1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት የወለደው ቀውስ በአማራ ክልል

ዓርብ፣ ነሐሴ 24 2016

«ሁሉም ሰው ፊቱ ጠቁሯል።ስለችግሩ አልቅሼ ብናገር ደስተኛ ነኝ።መንግስት ሰራተኛ ነኝ ለመኖር ተቸግሬ ነው ያለሁት።»ካሉ በኋላ፤ስደት ሁሉ እያሰብን ነው ያለን አሁን።በጣም ተቸጋግረን ማለት ነው።ያለው «ሪያሊቲ» ይህ ነው።»ብለዋል አንድ የክልሉ ነዋሪ ችግሩን ሲያስረዱ ።

በአማራ ክልል አዊ ዞን
በአማራ ክልል አዊ ዞን ከአንድ ዓመት በፊት ትጥቅ ፈቱ የተባሉ ሚሊሽያዎችምስል Awi zone communication office

ግጭት የወለደው ቀውስ በአማራ ክልል

This browser does not support the audio element.


በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደውን ግጭት ተከትሎ  ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን  አንዳንድ የክልሉ   ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በአካባቢያቸው ወጥቶ መግባት እና መደበኛ ሥራዎችን ማከናወን ፈተና ከመሆኑ ባሻገር፤ በትራንስፖርት እና በጤና አገልግሎት ችግር  ሰዎች ለሞት እየተዳረጉ ነው።

ነዋሪዎችን ያማረረው የትራንስፖርት ችግር 

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት በክልሉ የሚገኙ ታጣቂ ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታትና ልዩ ኃይሉንም ለመበተን  በሚል በወሰደው ርምጃ  ባለፈው ዓመት ሐምሌ በመንግስት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው  ግጭት፤ የክልሉን ነዋሪዎች ለከፋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየዳረጋቸው መሆኑን ገልፀዋል።  ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስቤት አካባቢ የሚኖሩ አንድ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ እንደገለፁት «ሕዝቡ ያጋጠመው ችግር ከሚችለው በላይ» ነው።ሰሞኑን ካጋጠመው የመጓጓዣ ችግር ይጀምራሉ።
«መንገድ ዝግ ነበረ። በዚያ ላይ ቀደም ሲል አስፓልቱ ሊሰራ ታርሶ ስለነበር መንገዱም ተበላሽቶ ነበር።እና እነዚህ ተደራራቢ ችግሮች ህዝቡን ለበለጠ ችግር ዳርጎታል ብዙ ለህክምና ሪፈር የተባሉ ሰዎች  በዚህ ምክንያት በሽቸው እየባሰ እየተሰቃዩ ነው።ችግሩ በጣም የከፋ ነው። ህዝቡ ከሚችለው በላይ።ችግር ላይ ወድቋል።» በማለት ገልፀዋል።

 እናቶች እና ሕጻናትን ወደ ጤና ተቋም መውሰድ አስቸጋሪ ነው

ሌላው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው።«ችግር ላይ ነው ያለነው።ትምህርት ቤት የሚባል የለም።የመንግስት መስሪያ ቤት ሁሉ አልፎ አልፎ የመንግስት ሰራተኛ ፈርሞ ይመለሳል።ከዚያ ውጭ  ስራ የለም ።ትምህርት ያው ዓመቱን ሙሉ ተቋርጧል አሁንም ተስፋ የለውም። የወረዳው ህፃናት ትምህርት አቋርጠው ነው ያሉ። ዘንድሮም ተስፋው የተሟጠጠ ነው።» ብለዋል።

በክልሉ ምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ ነዋሪ የሆኑና ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ እና ድምፃቸውም እንዲቀየር የፈለጉ ሌላው የክልሉ ነዋሪ በበኩላቸው «ሰሞኑን ከፋኖዎች ተላለፈ በተባለ ጥሪ ትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ ነበር»።ይሁን እና ትዕዛዙ ተነስቷል በሚል ተቋርጦ የነበረው አገልግሎት በጥቂቱም ቢሆን መልሶ መጀመሩን ገልፀዋል።  በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር  ሳቢያ ግን አሁንም ቢሆን በኅብረተሰቡ አጠቃላይ  እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው ጫና ከፍተኛ  መሆኑን ያስረዳሉ።«መጠነኛም ቢሆን አሁን ላይ እንቅስቃሴዎች አሉ።በአጠቃላይ እንቅስቃሴውን ካየነው ግን በጣም አስቸጋሪ ነው።የፀጥታ ጉዳዩ በትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ የፈጠረው ጫና ከፍተኛ ነው። የሱ ጫና ደግሞ በሁሉም ተግባራችን እና እንቅስቃሴያችን ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው።እንዳጋጣሚ እኔ የምሰራው በጤናው ሴክተር ነው እና እንደ ልብ እናቶችን፣ህፃናትን ሪፈር ወደ ተባሉበት የጤና ተቋም መውሰድ አስቸጋሪ ነው።የህክምና ግብዓቶችን ከሚጠበቁበት ተቋም ማምጣት በጣም አስቸጋሪ ነው።እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ሌሎች መደበኛ የሸቀጥ አገልግሎቶችንም እየፈተነ ነው። በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ነው ህብረተሰቡ እያለፈ ያለው።»ሲሉ ገልፀዋል።

በአማራ ክልል በጦርነት የወደመ ወታደራዊ ተሽከርካሪምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

እንደ ልብ ወጥቶ መግባት እና መደበኛ ሥራዎችን ማከናወን አይቻልም

ነዋሪው አያይዘውም በአካባቢው በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል በየቀኑ በሚደረገው ግጭት «በየቀኑ የጥይት ድምፅ መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል።»ይላሉ።በዚህም ወጥቶ መግባት እና መደበኛ ስራዎችን ማከናወን ለአካባቢው ነዋሪ ፈተና መሆኑን ይናገራሉ።
 «ተኩስ በየጊዜው የሚሰማበት አካባቢ ነው።የወረዳ የገጠር ቀበሌዎች አብዛኞቹ በሚባል ሁኔታ በፋኖ ቁጥጥር ስር ነው ያሉት።የከተማ ቀበሌዎች እና አስፓልቱን ይዞ ነው የመንግስት የፀጥታ ተቋማት ያሉት ስለዚህ በዚህ ሁኔታ እንደ ልብ ወጥቶ መግባት እና መደበኛ ስራዎችን ማከናወን አስቸጋሪ ነው።በየጊዜው የተኩስ ድምጾች ይሰማሉ።የንግድ ተቋማት ይዘጋሉ።»በማለት ተናግረዋል።

በሰሜን ጎጃም ዞን ጎንጅ አካባቢ የሚኖሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ  ድምፃቸውም እንዲቀየር የፈለጉ ሌላው አስተያየት ሰጪም «ስለሁኔታው ለማስረዳት ቃላት የለኝም»ሲሉ ምሬታቸውን ይገልፃሉ። «ሁሉም ሰው ፊቱ ጠቁሯል።ስለችግሩ አልቅሼ ብናገር ደስተኛ ነኝ።መንግስት ሰራተኛ ነኝ ለመኖር ተቸግሬ ነው ያለሁት።»ካሉ በኋላ፤ስደት ሁሉ እያሰብን ነው ያለን አሁን።በጣም ተቸጋግረን ማለት ነው።ያለው «ሪያሊቲ» ይህ ነው።»ብለዋል ችግሩን ሲያስረዱ ።
በመሆኑም መንግስት ኅብረተሰቡን ለመታደግ ችግሩን በሰላም እንዲፈታ ጠይቀዋል።በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር  የተጀመረውን ግጭት ተከትሎ፤  የክልሉ ነዋሪዎች ከገጠማቸው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ባሻገር በግጭቱ ሰላማዊ ሰዎች የጥቃት ሰለባ መሆናቸውንም የመብት  ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል። 

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለማካተት የአማራ ክልል የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ሀላፊን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW