1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጎርፍ ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ አደረገ

ሐሙስ፣ ኅዳር 27 2016

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኦሞ ወንዝ ሙላት ያስከተለው ጎርፍ ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ ማድረጉን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ (ኦቻ) አስታወቀ። በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ጎርፍ 6 ትምህርት ቤቶችን ሲያወድም ሌሎች 8 ትምህርት ቤቶችም አሁንም በውሃ ተከበው እንደሚገኙ ኦቻ ገልጿል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ጎርፍ 6 ትምህርት ቤቶችን ሲያወድም ሌሎች 8 ትምህርት ቤቶችም አሁንም በውሃ ተከበው እንደሚገኙ ኦቻ ገልጿል። ከነዚህ ትምሕርት ቤቶች አንዱ በዚህ ፎቶ ላይ የሚታየው ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኦሞ ወንዝ ሙላት ያስከተለው ጎርፍ ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ አደረገ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ / ኦቻ / አስታወቀ። በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ጎርፍ 6 ትምህርት ቤቶችን ሲያወድም ሌሎች 8 ትምህርት ቤቶችም አሁንም በውሃ ተከበው እንደሚገኙ ኦቻ ገልጿል።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

3ሺህ148 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል

This browser does not support the audio element.

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሁን ላይ በኢትዮጵያ ጎርፋ እና መሬት መንሸራተትን ጨምሮ በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከ760 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለችግር ተጋልጠዋል ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ቅንጅት ጽህፈት ቤት (ኦቻ) እንደሚለው የተፈጥሮ አደጋው የደረሰው ከባለፈው የጥቅምት ወር መግቢያ አንስቶ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የጣለውን ዝናብ ተከትሎ ነው ፡፡

ደቡብ ኢትዮጵያ ፣ ኦሮሚያ ፣ የሶማሌ እና የአፋር ክልሎች በክስተቱ የሰዎች መፈናቀል ካጋጠማቸው መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ ፡፡ በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች የመሠረተ ልማት መስመሮች በጎርፉ በመጎዳታቸው አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ አዳጋች እንዳደረገው ጽህፈት ቤቱ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

የትምህርት መታጎል

በኢትዮጵያ በተራራማ አካባቢዎች የጣለው ከልክ ያለፈ ዝናብ በዝቅተኛ የቆላማ አካባቢዎች በጎርፍ አደጋ እንዲጠቁ ምክንያት መሆኑን የሰብአዊ ጉዳዮች ቅንጅት ጽህፈት ቤት / ኦቻ /  በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ አሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሙላት ከ69 ሺህ በላይ ሰዎችን ማፈናቀሉ ነው የተነገረው

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኦሞ ወንዝ ሙላት በጎርፍ የተጥለቀለቁ ቤቶች ።የውሀ ማጥለቅለቁ 80 ሺህ ነዋሪዎችን አፈናቅሏል።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹት የዳሰነች ተፈናቃዮች

አሁን ላይ ለተፈናቃዮቹ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ሪፖርቱ አመልክቷል ፡፡ ያም ሆኖ ጎርፉ በወረዳው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ባደረሰው ጉዳት ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ ማድረጉንም ጽህፈት ቤቱ  አስታውቋል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጥጋቡ ጎሮጊ በኦሞ ወንዝ ሙላት ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት በወረዳው የመማር ማስተማር ሥራው መስተጓጎሉን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡

የወንዙ ሙላት ባስከተለው ጎርፍ 14 ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የጠቀሱት የትምህርት መምሪያ ሃላፊው አቶ ጥጋቡ “ ከእነዚህም ውስጥ ስድስቱ ሙሉ በሙሉ በጎርፍ የወደሙ ናቸው ፡፡ ቀሪዎች ስምንቱ ደግሞ አሁን ድረስ በውሃ እንደተከበቡ ይገኛሉ ፡፡ በዚህም የተነሳ 1ሺህ 860 ወንዶች እና  1 ሺህ 288 ሴቶች በድምሩ 3ሺህ148 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ለመሆን ተገደዋል “ ብለዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎርፍ ያጥለቀለቀው ትምሕርት ቤት ምስል South Omo Zone Government

አሁናዊ ሁኔታ እና የመልሶ መቋቋም ጉዳይ

የትምህርት ሥራው የተቋረጠው ትምህርት ቤቶቹ በጎርፉ በመጎዳታቸው ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡ በውሃ ከተከበቡት ቀበሌያት በመውጣት ወደ ደረቃማ አካባቢዎች በመሄዱ መሆኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ሃላፊው ተናግረዋል ፡፡ አሁን ላይ የተቋረጠውን የትምህርት ሥራ ለማስቀጠል ተማሪዎች በተፈናቀሉበት ቦታ ሆነው እንዲማሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሃላፊው “ ተማሪዎች በጊዜያዊ ድንኳን ውስጥ ሆነው ያቋረጡትን ትምህርት እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየሠራን እንገኛለን ፡፡ አሁን ላይ በቂ ባይሆንም ለማስጀመሪያ ያህል ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ፣ ዎርልድ ቪዢን እና ኢማጅን ዋን ዴይ ከተባለ ፕሮጀክት የቁሳቁስ ድጋፍ አግኝተናል» ብለዋል።

በሕይወትና ንብረት ጉዳት ያደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ በኢትዮጵያ

በጎርፍ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመጠገን ከ12 ሚሊየን በላይ ወጪን እንደሚጠይቅ በልየታ መረጋገጡን የጠቀሱት የትምህርት መምሪያ ሃላፊው ለዚህም ለተለያዩ አካላት የድጋፍ ጥሪን አቅርበዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW