቂዎችና በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በተመሳሳ የሰው ህይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ ይታወሳል ። 

ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW