ጎርፍ፣ ሌላዉ የአፍሪቃዉያን መጥፊያ
ቅዳሜ፣ መስከረም 14 2015
ምስራቅ አፍሪቃ ዉስጥ ብዙ ሚሊዮኖች ለመራብ፣መፈናቀል፣ መሰደዳቸዉ የጉሎቱ ምክንያቶች ሁለት ናቸዉ።ድርቅና ጦርነት።ምዕራብ አፍሪቃ በጣሙን ናይጄሪያ እንደ ምስራቆቹ ሁሉ ግጭት፣ሁከትና ድርቅ ለብዙ ነዋሪዎች መጎዳት ሰበብ መሆናቸዉ ብዙz ጊዜ ተነግሯል።ሰሞኑን የከፋዉ ግን ጎርፍ ነዉ።
«እንደዚያ ነዉ» ይላሉ ሐሊማቱ ቱሬ ጎርፍ ካጥለቀለቃቸዉ መንደሮች የአንዱ ነዋሪ «ከባድ ድርቅ-ማብቂያዉ ከባድ ጎርፍ ነዉ» ቀጠሉ የ66 ዓመቷ ባልቴት።
«ጣዩ የእልሕ፣ የእልሕ፣ዝናቡ የእልሕ የእልሕ
ታርስበትም እንደሁ ቅብቅቡ ያዉልሕ»
አለ ነዉ ያሉት ኢትዮጵያዊዉ ገበሬ-በ1977 ፈጣሪዉን ሲያማርር።
አብዛኛዉ ዓለም ከዩክሬን ጦርነት በተረፈዉ ጊዜ የፓኪስታንን የዉኃ መቅሰፍት እያነሳ ሲጥል ናጄሪያን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ 300 ሰዎች በልቷል፤ ከ100 ሺሕ በላይ አፈናቅሏል።የናጄሪያ ብሔራዊ የአደጋ መከላከያ መስሪያ ቤት (NEMA) እንደሚለዉ ዘንድሮ የደረሰዉ ጎርፍ በሐገሪቱ የረጅም ጊዜ ታሪክ ደርሶ አያዉቅም።
ካለፈዉ ኃምሌ ጀምሮ ያለማቋረጥ የጣለዉ ዝናብ ያስከተለዉ ጎርፉ ብዙ ሕዝብ የጎዳዉ የሰሜናዊ ናይጄሪያ ሶስት ግዛቶችን ነዉ።ዮቤ፣ አዳምዋና ቦርኖ።ሶስቱ ግዛቶች የቦኮ ሐራም ሸማቂዎች፣ወርሮ በሎችና ሽፍቶች የሚያዉኳቸዉ አካባቢዎች በመሆናቸዉ ወትሮም ቢሆን በቂ እሕል አይመረትባቸዉም።ባለሙያዎች እንደሚሉት ያሁኑ ጎርፍ በሰዉ ሕይወት፣ አካልና ኑሮ ላይ ካደረሰዉ ጉዳት በተጨማሪ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሐብት፣ ንብረትና ሰብል አዉድሟል።
የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸዉ ከየቤቱ የተፈናቀለዉ ሕዝብም ሆነ ሌላዉ ነዋሪ ለዉሐ ወለድ ተላላፊ በሽታዎች ተጋልጧል እያሉ ነዉ።ዶክተር የርማ አሕመድ አዳሙ እንደሚሉት ሕዝቡን ከዉኃ ወለድ በሽታ ለመከላከል፣የመንግስትና የጤና ባለሙያዎች አስቀድመዉ መዘጋጀት፣ ሕዝቡን ማስተማርና ማስጠንቀቅ ነበረባቸዉ።
«ሰዎች የሚጠጡትንና የሚያበስሉበትን ዉኃ ማፍላት አለባቸዉ።መንግስትና የጤና ማዕከላት ሕዝቡን በተለይም ሕፃናትን ከተቅማት በሽታ ለመከላከል ለነዋሪዎቹ ዚንክ ኦክሳይድ፣ በዉኃ የተበጠበጠ ጨዉ ማደል፣ ለነዋሪዎቹም ጥቅሙንና አጠቃቀሙን ማስተማር ነበረባቸዉ።»
ይሁንና ሐኪሙ እንደሚሉት በሽታዉን ለመከላከል አስቀድሞ መደረግ የሚገባቸዉ ጥንቃቄዎች ባለመደረጋቸዉ በጎርፍ የተጥለቀለቁት አካባቢዎች ነዋሪዎች በተለይም ተፈናቃዮች ለበሽታዉ ታጋልጠዋል፤ አንዳዶችም በበሽታዉ እየተጠቁ ነዉ።
ዶክተር የርመን እንደሚያምኑት ባለስልጣናቱ የባለሙያዎችን ምክር ሰምተዉ አስቀድመዉ ሁነኛ ርምጃ ቢወስዱ ኖሩ ጎርፉ ያስከተለዉን በሽታና መሰል ችግሮችን አይደለም፣ ጎርፉ ራሱ የሚያደርሰዉን ጉዳት መቀነሰ ይቻል ነበር።«ፖለቲከኞች ግን ሰዉን የሚያስታዉሱት ድምፅ እንዲሰጣቸዉ ሲፈልጉት ብቻ ነዉ» አሉ ሐኪሙ።
«በመንግስት በኩል የመከላከሉ ዝግጅት ጨርሶ ተዘንግቷል።የተዘነጋዉ አደጋዉ ፖለቲካዊ ስላልሆነ ብቻ ነዉ።በመሰረቱ ግን የሰዉ ሕይወት ከሌለ ፖለቲከኛ መሆን አይቻልም።እንግዲሕ ፖለቲከኞቹ ነገሮችን የሚመለከቱት በዚሕ መንገድ ነዉ።እነሱ ለሰዉ ሕይወት ደንታ የላቸዉም።ደንታ የሚኖራቸዉ የድጋፍ ድምፅ በሚፈልጉበት ጊዜ ብቻ ነዉ»
60 ከመቶ የሚሆነዉ አፍሪቃዊ የሚኖርበት አካባቢ የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት አይደርስበትም ወይም ጥናት አይደረግበትም።ይሁንና ድርቅ፣ረሐብና ጎርፍ እንደሚኖር ለማወቅ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃን መጠበቅ አያስፈልገም። አንድ አካባቢ በተከታታይ ባገረረ ፀኃይ ከተመታ በኋላ የሚጥለዉ ዝናብ ከባድ ጎርፍ ማስከተሉን ለማወቅ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ከብዙ ዓመታት በፊት፣ ናጄሪያዊቱ ባልቴት ደግሞ በቅርቡ ያሉትን ማስተዋሉ በቂ ነዉ።አፍሪቃ ለሕዝቡ የሚያስብ አስተዋይ ፖለቲከኛ አላት ወይ እንጂ ጥያቄዉ።
የዓለም ሚትሪዮሎጂ ድርጅት በቅርቡ እንዳስታወቀዉ በቅርብ ዓመታት ዉስጥ ሱዳን፣ደቡብ ሱዳን፣ናጄሪያ፣ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብልክ፣ጎንጎ ሪፐብሊክ በተደጋጋሚ በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል።አብዛኞቹ ጎርፎች የደረሱት ከከባድ ድርቅ በኋላ ነዉ።ናጄሪያዊዉ ሐኪም እንዳሉት የአፍሪቃ ገዢዮች ከየአብያተ መንግስቶቻቸዉ ወጣ ብለዉ ቢያዩና ቢያስቡ የዝናብ እጥረት ድርቅ፣ ድርቁ ጎርፉ ማስከተላቸዉ ማወቅ፣ በየአደጋዉ የሚደርሰዉን ጉዳት ለመከላከል መዘጋጀት አይገዳቸዉም ነበር።የኒጀር ወንዝን የሚያጠናዉ ተቋም ኃላፊ ኢሳ ባካዮኮ እንደሚሉት መስሪያ ቤታቸዉ የዝናብ እጥረት-ድርቅ፣ የድርቅ ክረት-ዝናብ፣ ዝናብ ጎርፍ የማስከተላቸዉን ዑደት የተረዳዉ ዓለም ስለ ዓየር ንብረት ለዉጥ ለመነጋገር ከመሰብሰብ፣ መጮሕ-መጨቃጨቁ ብዙ ዓመት በፊት ነዉ።ምናልባት ኢትዮጵያዊዉ ገበሬu ፈጣሪዉን ባማረረበት ዘመን።
«በድርቅ ጊዜ ተክሎች ይረግፋሉ።መሬቱም በርጋፊ ተክሎች በአቧራና አሸዋ ይሞላል።አዋራና አሸዋዉ ንፋስ ከነፈሰ በቀላሉ ይወሰዳል።ዝናብ ሲጥል በዉሐ እየተጠረገ በየወንዙና ዉኃ ማቋቸዉ ይደላደላል።ደለሉ ወንዙን ወይም ኩሬዉን ስለሚሞላዉ ዉኃዉ በቀላሉ እየተፋ አካባቢዉን ያጥለቀልቀዋል።»
4200 ኪሎ ሜትር የሚጓዘዉ ኒጀር ከአፍሪቃ 3ኛዉ ረጅም ወንዝ ነዉ።በወንዙ ግራና ቀኝ 160 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖራል።የባካዮኮ መስሪያ ቤት ሙሉ አቅም ባይኖረዉም ስለድርቅና የዉኃ ሙላት ምክንያትና ዉጤቱ የሚያደርገዉን ጥናት ለየአካባቢዉ መንግስታት ማጋራቱ አልቀረም።መንግስታት በየሕዝባቸዉ ላይ የሚደርሰዉን አደጋ መቀነስ ግን አልቻሉም ወይም አልፈለጉም።ይሁንና በኒጀርና በገባሮቹ ላይ የሚደረገዉን ዓይነት ጥናት ለማድረግ ከምዕራብ አፍሪቃ የቮልታ ወንዝ፣ ከምስራቅ የቪክቶሪያ ሐይቅ፣ ከደቡብ የኦካቫንጎ ወንዝ ተዋሳኝ ሐገራት ሽር ጉድ እያሉ ነዉ።በተደጋጋሚ ድርቅ የሚመታዉን አካባቢ የሚያቋርጠዉ የረጅሙ የዓለም ወንዝ የአባይ ተዋሳኞች ግን ከጋራ ጥናት ይልቅ የርስ በርስ ጠቡን ነዉ ያስቀደሙት።
ነጋሽ መሐመድ