1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭቶች ሰላማዊ መፍትሔ ማፈላለግ እና የሲቪክ ማህበረሰብ ሚና

ረቡዕ፣ ግንቦት 30 2015

ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ግጭቶች ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው በሚደረግ ጥረት ያልተገደበ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ። ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር እና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የጠየቀው የድርጅቶቹ ምክር ቤት የሰላም ስምምነቶች በሁሉም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ጠይቋል።

Karte Äthiopien Regionen EN

የሲቪክ ድርጅቶች ለግጭቶች ሰላማዊ መፍትሔ የማፈላለግ ሚና

This browser does not support the audio element.

ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ግጭቶች ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው በሚደረግ ጥረት ያልተገደበ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር እና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የጠየቀው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሰላም ስምምነቶች በሁሉም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ጠይቋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ 4400 ያህል የሲቪክ ድርጅቶች ፈቃድ አግኝተው በልማት፣ በሰብዓዊ ድጋፍ እና በዴሞክራሲ ባህል ዙሪያ የሚሠሩ ሲሆን ከግጭት ጋር ተያይዞ ለሚፈጠር መፈናቀል፣ አስቸኳይ ድጋፍ ምላሽ የሚሰጡ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ፣ የችግሩን ስፋት በሚያሳይ መልኩ ቁጥራቸው እያደገ መሆኑ ተነግሯል። እነዚህ "ድርጅቶች በልማት እና በዲሞክራሲ ሥርዓት እድገት ላይ አበረታች አስተዋጽኦ ማድረግ ችለዋል" በማለት የፍትሕ ሚኒስቴር እውቅና ሰጥቷቸዋል።

የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የፖለቲካ እና የንግድ ግብ ወይም ዓላማ ሳይኖራቸው ህብረተሰብን በልዩ ልዩ የሕይወት ፈርጅ ለማገልገል ከመንግሥት ፈቃድ ወስደው ይሠራሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ረገድ የጎላ ሥም ያላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት እና መንግሥታት በገንዘብ የሚደግፏቸው ሲቪል ድርጅቶች አሉ።

ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ባልተለያት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት ዜጎችን ከቤት ንብረት እያፈናቀለ፣ ውድመት እያስከተለ ፣ በርካታ ሚሊዮኖችን ለእርዳታ የሰው እጅ ጠባቂ አድርጓቸዋል።
አዲስ አበባ ውስጥ ጦርነትን ሸሽተው መጥተው ከሚታዩ እናቶችና ሕፃናት መካከል ጥቂቶቹን የሚደግፈው በቅርቡ የተመሰረተው ላይት የተባለው ድርጅት፣ የሲቪክ ድርጅቶች ሳምንት ሲከበር የበለጠ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሲጥሩ ካገኘናቸው መካከል አንደኛው ነው።
"እኛ ማንንም ሳይሆን ሰው ብቻ ይሁን ለተቸገረ ሰው እንደግፋለን። አሁን ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ ናት እና መርዳት ነው የምንፈልገው። ለምን እኛ እንበላለን እነሱም እንዲበሉ።" በማለት ተወካይዋ ገልፀዋል።

ፋርም ሬዲዮ የተባለው እና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የገበሬዎችን ሕይወት ለማቃናት ትምህርት በሰፊው በሬድዮ በመስጠት የሚታወቀው የካናዳው ድርጅት በተጨባጭ ለአርሶ አደሩ ምን አበርክቶ እንደሆን ጠይቀናል።
"ምርጥ ዘር የት እንደሚገኝ ፣ ማዳበርያ የት እንደሚገኝ ፣ በተለይ ገበራው የግብርና ምርቶችን የት እንደሚያገኝ ቤቱ ሆኖ በሬድዮ እየሰማ በተጨባጭ እውቀቱ እንዲሰራ አድርጎታል። ይህንን በተለይ በማር ፣ በስንዴ በጤፍ ላይ አበርክተናል።" ብለዋል ያነጋገርናቸው የድርጅቱ ተወካይ።

የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት ነው። ከዴሞክራሲያዊ እሴቶች እና ባህሎች የላቀ አማራጭ የለም በሚል መርህ ለዚሁ አጋዥ ነኝ ብሎ ይንቀሳቀሳል።
"ዴሞክራሲ ላይ በማቀንቀን ይሰራል። የሚሠራባቸው አምስት ዘርፎች አሉ። የዜጎች ተሳትፎ፣ የዲጂታል መብቶች፣ የሚዲያ አረዳድ ፣ ወጣቶች እና ሴቶችን ማጎልበት እንዲሁም ደግሞ የዴሞክራሲያዊነት ልኬት ሥራዎችን ይሠራል።"

ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር እና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የጠየቁት የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ የተኩስ አቁም ስምምነቶች በሁሉም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ጠይቋል።

የሲቪክ ድርጅቶች ሳምንት ዛሬ ሲጀመር የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞትዮስ በዝርዝር ባይገልፁትም  "መንግሥታዊ ያልሆኑ የሲቪክ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በልማት እና በዲሞክራሲ ሥርዓት እድገት ላይ አበረታች አስተዋጽኦ ማድረግ ችለዋል" በማለት እውቅና ሰጥተዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW