1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህጻናት ግድያ መጨመር

ሰኞ፣ ሰኔ 25 2010

በ2017 ዓ.ም በዐለም ላይ ከ10 ሺህ በላይ ሕጻናት የተገደሉ ወይም ለአካለ ጎደሎነት የተዳረጉ ሲሆን ከ8 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደሞ ለተዋጊነት ተልምለዋል ወይም በውጊያ እንዲሳተፉ ተደርገዋል፡፡ ሕጻናትን መጥለፍ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ለተዋጊነት መመልመል እና ለሕጻናት የሚደርስን ነፍስ አድን ዕርዳታ ሆን ብሎ ማስተጓጎል ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

Südsudan - Kindersoldaten
ምስል Getty Images/AFP/C. Lomodong

የህጻናት ግድያ መጨመር

This browser does not support the audio element.


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ ዘገባ በጎርጎሮሳዊው 2017 ግጭትና ጦርነት ባለባቸው ሀገሮች የሕጻናት ግድያ እና የከፋ ሰብዓዊ መብት ጥሰት በእጅጉ መጨመሩን አመለከተ፡፡ በተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ስም የወጣው ይኸው ዐመታዊ ዘገባ ይፋ የተደረገው ባለፈው ረቡዕ ነው፡፡ ዘገባው እንደሚለው እንደ ጎርጎሳዊያኑ አቆጣጠር በ2017 ዓ.ም በዐለም ላይ ከ10 ሺህ በላይ ሕጻናት የተገደሉ ወይም ለአካለ ጎደሎነት የተዳረጉ ሲሆን ከ8 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደሞ ለተዋጊነት ተልምለዋል ወይም በውጊያ እንዲሳተፉ ተደርገዋል፡፡ 
ሕጻናትን መጥለፍ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ለተዋጊነት መመልመል እና ለሕጻናት የሚደርስን ነፍስ አድን ዕርዳታ ሆን ብሎ ማስተጓጎል የመሳሰሉ አድራጎቶች በአሳሳቢ ሁኔታ ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነው የዋና ጸሃፊው ሪፖርት የገለጸው፡፡ ሕጻናት ቀደም ሲል ከታጣቂ ሃይሎች ጋር ባላቸው ግንኙነትም በተለያዩ ሃይሎች በእገታ ተይዘው እንደሚገኙ ያትታል- ሪፖርቱ፡፡ 
ሪፖርቱ ካካተታው 20 የግጭት ቀጠና ሀገሮች መካከል ደቡብ ሱዳን፣ ሱማሊያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ናይጀሪያ እና ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ይገኙበታል፡፡ 
ዘገባውን ያቀረቡት ለሕጻናት እና ግጭት ዘርፍ የዋና ጸሃፊው ልዩ መልዕክተኛ ቨርጅኒያ ጋምባ ናቸው፡፡
2017 በግጭት ቀጠናዎች ለሚኖሩ ሕጻናት በጣም አስቸጋሪ ዐመት ነበር፡፡ በሕፃናት ላይ የደረሱ ጥሰቶች እኤአ በ2016 ከነበረው 15 ሺህ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ 21 ሺህ ደርሷል፡፡ በጠቅላላው 6 ሺህ የተረጋገጡ ጥሰቶች በመንግስት አካላት ተፈጽመዋል፡፡ 15 ሺዎች ደሞ ከመንግስት መዋቅር ውጭ ባሉ ታጣቂ ቡድኖች የተፈጸሙ ናቸው፡፡ ከስምንት ሺህ በላይ ሕጻናት ደሞ ለውጊያ ተመልምለዋል ወይም በአውደ ውጊያ እንዲሳተፉ ተደርገዋል፡፡ 
የሕጻናት መብት ጥሰት ባለፈው ዐመት ለምን እንደጨመረ ቨርጅኒያ ጋምባ ሲያብራሩም እንዲህ ይላሉ፤
እንደሚመስለኝ የግጭቶቹ ባህሪ ነው፡፡ ያለፈው ዐመት በጣም ዘግናኝ ግጭቶች የታዩበት ዐመት ነው፡፡ አዳዲስ ግጭቶችም ተከስተዋል፡፡ ዐመቱን ሙሉ ግጭቶች ተሳሳይ አይደሉም፡፡ ባንድ ወሳኝ ወቅቶች ግጭቶች አንድን ወይም ሌላ ሥራ ለመቆጣጠር ሲባል አይተናል፡፡ በዚህ ጊዜ ንጹሃን ዜጎችን ከተዋጊዎች የመለየቱ ነገር ቸል ይባላል፡፡ በጣም ሲባባሱ እነ በሌላ ጊዜ ደሞ ቀዝቀዝ ሲሉ አይተናል፡፡ 
ዘገባው ለመብት ጥሰቱ መጨመር በደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ እና በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ያለው ግጭት ዐይነተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውንም ይገልጻል፡፡ 
በሱማሊያ ባለፈው ዐመት ሕጻናትን አስገድዶ መጥለፍ በእጥፍ ጨምሮ እንደተገኘ ነው ሪፖርቱ የሚገልጸው፡፡ አልሸባብ እስከ ዘጠኝ ዐመት ዕድሜ ያሉ ከ1700 በላይ ሕጻናትን አስገድዶ በማፈን ለተዋጊነት የተጠቀመባቸው ሲሆን ይህም ሸማቂው ቡድን በሕጻናት ተዋጊዎች ላይ ባለው ጥገኝነት አሁንም እየገፋበት መሆኑን ያረጋግጣል ሲል ይከሳል- የዋና ጸሃፊው ሪፖርት፡፡ ሸማቂው ቡድን ሕጻናትን በሃይል ያግታል፤ ወላጆችን እና መምህራንን በማስፈራራት እንዲያስረክቡት ያስገድዳል ሲል ከሷል፡፡ አልሸባብ በ75 ሕጻናት ላይ ጾታዊ ጥቃት እንዳደረሰ ሪፖርቱ የመዘገበ ሲሆን “ልዩ ፖሊስ” ሲል የጠቀሳቸው የኢትዮጵያ ጸጥታ ሃይሎችም በ10 ጾታዊ ጥቃቶች ተጠያቂ አድርጓቸዋል፡፡ የሱማሊያ መደበኛ ጦር ሠራዊትም 100 ያህል ሕጻናትን በተዋጊነት መልምሏል፡፡ 
በጠቅላላው በሱማሊያ 931 ሕጻናት መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን ለ208ቱ ግድያ አልሸባብን ነው ሪፖርቱ ተጠያቂ ያደረገው፡፡ ብዙዎቹ ሕጻናት የሞቱት የተለያዩ ሃይሎች በሚደረጉ ተኩስ ልውውጦች፣ በተቀበሩ ፈንጅዎች እና አየር ድብዳባ ሲሆን አልሸባብ ግን ሕጻናትን በአደባባይ ረሽኗል ይላል- ሪፖርቱ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ጦር (አሚሶም) 21 ሕጻናትን፣ የሱማሊያ ብሄራዊ ጦር ሠራዊት እና ፖሊስ 98 ሕጻናት እንዲሁም በሱማሊያ የሰፈሩ የኬንያ ወታደሮች ደሞ በተናጥል ስድስት ሕጻናትን እንደገደሉም ያትታል፡፡ 
በደቡብ ሱዳን ከተገደሉ 93 ሕጻናት መካከል ሪፖርቱ ለአብዛኛዎቹ ግድያ ተጠያቂ ያደረገው የመንግስት ጸጥታ ሃይሎችን ነው፡፡ በማዕከላዊ እና ምስራቃዊ ኢኳቶሪያ ግዛቶች አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ አብዛኛዎቹን ጾታዊ ጥቃቶች ያደረሱት እና ለአብዛኛዎቹ አስገድዶ ጠለፋዎች ተጠያቂ የተደረጉትም የመንግስት ሃይሎች ናቸው፡፡ በሀገሪቱ ከ1200 ሕጻናት በላይ ለተዋጊነት እንደተመለመሉም ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ ከቀዳሚው ዐመት ጋር ሲወዳደር ሰብዓዊ ዕርዳታን ሆነ ብሎ በማስተጓጎል ረገድ በርካታ እንቅፋቶች አጋጥመዋል፡፡ 
በሕጻናት ላይ የሚደርሰው መብት ጥሰት እጅግ አሳሰቢ ደረጃ ላይ ቢደርም አንዳንድ አወንታዊ ተስፋዎች መታየታቸውን ግን የተመድ ሪፖርት አልሸሸገም፡፡ ቨርጅኒያ ጋምባም እንዲህ ይላሉ፤
«መብት ጥሰቱ ቢጨምርም አንዳንድ መሻሻሎች ግን አይተናል፡፡ በተለይ ከግጭት ተዋናዮች ጋር መልካም መስተጋብር በፈጠርንባቸው የግጭት ቀጠናዎች ለተለያዩ አካላት ስልጠና በመስጠት እና የሕጻናትን መብት ጥሰት እንዲያቆሙ እና የመፍትሄ ርምጃዎችን እንዲወስዱ በማሳመን ረገድ፡፡ የሱዳን መንግስት ከዝርዝሩ መውጣቱም አስደሳች ነው፡ »

ምስል picture alliance/AA/UNICEF/S. Rich
ምስል Getty Images/AFP/M. Dahir
ምስል picture-alliance/dpa/AA/S. Bol

ቻላቸው ታደሰ
ኂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW