1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች አዋሳኝ የተቀሰቀሰው ግጭት

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 17 2018

"በንብረትም ላይ በሰውም ላይ ጉዳት ደርሷል በጨፋ ሮቢት ቀጠና ማለት ነው። በሰሜን ሸዋ ደግሞ ማጀቴ አቅጣጫ ማለት ነው። ከ340 በላይ የቀንድ ከብቶች ተወስደዋል። የቀበሌ አመራርን ጨምሮ የሰው ህይወት ተቀጥፏል።

የሰሜን ሽዋ የተወሰነ ክፍል መልክአ ምድር፤
ፎቶ ከማሕደራችን
የሰሜን ሽዋ የተወሰነ ክፍል መልክአ ምድር፤ ፎቶ ከማሕደራችንምስል፦ Seyoum Getu/DW

በአማራ ክልል በተከሰተ ግጭት 6 ሰዎች ተገደሉ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እናየኦሮሞ ብሔረሰብዞኖች አዋሳኝ በሆነችው በጨፋ ድሬ ቀበሌ ጃራ ወንዝ አካባቢ በተከሰተ ግጭት፣ የቀበሌ ሊቀመንበርን ጨምሮ ከስድስት በላይ ሰዎች መገደላቸውና በርካታ ከብቶች መዘረፋቸው ተነገረ። ለግጭቱ መነሻነት የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አመራሮች እና ነዋሪዎች "በከብት አጋጆች ላይ የተከፈተ ጥቃት እና የጽንፈኛ ኃይሎች ሴራ" መሆኑን ቢገልጹም፤ የሰሜን ሸዋ ዞን የኤፍራታ ግድም ወረዳ አመራር በበኩላቸው ግጭቱ የተቀሰቀሰው "በደረሰ ሰብል ላይ ከብቶች ለግጦሽ በመለቀቃቸው" መሆኑን ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ዞን አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች  የተዘረፉ የቀንድ ከብቶችን  ለማስመለስ በጋራ እየሰሩ መሆኑ ታውቋል።

በአማራ ክልልየሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አዋሳኝ ቦታ ላይ በተከሰተ ግጭት የቀበሌ አስተዳዳሪን ጨምሮ የሰዎች ህይወት ማለፉን እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከብቶች መዘረፋቸው ተነገረ። ግጭቱ የተከሰተው በጨፋ ድሬ ቀበሌ ልዩ ቦታው ጃራ ወንዝ በሚባል አካባቢ ሲሆን፣ በጉዳቱ ከስድስት ሰዎች በላይ ከሁለቱም ወገን መሞታቸው ተነግሯል።
እንደ አባገዳ አህመድ መሐመድ ገለጻ ከሆነ ግጭቱ በሚያዝያ 11 የተከሰተ ሲሆን፣ ከብት ለማገድ በወጡ ልጆች ላይ ተኩስ መከፈቱ የግጭቱ ምክንያት ነው ብለዋል።

"አሁንም ሴቶች እና ህጻናት ከብት ለማገድ ወደ ላይ አውጥተው እንግዲህ ሰላም ብሎ ነው ያወጡት። በዛ በክልላቸው ውስጥ ያው እንግዲህ የታጠቀ ኃይል መጣና ልጆችንም አባረሩ፣ አንድ ሴትም ገደሉና ወደ ሶስት መቶ አርባ የሚሆን ከብት ወስዶት ሄደ። 'ለምን ይሄ ከብት ይወሰዳል?' ብሎ የመንግስት አካል የቀበሌ ሊቀመንበር ሁላ እዛ ሄዶ ለማገልገል መሀል ሲገባ እሱም ተመትቶ ሞተ። ሁሉም እንግዲህ ያው የጸጥታ ኃይል ነው የሞተው።"

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የጨፋ ወረዳ ነዋሪ አቶ ኡስማን አሊ አካባቢው በተደጋጋሚ በተለያዩ የታጠቁ ክፍሎች ጥቃት እየተፈጸመበት በርካቶች ሲሞቱ ከፍተኛ የንብረት ዘረፋ ይካሄድበታል ብለዋል።

"በታች በሸኔ፣ በላይኛው ፋኖ ተያያዝን። እኛ መቼ ገባን አልገባንም። በላይ በኩል የገበሬ ከብት ወደ  ይወስዳሉ። ዋናኛው ደግሞ እኛ ጥላቻ አለ በቃ ተጨራረሰ፣ ሰው አለቀ። ምንም መላ የለም። በታች ደግሞ በሸኔ በኩል በቃ ዘረፋ ነው፣ ጠመንጃ አልቀረ፣ ገንዘብ አልቀረ እየዘረፉ ነው። በላይኛው እንደዛ ነው።"

የአስተዳዳሪዎች ምላሽ

የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አወል እንድሪስ በጥቃቱ ከ340 በላይ የቀንድ ከብት መዘረፉን እና ሰዎች መሞታቸውን ይናገራሉ። ጥቃት አድራሾቹ የአካባቢውን ህዝብ ሰላማዊ ግንኙነት ለማወክ የወሰዱት እርምጃ ነውም ብለዋል።

"በንብረትም ላይ በሰውም ላይ ጉዳት ደርሷል በጨፋ ሮቢት ቀጠና ማለት ነው። በሰሜን ሸዋ ደግሞ ማጀቴ አቅጣጫ ማለት ነው። ከ340 በላይ የቀንድ ከብቶች ተወስደዋል። የቀበሌ አመራርን ጨምሮ የሰው ህይወት ተቀጥፏል። ሁለቱን ህዝብለማጋጨት አቅዶ ነው የሰራው ይሄ ጽንፈኛ። እዚህ ቀጠና ላይ ህዝብ ለህዝብ ሰላም መሆኑ፣ በዚህ በሁለቱ ህዝብ መሀል ሰላም መፈጠሩ ያመመው ጽንፈኛ ነው ይሄን ወርዶ ያደረገው።"

በሌላ በኩል በሰሜን ሸዋ ዞን የኤፍራታ ግድም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አበራ መኮንን የግጭቱ መነሻ በደረሰ ሰብል ላይ ከብት ለግጦሽ መልቀቅ ነው ይላሉ።

"ከብት የተወሰደ አለ፣ ሰውም የሞተ አለ። ከላይ ደግሞ በጣም ብዙ የተቃጠለ እህል አለ፣ የተበላ ማሽላ አለ፣ የተገደለ ሰው አለ። መነሻቸው ምንድነው? እዛ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች ማሽላ ላይ፣ እህል ላይ ከብት ለቀው ነው። እንደ መነሻ ግጭታቸው። እኛ እንደ አመራር አብረን እየሰራን ነው። ንክኪው እየተነሳ በዛ ምክንያት ነው።"

 ግጭቱን ለመፍታት

አሁን ላይ አካባቢውን ወደ ነበረበት መልካም ጉርብትና ለመመለስ የሁለቱ ዞን አመራሮች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ነው አቶ አወል እንድሪስ የገለጹት።

"የሁለቱ ዞን አመራር፣ አመራር ለአመራር ተገናኝቶበጉዳዩ ላይ መክሮ ህዝብን እያገኘ እያረጋጋ ነው ያለው። ከዚያም በላይ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ጭምር በጋራ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። በዛ በኩል ያሉ ሽማግሌዎችን አግኝቶ ማወያየት፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ፣ ቢያንስ የተወሰደውን ንብረት እንዴት አድርጎ ነው መመለስ የሚቻለው? መተካት የሚቻለው? የሚለውን ምክክር እየመከረ ነው ያለው።"

በግጭቱ በሁለቱም በኩል ስድስት ሰዎች ሞተዋል የሚሉት አቶ አበራ መኮንን፣ ግጭቱ እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላት በመኖራቸው እነሱን የመከላከል ስራ ይሰራልም ብለዋል።

"ከላይ ወደ ሁለት ሰው ሞቷል፣ ከቆሰለ ውጪ። ከታች ወደ አራት ሰው ሞቷል። በዚህ ልክ ነው የምንገመግመው። ከዛ ውጪ በኢስቲሜት ባይደረግም በጣም ብዙ ሄክታር ማሽላ ተበልቷል፣ ተጨማሪ ጤፎች ተቃጥለዋል፣ ተጨማሪ አገዳ ተቃጥሏል። ከብቶቹን ደግሞ ወደ ሁለት መቶ አርባ አካባቢ የሚገመቱ ከብቶች ተወስደዋል ይባላል። የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ እየተደዋወሉ እየሰሩ ነው፣ እኛ እየሰራን ነው። ግን ምንድነው ከላይ ነገሮች ከተባባሱና ትንኮሳው ከባባሰ በኋላ ከብት ከተወሰደ በኋላ እንዳይመለስ የሚያደርግ ጽንፈኛ አለ ከብቶቹን እንዳይመለሱ። መነሻው ግን መነሻው ምንድነው ከተባለ ከብት ተለቆ ነው እህል ላይ። የሚነሳው ሁልጊዜ በዚህ ነው።"
ኢሳያስ ገላው
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW